በኢራን ተቀጥሮ ኔታኒያሁን ሊገድል አሲሯል የተባለው እስራኤላዊ በቁጥጥር ሥር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
አንድ እስራኤላዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ለመግደል ኢራን በነደፈችው ሴራ ላይ ተሳትፏል በሚል በቁጥጥር ሥር መዋሉን የእስራኤል ደኅንነት መሥሪያ ቤት አስታወቀ።
የእስራኤል ፖሊስ እና የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እንዳሉት፣ ሰውየው ሁለት ጊዜ በድብቅ ወደ ኢራን አቅንቶ ለዕቅዱ ክፍያ ተቀብሎ መጥቷል።
ሁለቱ መሥሪያ ቤቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ እንደገለፁት ግለሰቡ ቱርክ ይኖር የነበረ ነጋዴ ሲሆን፣ የቱርክ አጋሮቹ ናቸው ወደ ኢራን እንዲገባ ያመቻቹለት።
ቀጣናዊ ባላንጣ የሆኑት እስራኤል እና ኢራን ከፍተኛ ውጥረት ላይ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ነው ይህ የግድያ ሴራ ዜና የተሰማው።
መግለጫው እንደሚለው ስሙ ያልተገለፀው ግለሰብ ባለፈው ወር ነው በቁጥጥር ሥር የዋለው። ለግድያ ዒላማ ተድርገው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ እና የእስራኤል አገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ናቸው ተብሏል።
በመግለጫው መሠረት ተጠርጣሪው ባለፈው ሚያዝያ እና ግንቦት ወራት ሁለት ጊዜ ቱርክ ወደምትገኘው ሳማንዳግ ተጉዞ ኤዲ ከተባለ ሀብታም ኢራናዊ ጋር የተገናኘ ሲሆን፣ ሁለት ቱርካዊ ዜጎች ሲረዱት ነበር።
ኤዲ የተባለው ግለሰብ ከኢራን መውጣት ስላልቻለ እስራኤላዊው ከቱርክ ወደ ኢራን እንዲጓዝ ተደርጓል ተብሏል። ግለሰቡ ወደ ኢራን ከገባ በኋላ ኤዲን እና “የኢራን ደኅንነት ባለሙያዎችን” እንዳገኘ መግለጫው ይጠቅሳል።
ኤዲ እስራኤላዊውን ግለሰብ “እስራኤል ውስጥ ከኢራን አገዛዝ የተላለፉ የተለያዩ ትዕዛዞችን እንዲፈፅም” ጠይቆታል ብሏል የወጣው መግለጫው።
ገንዘብ እና ሽጉጥ ማዘዋወር፣ እስራኤል ውስጥ የሚገኙ ሕዝብ የሚበዛባቸውን ቦታዎች ፎቶግራፍ አንስቶ ለኢራን መስጠት እንዲሁም በኢራን ሥራ የተሰጣቸውን ሌሎች እስራኤላውያንን ማስፈራራት ከተልዕኮዎቹ መካከል መሆናቸውን ይገልፃል።
እስራኤላዊው ግለሰብ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢራን ባቀናበት ወቅት የአገሪቱ ደኅንነት ሰዎች ግለሰቡ እስራኤል ውስጥ የሽብር ጥቃት እንዲፈፅም በተለይ ደግሞ ኔታኒያሁ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ የዋቭ ጋላንት እና የደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊውን ሮኔን ባርን እንዲገልድ ጠይቀውታል ይላል።
ኢራን ውስጥ የተፈጸመውን የሐማስ መሪ ኢስማኢል ሃኒያ ግድያን ለመበቀል ሲባል የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት እና ሌሎች ታዋቂ ሰዎችን ለመግደል ታቅዶ እንደነበር በምርመራ መጣራቱን መግለጫው ያትታል።
ኢራን ለሃኒያ ግድያ እስራኤልን ተጠያቂ ብታደርግም እስራኤል ግን በድርጊቱ ስለመሳተፏ የእምነትም ሆነ የክህደት ቃል ሰጥታ አታውቅም።
መርማሪዎች እንደሚሉት እስራኤላዊው ግለሰብ ለዚህ ዕቅዱ አንድ ሚሊዮን ዶላር ቀብድ ጠይቋል።
ይህን ድርጊት ለመፈፀም አቅደዋል የተባሉት ሰዎች በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሚገኙ የኢራን መንግሥት ተቃዋሚዎችን ለመግደል እንዲሁም የሞሳድ (የእስራኤል ስለላ ተቋም) ሰዎችን አጥምዶ “መረጃ እንዲያመላልሱ” ለማድረግ አስበዋል ተብለው ተጠርጥረዋል።
እስራኤላዊው ግለሰብ ከሰዎቹ ጋር ተቀምጦ ስላወራ 5 ሺህ ዩሮ እንደተከፈለው መግለጫው ያትታል።
የእስራኤል የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት የሆነው ሺን ቤት ባለሥልጣን ይህ “የኢራን ደኅንነት ሰዎች እስራኤላዊ ዜጋ መልምለው እስራኤል ውስጥ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም የሚያደርጉት ጥረት ማሳያ ነው” ብለዋል።
የወቅቱ የኢራን አገዛዝ በአውሮፓውያኑ 1979 በኢስላማዊ አብዮት ወደሥልጣን ከመጣ በኋላ እስራኤል እና ኢራን ዓይን እና ናጫ ሆነው ቆይተዋል።
ኢራን ለእስራኤል ኅልውና እውቅና የማትሰጥ ሲሆን፣ እንደ ሐማስ እና ሄዝቦላህ ላሉ እስራኤልን ለሚዋጉ ቡድኖች ድጋፍ ታደርጋለች።
በተለይ በጋዛ ባለው ጦርነት ምክንያት በኢራን እና በእስራኤል መካከል ያለው መቃቃር የጠነከረ ሲሆን፣ በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት ሁለቱም አገራት ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ ጥቃት ተሰነዛዝረዋል።












