ፑቲን ምዕራባውያንን የሚያስፈራሩበት ‘ታክቲካል’ ኒውክሌየር ምን ያህል አስፈሪ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያው ፑቲን ድል እየራቃቸው ነው።
ቢሊዮን ዶላሮች የሚላኩላቸው የዩክሬን ተዋጊ ኃይሎች ቁልፍ ቦታዎችን መልሰው በእጃቸው እያስገቡ ነው።
ይህ ነገር ፑቲንን አበሳጭቷቸዋል።
በሳምንታት አጠናቅቀዋለሁ ያሉት ጦርነት እንደዋዛ ሰባተኛ ወሩን ይዟል።
ከቀናት በፊት ቪላድሚር ፑቲን 300 ሺህ ተጠባባቂ ሠራዊት ክተት ብለዋል።
ምዕራባዊያን ሶቭየት ኅብረትን እንዳፈራረሱት ሩሲያን ሊበታትኑ አሲረዋል ሲሉ ከሰዋል።
ስለዚህ “ታክቲካል የኒውክሊየር የጦር መሣሪያን መጠቀም ልንገደድ እንችላለን” ሲሉ አስፈራርተዋል።
ጆ ባይደን በበኩላቸው ፑቲን አደብ እንዲገዙ አስጠንቅቀዋል።
ፑቲን እነዚህን ታክቲካል [ስልታዊ] የኒውክሊየር ጦር ማሳሪያዎችን ከተጠቀሙ ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አስጨናቂ የሚባል ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል።
ታክቲካል የኒውክሊየሮች ምንድናቸው?
ለመሆኑ ታክቲካል የሚባሉት የኒውክሊየር ጦር መሣሪያዎች በተለያዩ አገራት እጅ የሚገኙ ሲሆኑ መጠናቸው ለየት ያደርጋቸዋል።
በግርድፉ ‘አነስተኛ ኒውክሊየር ጦር መሳሪያዎች’ ልንላቸው እንችላለን።
ታክቲካል ኒውክሊየር የጦር መሣሪያዎች ከዋናዎቹ ስትራቴጂክ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያዎች የሚለዩት በሦስት ነገሮች ነው።
በስሪት መጠናቸው፣ በሚያደርሱት የጥፋት መጠን እና ጠላት ላይ ሲወድቁ በሚኖራቸው የክብደት መጠን ነው።
እርግጥ በሚወነጨፉበት ርቀት ዙሪያም ልዩነት አለ።
ቀደም ሲል እንዳልነው ታክቲካል ኒውክሊየር ጦር መሣሪያዎች ትንንሽ ናቸው።
ጥቅም ላይ የሚውሉት በጦር አውድማ ላይ ብቻ ነው።
ስትራቴጂክ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያዎች ግን አንድ ከተማን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ይውላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታክቲካል ኒውክሊየር ጦር መሣሪያዎች በጠላት ላይ ተመጣጣኝ፣ ነገር ግን ሌሎች ተወንጫፊ መሣሪያዎች ሊያደርሱ ከሚችሉት ከፍ ያለ ጉዳትን ያደርሳሉ።
ስትራቴጂክ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያዎች ግን ወታደር እና ንጹሐንን ሳይለዩ ጨርሶውኑ ከተማን ያወድማሉ።
የጉዳት መጠኑም የምጽአት ቀን የሚመስል ነው።
ታክቲካል የኒውክሊየር ጦር መሳሪያዎች በአንጻሩ የሚውሉት የጠላት የጦር መንደሮችንና ይዞታን ለማውደም ነው።
ከተተኮሱ በኋላም የከፋ የራዲዮአክቲቭ ጨረር በመልቀቅ ሰፊ ከባቢን አያወድሙም፤ እንዲሁም ለትውልድ የሚሸጋገር ጥፋትን አያስከትሉም።
ስለ ግዝፈት መጠናቸው ብናወራ ታክቲካል የኒውክሊየር ጦር መሳሪያዎች በብዛት አንድ ኪሎ ቶን ነው የሚመዝኑት።
ግዙፍ የሚባለው ደግሞ 100 ኪሎ ቶን ቢመዝን ነው።
ስትራቴጂክ የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ግን 1000 ኪሎ ቶን ይመዝናል።
የሚወነጨፈውም ከዒላማው ሩቅ ከሆነ ቦታ ላይ ነው።
ለምሳሌ አሜሪካ በጃፓን ከተማ ሒሮሺማ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ የጣለችው የኒውክሊየር ቦምብ 15 ኪሎ ቶን የሚመዝን ነበር።

ሩሲያ ምን ያህል ያላት?
እንደ አሜሪካ የስለላ መሥሪያ ቤት መረጃ ከሆነ ሩሲያ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ታክቲካል የኒውክሊየር ጦር መሣሪያዎች አሏት።
እነዚህ አውዳሚ የጦር መሣሪያዎች በብዙ ዓይነት የሚሳኤል አረሮች ሆነው ሊተኮሱ ይችላሉ።
ለምሳሌ በክሩዝ እና አርቲለሪ ሚሳኤሎች ሊተኮሱ ይችላሉ።
ታክቲካል የኒውክሊየር ጦር መሳሪያዎች ከአየር፣ ከምድር ወይም ከባሕር ላይ ሊወነጨፉ ይችላሉ።
አሜሪካ እንደምትለው ሩሲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእነዚህ ጦር መሣሪያዎች ላይ ሰፊ ሥራ እየሠራች ነው። በተለይም ዒላማቸውን እንዳይስቱ ለማድረግ የሚያስችሉ ስኬታማ ምርምሮችን አድርጋለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ውለው ያውቃሉ?
እስከዛሬ በጦርነት ውስጥ እነዚህ ታክቲካል የኒውክሊየር ጦር መሣሪያዎች አገልግሎት ላይ ውለው አያውቁም።
ይህ የሆነው ግን በአመዛኙ ሌሎች ቀላል ተወንጫፊ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ታክቲካል የኒውክሊየር ጦር መሳሪያዎችን ያህል ውጤታማ በመሆናቸው ነው።
ከዚህም በላይ በዋናነት አገልግሎት ላይ ያልዋሉት ግን ኒውክሊየር ታጣቂ ከሆኑ አገራት ውስጥ አንዳቸውም ይህን አደገኛ የጦር መሣሪያ በመጠቀም የለየለት እልቂት መጋበዝ ባለመፈለጋቸው ነው።
ይሁንና ሩሲያ አሁን አነስተኛዎቹን የታክቲካል ኒውክሊየር ጦር መሣሪያዎችን ለመጠቀም ልትገደድ ትችላለች እየተባለ ነው።
የዓለም አቀፉ የደኅንነት ፕሮግራም የጥናትና የማማከር ቡድን ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ፓትሪሺያ ሌዊስ “ለዚህም ምክንያቱ ሩሲያ እነዚህን አነስተኛ የኒውክሊየር አረሮችን መጠቀሟ ብዙም ቀይ መስመር ማለፍ አድርጋ ላታየው ትችላለች” በሚል ያስረዳሉ።

የፑቲን ዛቻ አሳሳቢ ነው?
በየካቲት 2022 ዩክሬንን ከመውረራቸው ከቀናት በፊት ፑቲን የኒውክሊየር ጦር መሣሪያዎቻችን “በከፍተኛ ተጠንቀቅ ይቁሙ” ሲሉ አዘው ነበር።
ከዚያ ወዲያ የጦር ልምምዱም ተጠናክሮ ቀጥሎ ነበር።
በቅርቡ ደግሞ ፑቲን፣ “ሉአላዊነታችን አደጋ ላይ የወደቀ ከመሰለን ኒውክሊየር ከመጠቀም ወደ ኋላ አንልም፤ ይህንንም የምንለው ለጉራ አይደለም” ብለው ዝተዋል።
ሩሲያ የዩክሬን ደቡባዊ እና ምሥራቃዊ አውራጃዎችን መጠቅለል ትፈልጋለች።
አሁን እነዚህን አካባቢዎችን በእጇ አስገብታለች።
በተቻኮለ ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔ እያደረገች ነው።
ከሩሲያ ጋር እንሆናለን የሚል ሕዝበ ውሳኔ በማስደረግ ሕጋዊ የግዛቷ አካል ለማድረግ እየሞከረች ነው።
ይሁን እንጂ ሩሲያ አሁን በሚደረጉ ውጊያዎች መሬት ላይ ሽንፈት እያጋጠማት ነው።
ይህ ሽንፈት በዚሁ ከቀጠለ ፑቲን ምዕራባዊያንን ለማስፈራራት ታክቲካል የኒውክሊየር ጦር መሣሪያዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ ይላል የአሜሪካ የስለላ መሥሪያ ቤት።
ይህን ማድረጋቸው ደግሞ የማያባራውን ጦርነት ወደ ሌላ ምዕራፍ ሊያሸጋግረው ይችላል።
ፑቲን እነዚህን አነስተኛ የኒውክሊየር አረሮችን ሊያስወነጭፉ የሚችሉት በተለይ ጦራቸው አሳፋሪ ሽንፈት ከገጠመው ነው።
ጀምስ አክተን የተባሉ የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ባለሙያ፣ “ለጊዜው እዚያ ነጥብ ላይ አልደረስንም፤ ነገር ግን በዩክሬን የጦር ሜዳ ላይ ፑቲን ትንንሽ የኒውክሊየር አረሮች እንዲተኮሱ ሊያዙ ይችላሉ” ይላሉ።
በእርሳቸው አባባል ይህን የሚያደርጉት ምዕራቡ እንዲሸበርና የባሰ እንዳይመጣ ብሎ ፍርሃት ውስጥ ገብቶ ለፑቲ ፍላጎት እንዲያጎበድድ ለማድረግ ነው።

አሜሪካ ምን ልታደርግ ትችላለች?
ጆ ባይደን ከወዲሁ ለፑቲን ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ለአሜሪካው ሲቢሲ ቲቪ ባይደን በቅርብ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ፑቲን ይህን ከደፈሩ ጦርነቱ ሌላ መልክ ይይዛል ብለዋል።
ኔቶና አሜሪካ ለዚህ ምላሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ ነው።
ነገሮች የበለጠ እንዳይከፉ ለማድረግ መሞከራቸው የማይቀር ቢሆንም፣ ነገር ግን ለፑቲን ቀይ መስመር ማለፋቸውን ማሳየትም ይፈልጋሉ።
ያን እንዴት እንደሚያደርጉ ግን ግልጽ አይደለም። ምክንያቱም መልሰው ይህንኑ መሣሪያ ከተጠቀሙ ነገሩ እየከፋ ሊመጣ ይችላልና ነው።
ይልቅ ከምዕራቡ ይልቅ ሩሲያ ግልገል ኒውክሊየር እንዳታስወነጭፍ የምታስቆማት አንድ አገር አለች፤ ቻይና።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ሩሲያ በቻይና ላይ በብዙ መልኩ ጥገኛ የሆነች አገር ናት።
ቻይና የኒውክሊየር ታጣቂ አገሮች ይህን መሣሪያ ቀድመው እንዲጠቀሙ አትሻም።
ፑቲን ይህን ካደረጉ ግን እጅግ የሚፈልጓትን ቁልፍ ወዳጅ አገር ማስቀየም ይሆንባቸዋል።













