ትውልደ ኢትዮጵያዊው የአሜሪካ ጥብቅ መረጃዎችን ለኢትዮጵያ አሳልፎ በመስጠት ተከሰሰ

የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ

ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ እና ለአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ የሚሰራ የአሜሪካ ዜጋ የሆነው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ጥብቅ ምስጢራዊ መረጃዎችን ለኢትዮጵያ አሳልፎ በመስጠት ክስ ተመሰረተበት።

አብርሃም ተክሉ ለማ የተባለው የ50 ዓመት የቨርጂኒያ ነዋሪ ከስለላ ጋር የተያያዙ ሦስት ክሶች እንደተመሰረቱበት የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ አስታውቋል።

የውጭ አገር መንግሥትን ለመርዳት የአሜሪካ ብሔራዊ መከላከያን ጥብቅ መረጃ በመሰብሰብ ወይም አሳልፎ ለመስጠት በማሴር እና በመስጠት፤ እንዲሁም ብሔራዊ የመከላከያ መረጃን ከፍቃድ ውጭ በመያዝ ክስ ቀርቦበታል።

የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ ግለሰቡ የስላለ ሥራ የሰራው በቀጥታ ለኢትዮጵያ መንግሥት ነው ባይልም አብርሃም ላይ የቀረበው የክስ ሰነድ የቤተሰብ ግንኙነት ወዳለው እና ባለፉት ዓመታት ለበርካታ ጊዜ ከተመላለሰበት አገር ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ አመላክቷል።

ኒው ዮርክ ታይምስ አብርሃም ተክሉ ለማ ከቀናት በፊት በቁጥጥር ሥር መዋሉን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲዘግብ ግለሰቡ የተያዘው ለኢትዮጵያ መንግሥት በመሰለል ተጠርጥሮ ነው ብሎ ነበር።

ለኢትዮጵያ መንግሥት ምስጢራዊ መረጃዎችን አሳልፎ ሰጥቷል በተባለው ግለሰብ ላይ የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ፣ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) እና የአገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምርመራ እያደረጉበት መሆኑ ይፋ ተደርጓል።

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ያለው ነገር የለም።

አብርሃም ተክሉ ለማ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ እንዲሁም በፍትሕ ቢሮ ማናጅመንት አናሊስት ሆኖ ሲያገለግል ነበር ተብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ግለሰቡ ይህ ኃላፊነቱ የአሜሪካን ጥብቅ መረጃ እንዲያገኝ ረድቶታል ብሏል የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ።

የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ ባቀረበው ክስ በታኅሥሣ 10/2015 ዓ.ም. እና ነሐሴ 1/2015 ዓ.ም. መካከል ባሉት ቀናት ሕግ በመተላለፍ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ጥብቅ ምስጢራዊ መረጃዎችን ገልብጦ ወስዷል።

የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ አብርሃም ተክሉ ለማ ያለ ፍቃድ የወሰደው ጥብቅ መረጃ በደፈናው ከቀጠናው ጋር የተያያዘ ነው ያለ ቢሆንም፣ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን አብርሃም ኮፒ አድርጎ የወሰደው መረጃ በኢትዮጵያ ስለሚንቀሳቀስ ታጣቂ ቡድን እንቅስቃሴ እና ስለ ማዘዣ ጣቢያዎች ነው ብለዋል።

ሲኤንኤን መረጃውን ከአብርሃም ተክሉ የሚቀበለው የኢትዮጵያ መንግሥት የደኅንነት አባል ከመንግሥት ጋር እየተዋጋ ስለሚገኝ “የታጣቂ ቡድን ወታደራዊ እንቅስቃሴ” መረጃ እንዲፈልግ ነግሮታል ብሏል።

በሲኤንኤን ዘገባ ላይ አብርሃም ተክሉ መረጃ እንዲያፈላልግ የተጠየቀው ስለየትኛው የታጣቂ ቡድን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንደሆነ የተባለ ነገር የለም።

ኤንቢሲ የተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ ደግሞ የፍርድ ቤትን ሰነዶችን ዋቢ አድርጎ በሰራው ዘገባ አብርሃም ተክሉ ደኅንነቱ በተጠበቀ መልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ ካርታዎችን፣ ምስሎችን እና የሳተላይት ምስሎችን ልኳል ብሏል።

አብርሃም ለማ ባለፉት ወራት ወደ ኢትዮጵያ ለበርካታ ጊዜ መመላለሱን እና ከደኅንነት አባሉ ጋር አዲስ አበባ በሚገኝ ሆቴል በአካል ተገናኝቶ እንደነበረ ተገልጿል።

ግለሰቡ ወደ ኢትዮጵያ በተጓዘባቸው ጊዜያት በርካታ የታተመ ሰነድ ሰጥቷል የተባለ ሲሆን ጥብቅ መረጃዎችን ከፍቃድ ውጭ መውሰድ ከጀመረ እና ወደ ኢትዮጵያ ከተመላለሰ በኋላ በተለያዩ ባንኮች ገንዘብ ገቢ አድርጓል።

የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ በግለሰቡ ላይ የቀረቡትን ክሶች ይፋ ባደረገበት መግለጫው፣ አብርሃም ሚስጢራዊ መረጃዎቹን አሳልፎ ለመስጠት ፍላጎቱን የተገለጸበት የጽሑፍ ልውውጥ አግኝቻለሁ ብሏል።

አብርሃም ከውጭ አገር ባለሥልጣን ጋር በነበረው አንድ የጽሑፍ ልውውጥ ኃላፊው “እርዳታህን የምትቀጥልበት ጊዜው አሁን ነው” ብለው ሲልኩለት አብርሃም “ተቀብያለሁ” ሲል መልሷል።

በሌላ የጽሑፍ ልውውጥ ባለስልጣኑ “ይህች ውብ አገር ሁልጊዜም አኩሪ ታሪኳን ለመጠበቅ እራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ ሰዎች አሏት። ሁሌም ትታወሳለህ . . .” ሲሉ አብርሃም ተክሉን አወድሰዋል።

አብርሃም ከቀረቡበት ክሶች መካከል ሁለቱ የሞት ቅጣት ወይም የዕድሜ ልክ እስራት የሚያስፈርዱ መሆናቸውን ፍትሕ ቢሮ ገልጿል።