የአፍሪካ ቡናን እያስተዋወቀ ስለ ሰው ልጆች መብት የሚታገለው ካፌ

የፎቶው ባለመብት, Denver 7
በአሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት ከተማ ዴንቨር በሚገኝ ጎዳና ላይ፣ በአትክልቶች የተከበበች የአንዲት ኢትዮጵያዊት የኤስፕሬሶ ባር አለች።
የካፌዋ አንዱ ግድግዳ በአትክልቶች የተሸፈነ ሲሆን፤ አንደኛው ግድግዳ ደግሞ በተለያዩ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ያጌጠ ነው።
ሌላኛው የካፌው ግድግዳ ማንኛውም ወደ ከተማዋ የሚመጣና ካፌውን የሚጎበኝ የሥነ ጥበብ ባለሙያ ሥራዎቹን የሚሰቅልበት በየወሩ የሚቀያየር ‘wall of Artists’ የተሰኘ ግድግዳ አለ።
የመጨረሻው ክፍል፤ ከአፍሪካ የሚመጡ የተለያዩ የቡና ዓይነቶች ተሰርቶ የሚቀርብበት ኤስፕሬሶ ባር ነው።
በእርግጥ በዊትየር ካፌ (Whittier Cafe)፣ ጣፈጭ ቡና ነው የሚቀርበው፤ ሆኖም ካፌ ውስጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች በአሜሪካን እና ሌሎች አገራት የሚያጋጥሙ ችግሮች ምክንያት በማድረግ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
አልፎ አልፎ በአገሪቷ የሚያስደነግጡ ክስተቶች - ለምሳሌ የጥቁር አሜሪካውያን ግድያ ሲያጋጥም በርካታ የዴንቨር ነዋሪዎች የተለያዩ መፈክሮች ይዘው ወደ ካፌዋ ይመጣሉ። በዚያው ከተማዋ መሃል ወደሚካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ይቀላቀላሉ።
ሲመለሱ፤ ይዘዋቸው የወጡትን መፈክሮች ካፌው ውስጥ ትተው ነው የሚሄዱት፤ የዊትየር ካፌ ባለቤት ምልዕቲ ብርሃነመስቀል ደግሞ እነዚህን መፈክሮች መጸዳጃ ቤት ውስጥ ታስቀምጣቸው እንደነበረ ትናገራለች።
ከጊዜ በኋላ፣ የንጽህና ቤቱ ግድግዳም በእነዚህ በመቶዎች በሚቆጠሩ መፈክሮች ሞልቶ፤ በየቀኑ ወደ ተቃውሞ እየተገባ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ መፈክሮች ይነበባሉ።
በዚህ ምክንያት የዊትየር ካፌ ልዩ ባህሪ እና ሁኔታን የታዘቡ ሰዎች ‘የአክቲቪስቶች ካፌ’ የሚል ቅጽል ስም ሰጥተውታል።
ሌላው አሁን ወደ ተለያዩ የመዝናኛ ቦታዎች ስንሄድ ሰዎች አንድ ጠረጴዛ ላይ ቢቀመጡም ስልኮቻቸው ላይ ብዙ ሰዓታት ሲያሳልፉ ይስተዋላል።
እዚች ካፌ ውስጥ ግን ሰዎች ለመወያየት፣ ለመነጋገር ነው የሚመጡት። ለዚህም ምክንያት የሆነው አንዱ ነገር ካፌ ውስጥ የሚገኙ ትናንሽ ወንበሮች ደንበኞች ሃሳብ እንዲቀያየሩ እንዲችሉ ተደርገው የተዘጋጁ መሆናቸው ነው።
ሰዎች በማንኛውም አጋጣሚ መነጋገር፣ መከራከር እና ሃሳብ መቀያየር አለባቸው ትላለች ምልዕቲ።
ዊትየር ካፌ፤ በዴንቨር ብቸኛ የአፍሪካ ኤስፕሬሶ ባር ሆና ለአስርት ዓመታት ዘልቃለች።
የካፌው ባለቤት ምልዕቲ “ቡና ብቻ ሳይሆን ተሞክሮ፣ ንግግሮች እና ግንኙነቶች ጭምር ነው የምሸጠው” ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።
እሁድ ከሰዓት ካፌው ከሌላው ቀን በተለየ መልኩ በርካታ ሰዎች ይመጣሉ፤ ለሁለት ሰዓታት ደግሞ አንድ የመወያያ ርዕስ ተመርጦ ውይይት ይካሄዳል።
“በዚህ አጋጣሚ የምንሰባሰብ ሰዎች እርስ በእርሳችን አንተዋወቅም፤ ግን ይሄንን አጋጣሚ ብቻ ፈልጎ የሚመጣ ሰው ብዙ ነው። አፍ አውጥተን ሰው ያስፈልገኛል አንልም እንጂ የሆነ ነገር እየጎደለን እንደሆነ ገብቶናል። ስለዚህ ደንበኞች ወደ እኛ ሲመጡ ንግግርም ፈልገው ነው የሚመጡት። ውይይት እና ማኅበራዊ ግንኙነቶች ለማበረታታት ነው ጥረት የምናደርገው” ትላለች ምልዕቲ።
ዊትየር ካፌ ላለፉት ዓመታት የማኅበራዊ ፍትህ ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል የምትለው ምልዕቲ፤ ሆን ብዬ የማኅበራዊ ፍትህ ካፌ እንዲሆን ግን አላደረግኩትም ስትል ትናገራለች።
“ሆን ብዬ ያደረግኩት አይደለም፤ ሳስበው ግን ቤተሰቦቼ እድሜያቸውን በሙሉ ለፍትህ ሲታገሉ ነበር። ለምሳሌ አባቴ ከደርግ ጋር በተደረገው ትግል አግዟል፤ በዚህ ምክንያት ነው ወደ ሱዳን የተሰደደው።
“የፖለቲካ ጥገኝነት እንዲጠይቅ ምክንያት የሆነውም ትግሉ ነው። ወደ አሜሪካ ከመጣን በኋላም ወላጆቼ አገር ቤት ያለውን ነገር ለመርዳት ጥረት ያደርጉ ነበር። ስለዚህ ለራስህ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለሌላም መታገል አለብህ፣ ፍትህ መፈለግ አለብህ የሚለው ነገር የማንነታችን አካል ነው።”
ካፌው ከኬንያ፣ ከሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ኢትዮጵያ የሚመጣ ቡና፤ ከደቡብ አፍሪካና ሞሮኮ የሚመጡ የሻይ ዓይነቶች በማቅረብ ሰዎች በቀን ተቀን ውሏቸው የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውበት ቀለል ባለ መልኩ እንዲመለከቱ ጥረት ያደርጋል።

የፎቶው ባለመብት, Millete
‘የሁላችንም ቀን በአፍሪካ ነው የሚጀምረው’
ምልዕቲ ዊትየር ካፌን ከመክፈቷ በፊት ለ10 ዓመታት ጋዜጠኛ ሆና በተለያዩ የአሜሪካ አካባቢዎች ሠርታለች።
ለ‘ስክሪፕስ ሃወርድ ኒውስፔፐርስ ግሩፕ’ ጨምሮ ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት በመሥራት በላይቤሪያ፣ ኢትዮጵያ እና ሌሎች አገራት በተካሄዱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎች፣ የጤና ጉዳዮች እና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮችን ዘግባለች።
በሂደት በአሜሪካ በርካታ ሰዎች ስለአፍሪካ ሲያወሩ የሚያነሷቸው እንደ ጦርነት፣ ረሃብ፣ ስደት . . . ያሉ የአህጉሪቱ መጥፎ ገጽታዎች መሆናቸው ዊትየር ካፌ ለመክፈት ከገፏፏት ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ታነሳለች።
ነገር ግን “በየቀኑ፣ በአሜሪካ ውስጥ ቡና የሚወድ ወይም አብዛኛው የዓለም ሰዎች ቀናቸውን በአፍሪካ ነው የሚጀምረው። ቡና የሚጠጡ ሰዎች በትንሹ ቀናቸውን የሚጀምሩት በአፍሪካ ገጸበረከቶች ነው። ስለዚህ ቡና ከየት ነው የሚመጣው ላስተምራቸው ፈለግኩኝ፤ የምትወዱት ነገር ከእኛ የመጣ ነው ልላቸው ፈለግኩ” ትላለች።
በተጨማሪም፣ ካፌው በአገሪቷ ውስጥ ያሉ እንደ ዘረኝነት፣ ኢ-ፍትሐዊነት ያሉ በርካታ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመታገል የሚደረጉ ተቃውሞዎችን በማገዝ ለማኅበራዊ ፍትህ የሚያገለግል ካፌ ነው የምትለው ምልዕቲ፤ ካፌው ለትምህርት ጉዳዮች፣ ለ‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ እንቅስቃሴ፣ የሴቶች መብቶች ለመሳሰሉት ጉዳዮች እንደሚያግዝ ገልጻለች።
“በአሜሪካ ውስጥ ዘረኝነት በነበረበት ጊዜ፤ አፍሪካ-አሜሪካውያን በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ እንዲኖሩ ነበር የሚፈቀደው። እኛ ያለንበት አካባቢም አንዱ ነበር። ሁሉም ሱቆች፣ ዶክተሮች . . . ጥቁር ነበሩ።
“ከዚያም ማኅበረሰቡ ሲዋሃድ ግን አሁን በብዛት ነጮች ናቸው የሚኖሩበት። በጊዜው የነበረው ኢ-ፍትሃዊነት ግልጽ ስለሆነ ደንበኞቻችን ምን እንዳለፈ ይገነዘባሉ፤ ስለዚህ ማኅበረሰቡ ያለፈውን ማረም ይፈልጋል፤ ለትግራይ እና ለኢትዮጵያ የማልመው ነገርም ይህንኑ ነው።”
አብዛኞቹ ካፌው ውስጥ የሚካሄዱ ንግግሮች ባለፈው የአገሪቷ ታሪክ የተፈጸሙ ስህተቶች የፈጠሯቸው ችግሮችን በማረም ረገድ የእርስ በርስ ሚና ምን መሆን እንዳለበት የሚያተኩሩ ናቸው። ካፌው አማራጭ ሃሳቦችን ለማየት የሚያመች ቦታ በመሆን ችግሮችን ለመፍታት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል የሚል እምነት አላት።
“በአገራችንም ብዙ ግፎች ይሠራሉ፤ ግን ይህንን ለማረም የሚደረግ ጥረት የለም፤ ቢያንስ ምንም ዓይነት ውይይት የለም። ‘እንደ ሕዝብ፣ እንደ አገር ስህተት ሰርተናል። እንዴት እናስተካክለው?’ የሚል ንግግር ቢጀመር ረዥም ርቀት በተጓዝን ነበር። ሆኖም ምንም እንዳልተደረገ ለማስመሰል እንሞክራለን፤ የሆነውን ሆኗል እና እንለፈው ይባላል። ይህ ግን ስህተት ነው፤ መነጋገር መቻል አለብን።
“በአሜሪካ ከማደንቃቸው ነገሮች አንዱ ይህ ነው። ብዙ ኢ-ፍትሐዊነት የተፈፀመባት አገር ናት - አብዛኛው በነጮች። ነገር ግን ይህንን ለማስተካከል ፈቃደኞች ናቸው። ከዚህ አንፃር ያለንበት መንደር እና ካፌያችን በጣም ደስ የሚል አካባቢ ነው” ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Millete
ጉዞ ወደ ሱዳን
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውም ጦርነት ተከትሎ ዊትየር ካፌ ጦርነቱን በመቃወም የኢትዮጵያ ቡና ማቅረብ አቁሞ ቆይቷል።
ምልዕቲ በጦርነቱ ወቅት፤ ካፌዋ የአክቲቪዝም ሥራዎች ሲሠራ እሷ የጋዜጠኝነት ሥራው ለመሥራት መጀመሪያ ወደ ሱዳን አቀናች።
“በሠለጠነ ዓለም ሰዎች ስለምን ጾታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል? ህጻናት በምን ምክንያት ይጠቃሉ? በዚህ ምክንያት ነበር ጊዜ እና ገንዘቤን መስዋዕት አድርጌ ለምንድን ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረስነው፣ ከዚህ በምን መንገድ መውጣት እንችላለን? በሚሉ ጉዳዮች ሰዎችን መጠየቅ፣ ሴናተሮች ማስረዳት ጀመርኩኝ” በማለት ታስረዳለች።
በአገሪቷ በ20 እና 30 ዓመታት ውስጥ የሚደጋገመው የእርስ በእርስ ጦርነት እና ግጭት መቆም እንዳለበት ትናገራለች።
“የተከሰተውን ነገር በሙሉ እንረሳዋለን የሚል ስጋት አለኝ። ያ ሁሉ ከተረሳ ግን ወደ ነበርንበት ነው የምንመለሰው፤ ከ30 ዓመታት በኋም ደግሞ ልጄ ወደ ሱዳን ልትመጣ ነው ማለት ነው። እኔ ይህ እንዲሆን አልፈልግም፤ ሁሌም ደግመን ወደዚህ እንመለስ ይሆን ወይ የሚል ያሰጋኛል።”
አሁን ላይ በትግራይ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በመቆሙ ካፌዋ በኢትዮጵያ ቡና ላይ የነበረውን እቀባ አንስቷል።
ምልዕቲ በሱዳን ተወልዳ በኮላሮዶ ግዛት ነው ያደረገችው። 17 ዓመት ሲሞላት ወላጆችዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትግራይ ይዘዋት መምጣታቸውን ታስታውሳለች።
“ወላጆቼ አገራቸው የሚወዱና የሚናፍቁ ሰዎች ነበሩ፤ ልጅ ሆኜ የሚያወሩት በሙሉ አእምሮዬ ላይ ተቀርጾ ስላደግኩኝ ወደ ትግራይ መጥቼ ብዙ ቤተሰቦች ሳገኝ፤ ማን ነኝ? ከየት ነው የመጣሁት? የሚለው ገባኝ። የሕብረተሰቡን ባህል እና ፍቅር ባየሁ ጊዜ ከትግራይ ጋር ፍቅር ይዞኛል አልኩ” ስትል የልጅነት ትውስታዋ ታነሳለች።
በትግራይ በተካሄደው ጦርነት 14 የቤተሰብ አባላት ማጣትዋን ገልጻለች።
አሁን ሕይወት “እጅግ ስሱ ሆኜ ነው የማያት፤ በቂ ጊዜ የለኝም የሚል ስጋት ስላለኝ ለሁሉም ነገር ጊዜ ሳይደርስብኝ ትክክለኛውን ነገር ለመሥራት ነው የምሯሯጠው” ትላለች።
በውጪ አገራት የሚገኙ የዲያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ከጦርነቱ በኋላ የተፈጠሩ በርካታ የውስጥ ችግሮችን ለመፍታት ገንቢ ሚና እንዲኖራቸው ደግሞ ትማጸናለች።
“ሕዝቡን በማንቃት ማገዝ አለብን፤ የምንፈልገውን መንግሥት ማግኘት የምንችለው በዚህ መንገድ ነው። በዓለም ላይ መሪ የሆኑ፣ ቢዝነሶች እና ሌሎች ነገሮችን የሚያስተዳድሩ፣ ትውልድ የሚገነቡ ብዙ ሴቶች እንዳሉ እናውቃለን።
“ነገር ግን በአገራችን በተለይ በትግራይ፣ ሥልጣን ላይ የሉም። ለምን ብለን ስንጠይቅ መልሱ የሉም፣ አይፈልጉም የሚል ነው። ይህ ለእኔ ቀልድ ነው። ስላላየናቸው ብቻ የሉም ማለት አይደለም። አሉ፤ ይህንን ክፍተት ለማጥበብ ነው መሥራት ያለብን” ስትል ተናግራለች።
ከሁሉም በላይ ግን አሁን “ለትግራይ የምፈልገው ደስታ እና ሃሴት ነው፤ ሰዎች ስለ ምግብ፣ ደኅንነታቸው ወይም የሃብት እጥረት እንዲጨነቁ አልፈልግም። ምኞቴ ደስታ እና ደስታ ብቻ ነው” ትላለች ምልዕቲ።

የፎቶው ባለመብት, Millete
ስለ ምግብ አብሳዮች እና የምግብ ምርጫቸው
ምልዕቲ የሦስት ልጆች እናት፣ የበርካታ ቢዝነሶች እና ፕሮጀክቶች አስተዳዳሪ እንዲሁም በኮሎራዶ የትግራይ ተወላጆች ማኅበር ፕሬዝዳንት ናት።
የሰዎችን ታሪክ ማዳመጥ እና መጻፍ እንደምትወድ ትናገራለች፤ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አገራት ያሉ የምግብ ባለሙያዎችን (በዋነኛነት በሰሜን አሜሪካ) ቃለ መጠይቅ በማድረግ የምግብ ዝግጅት መጽሐፍ በማሰናዳት ላይ ትገኛለች።
ይህም ሰዎች ለምግብ ያላቸውን አሉታዊ አመለካከት ለማስወገድ እና ከምግብ ጋር አዎንታዊ ግንኙነት ለማዳበር እንዲችሉ ትኩረት ያደረገ ነው የምትለው ምልእቲ፤ የምግብ አዘገጃጀት መመሪያው የሼፎችን ተወዳጅ ምግብ በመለየት ከእሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እና ሌሎችንም እንደሚመረምር ገልጻለች።
መጽሐፉ ስለ “ምግብ እና አብዮት” ነው በማለት በተለይ በትግራይ ውስጥ በምግብ ዙሪያ የሚነገሩ ‘የተሳሳቱ አመለካከቶች’ አላቸው የምትላቸው ጉዳዮችን ለመቀየር ያለመ ነው ስትል ትናገራለች።
በዝግጅት ላይ በሚገኘው መጽሐፏ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ የምግብ አዘገጃጀቶች ከእናቷ የመጡ እንደሆኑ የምትናገረው ምልዕቲ፣ ግማሹ የመጽሐፉ ክፍል ደግሞ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው የምግብ ማብሰል ባለሙያዎች እና ታሪካቸውን የሚዳስስ ነው።
“ይህ መጽሐፍ ስለ ምግብ ያለን አመለካከት ለመቀየር እንዲሁም እዚህ እንዴት እንደ ደረስን እንድንረዳ ያግዘናል። በባህላችን ለምን እንዲህ እንላለን? ምግብን የጦር መሣሪያ ከማድረግ ጋር ያለው ግኑኝነት ምንድን ነው? የሚለውን ይዳስሳል” ብላለች።












