በፈረንሳይ በአፍ ጭንብል ውዝግብ የተነሳ የአውቶብስ ሹፌሩን ደብድበው የገደሉት ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኮቪድ-19 ወረረሽኝ ወቅት የአፍ መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ) በትክክል ባለማድረጋቸው ከአውቶብስ እንዲወርዱ የጠየቀውን ሹፌር ደብድበው የገደሉት ሁለት ግለሰቦች የ15 ዓመት እና የ13 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው።
ሹፌሩ ፊሊፕ ሞንጊሎት በድብደባ ህይወቱ ያለፈው በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ ባዮኔ በተሰኘችው ከተማ በአውሮፓውያኑ 2020 ነው።
ዋይሴም ማናይ እና ማክስሜ ጉየንኖች የተባሉት ግለሰቦች ሹፌሩን በደበደቡት ወቅት ከባድ የጭንቅላት አደጋ የደረሰበት ሲሆን እዚያውም ትተውት ሄደዋል ተብሏል።
ሐሙስ ዕለት የዋለው ችሎትም ዋይሴምን 15 ዓመት እስር እንዲሁም ማክስሜን 13 ዓመት እስር አከናንቧቸዋል።
የ25 ዓመት እድሜ ያላቸው ሁለቱ ግለሰቦች ሆን ብለው ጥቃት ፈጸውመው ለግድያ ዳርገውታል በሚልም ነው ብያኔው የተላለፈባቸው።
ሆኖም ፍርድ ቤቱ ለመግደል አስበው ነው ጥቃቱን የፈጸሙት በሚለው ጥፋተኛ ሆነው አላገኛቸውም።
ሹፌሩ በአውቶብሱ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ የተወሰኑ ወንዶችን ቲኬታቸውን እንዲያሳዩ እና የአፍ መሸፈኛ ጭንብላቸውን እንዲያስተካክሉ ከጠየቀም በኋላ ድብደባው እንደተፈጸመበት አቃቤ ህግ አስታውቋል ።
ጥቃቱ የተከሰተው በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 5/ 2020 የፈረንሳይ የመጀመሪያው የእንቅስቃሴ ገደብ በተነሳበት ወቅት ነው። ሆኖም በየትኞቹም የህዝብ ማመላለሻዎች ላይ የአፍ መሸፈኛ ጭንብሎችን ማጥለቅ አስገዳጅ ነበር።
ከማስክ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ውዝግብ ግለሰቦቹ በእርግጫ እንዲሁም በጡጫ ሲደበድቡት የወደቀ ሲሆን ጭንቅላቱም አስፓልት ላይ አርፏል።
የሶስት ልጆች አባት የሆነው የ59 አመቱ አሽከርካሪ ከአምስት ቀናት ሆስፒታል ቆይታ በኋላ ህይወቱ አልፏል።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በፓኡ የሚገኘውን ፍርድ ቤት ግለሰቦቹ በ15 ዓመት እስራት እንዲቀጡም ጠይቋል።
ባለቤቷን በዚህ ድብደባ ያጣችው ቬሮኒኬ ሞንጉይሎት ግለሰቦቹ ከፍተኛ የሚባለውን የ30 ዓመት እስራት ባለመቀጣታቸው መናደዷን ገልጻለች።
“ሰዎችን የሚያስተምር ፍትህን ነው የጠየቅነው። ምንም እንኳን እስራት ቢፈረድባቸውም ይህንን ፍትህ አግኝተናል ማለት አንችልም። እስር ቤት መበስበስ ነበረባቸው” ስትልም ከፍርድ ቤቱ እየወጣች በነበረችበት ወቅት ተናግራለች።
“ባለቤቴን፣ የልጆቼን አባት ገደሉት። እሱ ከሞተበት ዕለት ጀምሮ የኔም ህይወት አክትሟል” ብላለች።
የሹፌሩ ሞት በመላው ፈረንሳይ ድንጋጤ የፈጠረ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ባዮን በተካሄደው የአደባባይ ተቃውሞ ላይ ተሳትፈዋል።












