አረብ ኤምሬትስ በየመን ፖለቲካዊ ግድያዎችን በገንዘብ መደገፏን የቢቢሲ ምርመራ አጋለጠ

በየመን በፖለቲካ ምክንያት ለተፈጸሙ ግድያዎች የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓን ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ እንደደረሰበት አስታውቋል።
የየመን መንግሥት እና ተፋላሚ ወገኖችን ያሳተፈው ግጭት ከመባባሱ ባለፈ በቅርቡ የዓለምን ትኩረት ወደ ሳበውና በቀይ ባሕር መርከቦች ላይ ወደተፈጸመው ጥቃት ፊቱን አዙሯል።
አሜሪካውያን ቅጥረኞች መቀመጫቸውን በየመን ላደረጉ የኤምሬትስ መኮንኖች የፀረ-ሽብር ሥልጠና ይሰጣሉ። ኤምሬቶች ደግሞ ያገኙትን ሥልጠና በዝቅተኛ ደረጃ ለሚሠሩ የየመን ዜጎችን ያካፍላሉ።
ይህ ደግሞ ፖለቲካዊ ግድያዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስፋፋ መንገድ ከፍቷል ሲል አንድ መረጃ አቀባይ ለቢቢሲ አረብኛ ምርመራ ዘጋቢ ተናግሯል።
የአሜሪካ ቅጥረኞች ዓላማ በደቡባዊ የመን የሚገኙትን አልቃኢዳ እና ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) የተባሉትን ጂሃዲስት ቡድኖችን ለማጥፋት መሆኑን ይገልጻሉ። ቢቢሲ ግን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የቀድሞ የአልቃኢዳ አባላትን ለፀጥታ ኃይል መመልመሏን አረጋግጧል። የምልመላው ትኩረት ደግሞ በየመን የሁቲ አማፂያንን እና ሌሎች የታጠቁ ቡድኖችን ለመዋጋት በሚል ነው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት ከሽብርተኝነት ጋር ግንኙነት የሌላቸውን መገደላቸውን በተመለከተ ቢቢሲ በምርመራ ማረጋገጡን “ውሸት እና መሠረት የሌለው” በማለት ውድቅ አድርጎታል።
በየመን በሦስት ዓመታት ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ ግድያዎች ተፈጽመዋል። ይህም የመን ውስጥ ዓለም አቀፍ ኃይሎችን እያጋጨ ያለው መራራው የእርስ በእርስ ጦርነት አንዱ አካል ነው።
ግድያው ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን የአገሪቱን መንግሥት በቋሚነት ወደ መንበሩ እንዳይመለስ እንቅፋት ሆኗል። ይህም በተዘዋዋሪ በኢራን የሚደገፉትን ሁቲዎችን የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል ማለት ይቻላል።
ቡድኑ በአሁኑ ጊዜ መርከቦችን በማጥቃት እና የቀይ ባሕር ንግድን በማወክ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስቧል። ዋሽንግተን ቡድኑን “ዓለም አቀፍ አሸባሪ” በማለት በድጋሚ እንደምትፈርጀው ከሰሞኑ አስታውቃለች።
የመን ወደ ግጭት ያመራችው እአአ ከ2014 ጀምሮ ነው። ጦርነቱ ሁቲዎች ሰሜን የመንን እንዲቆጣጠሩ በር ከፈተ እና በጊዜ ሂደትም በመሣሪያ እንዲጠናከሩ ያደረገ ነው።
እአአ በ2015 የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ቁልፍ አባል በሆነችበት፣ ሳዑዲ አረቢያ የምትመራው እና በአብዛኛው አረብ አገራት ያሉበትን ጥምረት አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ደግፈውታል።
ጥምር ኃይሉ የመንን በመውረር በግዞት ላይ ያለውን መንግሥት ለመመለስ እና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ዘመቻ ጀመረ።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በደቡብ ያለውን የፀጥታ ጉዳይ በበላይነት እንድትመራ ኃላፊነት ተሰጣት። ሽብረተኝነትን በመከላከል ረገድም የአሜሪካ ቁልፍ አጋር ለመሆን በቃች። አልቃይዳ በደቡብ አካባቢ ለረዥም ጊዜ የነበረውን የበላይነት አሁን በማስፋት ላይ ይገኛል።
የየመን ግጭት
- እአአ በ2014 በየመን አናሳ ከሆኑት የሺዓ ሙስሊም የሚመመዘዙት የሁቲ አማጽያን መዲናዋ ሰነዓን ተቆጣጠሩ።
- ፕሬዝዳንት አብድራቡህ ማንሱር ሃዲ በ2015 ሰንዓ ውስጥ ከነበሩበት የቁም እስር በመሸሽ በደቡባዊቷ ኤደን ከተማ ጊዜያዊ ዋና ከተማ አቋቋሙ።
- ሳዑዲ አረቢያ እና በአብዛኛው የሱኒ አረብ የሆኑ ሌሎች ስምንት አገራት በተቀናቃኛቸው ኢራን ይደገፋሉ የሚሏቸው ሁቲዎች ላይ የአየር ጥቃት ጀመሩ። በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት ከአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ከፈረንሳይ ድጋፍ አግኝቷል።
- በአንድ ወገን በተሰለፉት መካከልም ግጭት ተፈጥሯል። እአአ በ2019 በደቡብ በሳዑዲ በሚደገፉ የመንግሥት ኃይሎች እና በተባባሪው ሳውዘርን ትራንዚሽናል ካውንስል (ኤስቲሲ) መካከል ጦርነት ተቀሰቀሰ።
- የአልቃይዳ የአረቢያ አካባቢ ታጣቂዎች እና ተቀናቃኙ ኢስላሚክ ስቴት (አይ ኤስ) ግርግሩን ተጠቅመው በደቡብ የሚገኘውን ግዛት ከመያዝ ባለፈ፣ በተለይም በአደን ሕይወት የቀጠፉ ጥቃቶችን አድርሰዋል።
- ሁቲዎች ተጽእኗቸውን አስፍተዋል። እአአ ከ2023 ጀምሮ በቀይ ባሕር በሚተላለፉ ዓለም አቀፍ መርከቦች ላይ ጥቃቶችን መፈጸም ጀመሩ።
በዚህም ሳቢያ በአካbኣቢው መረጋጋት ራቀ። የየመን መንግሥት በሚቆጣጠራቸው ደቡባዊ አካባቢዎች ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ዜጎች ጭምር በምሥጢር መገደላቸው ሌላ ስጋትን ፈጠረ።
በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በዘፈቀደ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ግድያ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ እንደተፈጸመ ይቆጠራል።
ከተገደሉት መካከል አብዛኞቹ የኢስላህ አባላት ናቸው። ቡድኑ የሙስሊም ብራዘርሁድ የየመን ቅርንጫፍ ነው። ቡድኑ ታዋቂ ዓለም አቀፍ የሱኒ እስልምና እንቅስቃሴ አካል ነው። በአሜሪካ በአሸባሪነት ባይፈረጅም በአረብ አገራት ታግዷል። የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ቡድኑ የፖለቲካ እንቅስቃሴዋን እና ለአገሪቱ ንጉሣዊ ቤተሰብ አገዛዝ እንደ ስጋት ትቆጥረዋለች።
ሾልኮ የወጣው የመጀመሪያው በሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮን የተደረገ ጥቃት ለዚህ ምርመራ መነሻ ምክንያት ሆኗል። ጥቃቱ እአአ 2015 የተፈጸመ ሲሆን፣ ከጀርባው ደግሞ ስፒር ኦፕሬሽን ግሩፕ የተባለ የአሜሪካ የግል የደኅንነት ኩባንያ አባላት ይገኙበታል።
በምስሉ ላይ ከሚታዩት የዘመቻው አንቀሳቃሾች መካከል አንዱን እአአ በ2020 ለንደን ውስጥ በሚገኝ ምግብ ቤት ውስጥ ቢቢሲ አግኝቶታል። የቀድሞው የአሜሪካ ባሕር ኃይል አባል እና በኋላም የስፒር ዋና የዘመቻ ባልደረባ የሆነው አይዛክ ጊልሞር የመን ውስጥ ግድያ ለመፈጸም በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንደተቀጠሩ ከሚናገሩ አሜሪካውያን መካከል አንዱ ነው።

የፎቶው ባለመብት, JACK GARLAND/BBC
በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለስፒር በቀረበው “የሚገደሉ ሰዎች ዝርዝር” ውስጥ ስለተካተቱት ሰዎች ለመናገር ፈቃደኛ አልሆነም። በመጀመሪያ ዒላማ ያደረጉት የየመን የፓርላማ አባል የሆኑትን እና መቀመጫቸው በአደን የሆነውን የኢስላህ መሪ የሆኑት አንሳፍ ማዮን ነው።
ኢስላህ በአሜሪካ ባለሥልጣናት በአሸባሪነት አልተፈረጀም።
“ዘመናዊ ግጭቶች በሚያሳዝን ሁኔታ በጣም ግልጽ አይደሉም። ይህንን በየመን እናያለን። የአንድ የቡድን መሪ ለአንዱ የሃይማኖት አባት፣ የሌላው አሸባሪ መሪ ነው” ብሏል።
ጊልሞር እና በወቅቱ የመን ውስጥ የስፒር ባልደረባ የነበረው ዴል ኮምስቶክ የጀመሩት ተልእኮ በ2016 እንዳበቃ ተናግረዋል። በደቡብ የመን ያለው ግድያ ግን ቀጥሏል። የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነው ሪፕሪቭ መርማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ ግድያዎቹ ይበልጥ ተደጋጋሚ ሆነዋል።
እአአ ከ2015 እስከ 2018 ድረስ በየመን የተፈጸሙ 160 ግድያዎችን መርምረዋል። አብዛኞቹ ከ2016 ጀምሮ የተፈጸሙ ሲሆኑ፣ ከተገደሉት 160 ሰዎች መካከል 23ቱ ብቻ ከሽብርተኝነት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሁሉም ግድያዎች የተፈጸሙት የስፒርን ተመሳሳይ ዘዴ በመጠቀም ነው። የተቀበረ ፈንጂ በማፈንዳት ዐይኖች ሁሉ ወደዚያ ሲሆኑ ዒላማ የተደረገው ግለሰብ ተተኩሶ ይገደላል።
የየመን የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ሁዳ አል ሳራሪ እንደተናገሩት በቅርብ ጊዜ የተደረገው ፖለቲካዊ ግድያ ባለፈው ወር የተፈጸመ ነው። ላህጅ ውስጥ በተመሳሳይ መንገድ አንድ ኢማም ተገድለዋል።
ጊልሞር፣ ኮምስቶክ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሁለት የስፒር ቅጥረኞች እንደገለጹት ከሆኑ ስፒር በአደን በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወታደራዊ ካምፕ፣ የኤምሬትስ መኮንኖችን በማሠልጠን ተሳትፏል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቀ ጋዜጠኛም ይህን የመሰለ የሥልጠና ምስል ማየቱን ገልጾልናል።
ቅጥረኞቹ ምን እንደሆነ በዝርዝር ባይናገሩም ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር በቀጥታ የሠሩ ከፍተኛ የየመን ወታደራዊ መኮንን ዝርዝር መረጃ ሰጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, JACK GARLAND/BBC
ቅጥረኞቹ እንዳይታወቁ እና ተጋላጭ እንዳያደርጋቸው ጉዳዩ የኤምሬትስ መኮንኖች ሥልጠና በሚል ተለውጧል። “የመን ዜጎች ግዳጁን እንዲፈጽሙ ደግሞ ከኤምራትስ ሥልጠና ያገኛሉ” ሲሉ የየመን ወታደራዊ መኮንን ነግረውናል።
በምርመራው ሂደትም ከደርዘን በላይ የሚሆኑ ሌሎች የየመን ምንጮችን አነጋግረን ይህንኑ አረጋግጠናል። በኤምሬትስ ወታደሮች ሠልጥነው ከሽብር ጋር ያልተያያዙ ግድያዎችን ፈጽመናል ያሉ ሁለት ሰዎችን እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እስር ቤት ለመፈታት አንድን የመናዊ ፖለቲከኛ አንዲገድል ጥያቄ የቀረበለት አንድ ሰው ይገኙበታል። የግለሰቡ ተልዕኮውን አልተቀበለውም።
የመናውያን ግድያውን እንዲፈጽሙ መደረጉ ግድያው ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር አንዲያያዝ የሚያደርገውን መንገድ ከባድ ያደርገዋል።
እአአ በ2017 የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በደቡባዊ የመን ዙሪያ የታጠቁ ቡድኖችን የሚያስተዳድረውን ሳውዘርን ትራንዚሽናል ካውንስልን (ኤስቲሲ) የመከላከያ ኃይል በኤምሬትስ የገንዘብ ድጋፍ እንዲገነባ ረድታለች።
ኃይሉ በደቡብ የመን ከአገሪቱ መንግሥት ነፃ ሆኖ ይንቀሳቀስ ነበረ። ትዕዛዝም ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ብቻ ይቀበል ነበር። ተዋጊዎቹ በጦር ግንባር ላይ ለመዋጋት ብቻ የሠለጠኑ አልነበሩም። አንድ መረጃ አቀባይ እንደነገሩን የፀረ ሽብር ቡድኑ ግድያዎችንም ለማከናወንም የሠለጠነ ነው።
መረጃ አቀባዩ አሁን ኤስቲሲ ውስጥ የሚሠሩ 11 የቀድሞ የአልቃኢዳ አባላትን ስም የያዘ ሰነድም ልኮልናል። የተወሰኑትን ማንነትም ማረጋገጥ ችለናል።
በምርመራችን ወቅት ናስር አል-ሺባን የሚል ስም አጋጥሞናል። በአንድ ወቅት የአልቃኢዳ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሆኖ በአሸባሪነት ቢታሰርም በኋላ ላይ ግን ተፈትቷል።
ጥቅምት 2000 ላይ 17 አሜሪካውያን መርከበኞችን በገደለው ዩኤስኤስ ኮል በተሰኘው የአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ አል-ሺባ ተጠርጣሪ እንደነበር ያነጋገርናቸው የየመን መንግሥት ሚኒስትር ነግረውናል። በርካታ ምንጮች እንደነገሩን ከሆነ አሁን ከኤስቲሲ ወታደራዊ ክፍሎች የአንዱ አዛዥ ነው።

የሕግ ባለሙያዋ ሁዳ አል ሳራሪ በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የሚደገፉ ኃይሎች የፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ረገጣ ስትመረምር ቆይታለች። በሥራዋ ምክንያት በተደጋጋሚ የግድያ ዛቻዎች ደርሷታል። ጽዋውን የጠጣው ግን የ18 ዓመቱ ልጇ ሞህሰን ነበር።
እአአ በ2019 ወደ አካባቢው የነዳጅ ማደያ ሲጓዝ ደረቱ ላይ በጥይት ተመትቶ ከአንድ ወር በኋላ ሕይወቱ አልፏል። ሁዳ ከልጇ ሞት በኋላ ወደ ሥራ ስትመለስ የጠበቃት ሁሉን ነገር እንድታቆም የሚያስጠነቅቅ መልዕክት እንደሆነ ትናገራለች። “የአንዱ ልጅ አይበቃም? ሌሎቻችሁንም እንድንገድል ትፈልጋላችሁ?” ብለዋል።
የአደን ዐቃቤ ሕግ ባደረገው ምርመራ ሞህሰን የተገደለው በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሚደገፈው የፀረ ሽብርተኝነት ቡድን አባል እንደሆነ ቢያረጋግጥም ክስ ግን አልተመሠረተም።
ለደኅንነት ሲባል ስማቸውን መጥቀስ ያልቻልነው የዐቃቤ ሕግ አባላት የተስፋፋው ግድያ የፍርሃት ድባብ ፈጥሯል ብለዋል። ይህም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚደገፉ ኃይሎችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ፍትህ እንዲሰጥ ለማድርገ በጣም እንደሚፈሩ ነግረውናል።
ስፒር በ2020ም እየተከፈለው መሆኑን የሚያሳይ ሾልኮ የወጣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሰነድ ለሪፕራይቭ ደርሶታል። ምንም እንኳን ምን ሠርቶ የሚለው ግልጽ አይደለም።
የስፒር መሥራች የሆነው አብርሀም ጎላን ቅጥረኞቻቸው ለኤምሬቶች የግድያ ቴክኒኮችን አሠልጥነዋል ወይ? ብለን ብንጠይቅም ምላሽ አልሰጠም።
ምርመራችንን በተመለከ ለተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ መንግሥት ጥያቄ አቅርበናል።
ጥቃቱ ከሽብርተኝነት ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ መባሉ ከእውነት የራቀ መሆኑን እና በየመን የሚካሄደውን የፀረ ሽብር ዘመቻ የሚደግፈው በየመን መንግሥት እና በዓለም አቀፍ አጋሮቹ ግብዣ መሆኑን ጠቅሷል።
“የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በእነዚህ ዘመቻዎች ላይ ዓለም አቀፍ ተፈፃሚነት ያለውን ሕግን በማክበር ተንቀሳቅሳለች” ብሏል።
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ ስፒር ኦፕሬሽን ግሩፕ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁም ለምላሽ ፈቃደኛ አልሆኑም።
የአሜሪካ የስለላ ድርጅት በሰጠው መግለጫ “ሲአይኤ እንዲህ አይነት ዘመቻ እንዲፈጸም ፈቅዷል የሚለው ሐሳብ ውሸት ነው” ብሏል።












