ሊቨርፑል ከማንቸስተር ሲቲ እና ሌሎች የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተጠባቂ ጨዋታዎች ግምት

ክሎፕ እና ጓርዲዮላ

ማንቸስተር ሲቲ በያዝነው የውድድር ዓመት ከላይ ካሉት አምስት ቡድኖች ጋር ተገናኝቶ አንድም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም። እሑድ ከሊቨርፑል ጋር ሲገናኙ ይህ ይቀየር ይሆን?

የቢቢሲው የስፖርት ተንታኝ ክሪስ ሱተን “ከላይ ያሉ ክለቦች እርስ በርስ ተገናኝተው የሚመጣው ውጤት ዋንጫው ወደየት እንደሚሄድ ያሳያል” ይላል።

“ሲቲ ወደ አንፊልድ ተጉዞ ይህ ነው የሚባል የበላይነት አያሳይም። ባለፉት ሰባት ፍልሚያዎች አንድ ጊዜ ብቻ ነው ድል የቀናው። ነገር ግን ሲቲ ይሸነፋል ብሎ መገመት የዋህነት ነው” ይላል ሱተን።

ሱተን የዚህን ተጠባቂ ጨዋታ ጨምሮ የሌሎች የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን ግምት እንዲህ አስቀምጧል።

እሑድ

አስተን ቪላ ከቶትንሃም

በዚህ ዓመት የሚደረጉ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ለመገመት አስቸጋሪ ሆነዋል።

ባልተጠበቀ ሁኔታ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኙ ቡድኖች አስደናቂ ውጤት የሚያስመዘግቡበት አጋጣሚ አለ።

አስተን ቪላዎች በሜዳቸው ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው። በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየደከሙ የመጡ ይመስላሉ።

ቶተንሃሞች እንደ ጄምስ ማዲሰን የመሳሰሉት ወሳኝ ተጫዋቾችን በጉዳት በማጣቱ አስተን ቪላዎች የማሸነፍ ዕድል እንዳላቸው ሱተን ይገምታል።

ለእንደዚህ አይነት ጨዋታ የማዲሰን አለመኖር የቶትንሃምን የአጥቂ ክፍል እንቅስቀሴ ይገታዋል።

በአንጻሩ የቪላው ኦሊ ዋትኪንስ ደግሞ የቶትንሃም የተከላካይ ክፍል በማስጨነቅ ልዩነት እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

ግምት 3 - 2

ብራይተን ከኖቲንግሀም ፎሬስት

ብራይተን ከኖቲንግሀም ፎሬስት

የአውሮፓ እግር ኳስ ይሁን ያዳከማቸው አሊያም ሌላ ነገር አላውቅም፤ ነገር ግን ብራይተኖች እጅግ ወርደዋል። እርግጥ ነው በሜዳቸው ያላቸው ክብረ-ወሰን መልካም የሚባል ነው። ቢሆንም ሐሙስ ዕለት በሮማ መሸነፋቸው ሌላ ጉዳት ነው።

ኖቲንግሀም ፎሬስት ባለፈው ሳምንት በእንጥፍጣፊ ደቂቃ በሊቨርፑል በመረታታቸው ዳኛውን ሲወቅሱ ነበር።

ፎሬስት አሁንም ብስጭት ላይ እንዳሉ ይሰማኛል። ብራይተን ከዚህ ጨዋታ የተሻለ ነገር የሚያገኝ ይመስለኛል።

ግምት 2 - 1

ዌስት ሀም ከበርንሊ

በርንሊ ከፕሪሚዬር ሊጉ ወርደዋል ማለት ይቀላል። እንደ ቡድን ሲጫወቱ ደስ ይላሉ ነገር ግን ጥርስ የላቸውም።

የዌስትሃም ደጋፊዎች በዴቪድ ሞየስ አጨዋወት እየተደሰትን አይደለም እያሉ ነው። ነገር ግን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ዌስትሃም ሰባት ጎግቦች አስቆጥሯል።

ሞየስ ብሬንትፈርድ እና ኤቨርተንን በመርታት ወደ ሰባተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።

እርግጥ ነው ዌስትሃም በአውሮፓ ሊግ ወደ ጀርመን ተጉዞ የአውሮፓ ሊግ ፍልሚያ አድርጎ ተመልሷል። ይህ ጉዞ ምን ያክል ይጎዳቸዋል የሚለውን እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም። ነገር ግን ይሸነፋሉ ብዬ አላስብም።

ግምት፡ 2 - 0

የሊቨርፑል እና የሲቲ ሎጎ

ሊቨርፑል ከማን. ሲቲ

ሲቲ የፕሪሚዬር ሊጉ ሻምፒዮን ነው። የአውሮፓም ሻምፒዮን ነው። የዓለምም ሻምፒዮን ነው። እና ማነው ይሸነፋሉ የሚለው? እኔ ግን ይሸነፋሉ ባይ ነኝ።

ሊቨርፑል በሜዳ እንደመጫወቱ እና ሞሐመድ ሳላህ ወደ ሜዳ በመመለሱ ሲቲ ይህን ጨዋታ የማሸነፍ ዕድል የለውም እንድል ያደርገኛል።

እርግጥ ነው ጨዋታው ሲጠናቀቅ ምናልባት በማየው ውጤት እኔው ራሴ ልቆጭ እችል ይሆናል። ነገር ግን ዳርዊን ኑኔዝ ያስቆጥራል፤ ሊቨርፑል ያሸንፋል እላለሁ።

ግምት፡ 2 - 1

ሰኞ

የቼልሲ እና ኒውካስል ሎጎ

ቼልሲ ከኒውካስል

እንዴት ነው አንድ ሰው ቼልሲ ከኒውካስል ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ መገመት የሚችለው? ሁለቱም ክለቦች አቋማቸው ይዋዥቃል።

የትኛውን የቼልሲ ቡድን ነው የምናየው? የትኛውስ የኒውካስል ቡድን ወደ ስታምፈርድ ብሪጅ ይመጣል?

ኒውካስል በአርሰናል ከደረሰበት ሸንፈት ዎልቭስን በመርታት አገግሟል። ነገር ግን ካለፈው ታኅሣሥ ጀምሮ በተከታታይ ሁለት ጨዋታ አሸንፎ አያውቅም።

ቼልሲ በሜዳው ያሸንፋል ብዬ ስንት ጊዜ ገምቼ ስንት ጊዜ ተሳስቻለሁ። ነገር ግን ይህን ጨዋታ ማሸነፍ አለባቸው የሚል ዕምነት አለኝ።

ግምት፡ 3 - 1

ቅዳሜ [ውጤታቸው የታወቁ ጨዋታዎች]

የዩናይትድ እና ኤቨርተን ሎጎ

ማንቸስተር ዩናይትድ ከኤቨርተን

ኤቨርተን ከሰሞኑ እያሳየ ያለው አቋም እጅግ የወረደ ነው። ነገር ግን ማንቸስተር ዩናይትድ ይህን ጨዋታ ይረታል ብዬ በልበ ሙሉነት መናገር ይከብደኛል።

ባለፈው ኅዳር ዩናይትድ ወደ ጉዲሰን ፓርክ ተጉዞ 3-0 አሸንፎ ቢመለስም በጨዋታው ተፈትኖ ነበር።

ይህ ጨዋታ አቻ ይጠናቀቃል ብዬ መገመት እየቃጣኝ ነው። ነገር ግን ዩናይትድ ተፍጨርጭሮ ይረታል የሚል ዕምነት አለኝ።

ባለፈው ዩናይትድ ከሲቲ ሲጫወት እስከመጨረሻው ድረስ ተናንቆ ነበር የሚሉ ሰዎች አሉ። ምንም እንኳ የማርከስ ራሽፈርድ ግብ ድንቅ ብትሆንም እኔ ይህ ሐሳብ አያሳምነኝም።

ሲቲ እና ዩናይትድ ያሉበት ደረጃ እጅግ የተለያየ ነው። ምናልባት አጥቂው ራስመስ ሆይለንድ ከጉዳት ከተመለሰ ዩናይትድ መነቃቃት ሊያሳይ ይችላል።

ግምት፡ 2 - 1 [የጨዋታው ውጤት 2 - 0]

ቦርንመዝ ከሼፊልድ ዩናይትድ

ቦርንመዝ ባለፈው ሳምንት በርንሊን እንደምንም ረትቷል። ይህኛው ጨዋታ ግን እጅግ የሚቀላቸው ይመስለኛል። አጥቂው ዶሚኒክ ሶላንኬ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው እጠብቃለሁ።

ቦርንመዝ ከዚህ ጨዋታ በኋላ ከወራት በፊት ተቋርጦ የነበረውን ከሉተን ጋር የነበራቸውን ጨዋታ በሚቀጥለው ረቡዕ ያደርጋሉ።

እኔ ከሼፊልድ ጋር የሚኖራቸውን ጨዋታ የማያሸንፉ ከሆነ የሆነ ችግር እንዳለ ነው የሚገባኝ።

ሼፊልድ ባለፈው ሳምንት በአርሰናል 6 ለምንም መረታቱን ተከትሎ አሠልጣኙ ክሪስ ዊልደር ተጫዋቾቼ ቅስማቸው ተሰብሯል ብለው ነበር።

ግምት፡ 3 - 0 [የጨዋታው ውጤት 2 - 2]

ክሪስታል ፓላስ ከሉተን

ይህ ጨዋታ ለሉተን በጣም አስፈላጊ ነው። ያለፉት አራት ጨዋታዎች በተከታታይ ተሸንፈዋል። ከኤፍ ኤ ዋንጫ ውጪም ሆነዋል።

ባለፈው ጥር የነበራቸው መልካም አቋም አሁን የለም። ነገር ግን በፕሪሚዬር ሊጉ መቆየት ከፈለጉ ነጥብ መሰብሰብ ያለባቸው አሁን ነው።

በመጀመሪያው ጨዋታ ክሪስታል ፓላስን መርታታቸው ይታወሳል። አሁን ዒላማቸው እሱ ሊሆን ይገባል።

ክሪስታል ፓላሶች በበኩላቸው ኤቤሬቺ ኤዜ መመለሱ ትልቅ ደስታ ፈጥሮላቸዋል። ባለፈው ቶተንሀም ላይ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል።

ምንም እንኳ ኤዜ ሲኖር ጥሩ የሚጫወቱ ቢሆኑም አዲሱ አሠልጣኝ ኦሊቨር ግላስነር ገና በመሆናቸው መገመት አዳጋች ነው።

ግምት፡ 1 - 1 [የጨዋታው ውጤት 1 - 1]

ዎልቭስ ከፉልሀም

በዚህ ጨዋታ ዎልቭስ ልክ እንደ ኒውካስሉ ጨዋታ ተበልጦ ይሸነፋል የሚል ዕምነት የለኝም። ፉልሀምም ቢሆን ብራይተንን ያሸነፈበት ብቃት አመርቂ አልነበረም።

እርግጥ ነው የፉልሀም የሰሞኑ አቋም መልካም የሚባል ነው። ዎልቭስ ደግሞ አጥቂያቸው ማቴውስ ኩንሃ አለመኖሩ ይጎዳቸዋል።

ይህን ጨዋታ መገመት ከባድ ነው። ምንም እንኳ ፍላጎቴ አቻ ይወጣሉ የሚል ባይሆንም ጨዋታው ወደዚያ የሚያደላ ይመስላል።

ግምት፡ 1 - 1 [የጨዋታው ውጤት 2 -1]

የአርሰናል እና ብሬንትፈርድ ሎጎ

አርሰናል ከብሬንትፈርድ

አርሰናሎች እያደረጉት ያለው ነገር እየሆነላቸው ነው። በፕሪሚዬር ሊጉ በርካታ ጎሎችን እያስቆጠሩ ይገኛሉ። ይህን ጨዋታ ካሸነፉ ካለፈው ታኅሣሥ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉ አናት ላይ ይቀመጣሉ።

ካይ ሀቨርትዝ እያሳየ ላለው ብቃት ውዳሴ ይገባዋል። ብዙዎች ለምን አርቴታን አስፈረመው ሲሉ ነበር፤ ነገር ግን አሁን ያን ቅሬታቸውን የረሱት ይመስላል።

ቤን ሚ በጉልበት ጉዳት ምክንያት ከዚህ ጨዋታ ውጭ መሆኑ እጅግ ከባድ ዜና ነው። ይህ ማለት የብሬንትፈርድ የኋላ መስመር የመጀመሪያ ምርጫዎች ሙሉ በመሉ የሉም ማለት ነው።

አሮን ራምስዴል የአርሰናል ግብ ጠባቂ ነው። ምክንያቱም ዴቪድ ራያ እናት ክለቡን መግጠም አይችልም። ነገር ግን አርሰናል አሁን የግብ ጠባቂ ነገር የሚያሳስባቸው አይደለም። እኔ ግብ ጠባቂ ብሆንም ከማሸነፍ ወደ ኋላ አይሉም።

ግምት፡ 3 - 0 [የጨዋታው ውጤት 2 - 1]