በቱኒዚያ ባሕር ዳርቻ ጀልባዎች ሰጥመው 27 ስደተኞች ሳይሞቱ አይቀርም ተባለ

ስደተኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቱኒዚያ ባሕር ዳርቻ ስደተኞችን ጭነው የነበሩ ሁለት ጀልባዎች ሰጥመው 27 ሰዎች ደብዛቸው ጠፍቷል አልያም ሕይወታቸው ሳያልፍ አይቀርም ተባለ።

ከሰጠሙት ጀልባዎች መካከል መዳረሻዋን ጣሊያን ያደረገችው የመጀመሪያዋ ጀልባ ከትናንት በስቲያ አርብ ከቱኒዚያ የተነሳች ነበረች። በዚህች ጀልባ ተሳፍረው ከነበሩ መካከል 20 ስደተኞች የደረሱበት የጠፋ ሲሆን 17 ሰዎችን ግን መታደግ መቻሉን አንድ የቱኒዚያ ባለስልጣናን ተናግረዋል።

ባለፉት 4 ሳምንታት በቱኒዚያ ባሕር ዳርቻ ጀልባዎች ሲሰጥሙ ይህ ለ7ኛ ግዜ ነው። በእነዚህ አደጋዎች በጠቅላላው 100 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል ወይም ደብዛቸው ጠፍቷል።

አንዳንድ የቱኒዚያ ባሕር ጠረፈ አካባቢዎች ከጣሊያኗ ደሴት ላፔዱሳ 150 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቀው ይገኛሉ፤ በዚህም ምክንያት ከቅርብ ግዜ ወዲህ ቱኒዚያ ከሊቢያ ይልቅ የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ አውሮፓ መድረስ ለሚፈልጉ ስደተኞች ተመራጭ መሸጋገሪያ እየሆነች መጥታለች።

እንደ ቱኒዚያ የባሕር ዳርቻ ጠባቂ ተቋም ከሆነ ከአውሮፓውያኑ 2023 መጀመሪያ አንስቶ በብዛት ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገራት የሚጡ ከ14ሺህ በላይ ስደተኞች አውሮፓ ከመድረሳቸው በፊት በቱኒዚያ የባሕር ክልል ውስጥ ተይዘዋል።

መነሻቸውን ቱኒዚያ የሚያደርጉ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩን የአገሪቱ የባሕር ጥበቃ ቃል አቀባይ ሁሴም ጄባብሎ ተናግረዋል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ከሆነ በዚህ ዓመት በጣሊያን የባሕር ዳርቻ የደረሱ ቢያንስ 12 ሺህ ስደተኞች ከቱኒዚያ የተነሱ ናቸው። ይህ ቁጥር በባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት 1 ሺህ 300 ነበር።

ስደተኞች ደኅንነታቸው ባልተረጋገጡ መናኛ ጀልባዎች በመጓዝ አውሮፓ ለመድረስ ለሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ ይከፍላሉ።