የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሲጓዙበት የነበረ ሄሊኮፕተር አደጋ እንደረሰበት ተዘገበ

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ ሲጓዙበት የነበረ ሄሊኮፕተር አደጋ እንዳጋጠመው የአገሪቱ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

ዘገባው እንዳለው ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ ተሳፍረውበት የነበረው ሄሊኮፕተር ዛሬ እሁድ በአደገኛ ሁኔታ መሬት ላይ ማራፉን አመልክቷል።

የኢራን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው አደጋው ደርሷል በተባለበት ስፍራ ላይ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ እንዳለ እና የነፍስ አድን ሠራተኞች ወደ ቦታው ለመድረስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጿል።

ፕሬዝዳንቱ ኢራን ከአዘርባጀን ጋር በምትዋሰንበት አካባቢ የተገነቡ ሁለት ግድቦችን መርቀ ከከፈቱ በኋላ ወደ ሰሜን ምዕራቧ የአገሪቱ ከተማ ታብሪዝ እያመሩ እንደነበረ የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የፋርስ የዜና ወኪል ዘጋቢ እንዳለው ሄሊኮፕተሩ አርፎበታል በተባለው ስፍራ ላይ ባለው ከባድ ጭጋግ ምክንያት የነፍስ ማዳን ፍለጋ ሥራው አስቸጋሪ ሆኗል።

ሪፖርተሩ ጨምሮም አደጋው ደርሶበታል በተባለው ተራራማ እና ደናማ አካባቢ ከአምስት ሜትር ርቀት በላይ ለመመልከት አዳጋች ነው።

ሄሊኮፕተሩ ይገኝበታል የሚባለው አካባቢ ፕሬዝዳንቱ ሊጓዙባት ከነበረችው ታብሪዝ ከተማ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሆነ ተነግሯል።

ከታብሪዝ ከተማ ተወክለው የአገሪቱ ምክር ቤት አባል የሆኑት አህመድ አሊሪዛቤጊ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ የነፍስ አድን ሠራተኞች ፕሬዝዳንቱን ያሳፈረችው ሄሊኮፕተር ያለችበትን ስፍራ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነው።

የምክር ቤት እንደራሴው ጨምረውም ሄሊኮፕተሯ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት በተጨማሪ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑትን ሆሴን አሚራብዶላሂያንን አሳፍራለች።

ፕሬዝዳንቱን አጅበው የነበሩት ሌሎቹ ሁለት ሄሊኮፕተሮች በሰላም ማረፋቸውንም የምክር ቤት አባሉ ገልጸዋል።

በመንግሥት ቴሌቪዥን ላይ ከኢራኗ ቅዱስ ከተማ ማሻድ በቀረበ ቪዲዮ ላይ ምዕመናን ለፕሬዝዳንቱ ጤንነት ጸሎት ሲያደርጉ ታይተዋል።