ድንጋይ ቀብቶ ወርቅ ብሎ የሸጠው ድርጅት እና የኩባንያው ሳይንቲስት ሚስጥራዊ አሟሟት

በአውሮፓውያኑ መጋቢት 19/1997 የካናዳው ማዕድን አውጭ ኩባንያ ብሬ-ኤክስ ሚኒራልስ ዋና ጂኦሎጂስት የሆነው ሚካኤል ደ ጉዝማን ሄሊኮፕተር ተሳፍሮ ኢንዶኔዥያ ወደሚገኝ ራቅ ያለ ሥፍራ አመራ።

ወደዚህ ጥቅጥቅ ጫካ ሲጓዝ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ሥፍራው እምቅ ወርቅ የተከማቸበት ነው ሲል ይፋ ያደረገው እሱ ነው።

ነገር ግን በዚህች ጥዋት ወደ ሥፍራው ያመራው መዳረሻውን ሳያይ ቀረ።

ጉዞውን ከጀመረ ከ21 ደቂቃዎች በኋላ የሄሊኮፕተሯ የግራ በር ተከፈተ። ጉዝማንም ወደ ጥቅጥቁ ጫካ እየተንሳፈፈ ሄደ።

የማዕድን አውጭው ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጉዝማን ራሱን አጥፍቶ ነው አሉ። ይህን ያደረገው ሄፒታይተስ ቢ ስላለበት እንዲሁም ከወባ ጋር ሲታገል ስለከረመ ነው የሚል መግለጫ ሰጡ።

ከ10 ዓመታት በኋላ ካናዳዊቷ ጋዜጠኛ ሱዛን ዊልተን የደ ጉዝማንን አሟሟት መርምራ እንድትደርሰበት በካልጋሪ ሄራልድ ትዕዛዝ ተሰጣት።

"የዓለምን ግማሽ ተጉዤ ነው የሄድኩት። ከዚያን ጊዜ በኋላ ይህ ታሪክ ይኸው እየተከተለኝ ይኖራል" ትላለች።

ደ ጉዝማን የተወለደው በቫለንታይን ቀን 1956 ዓ.ም. ፊሊፒንስ ውስጥ ነው። በተለያዩ ሀገራት በአንድ ጊዜ ከሶስት በላይ ሚስቶች እንዳሉት ይነገርለት ነበር።

ካራኦኬ መጫወት ይወዳል፤ ቢራ ደግሞ ነፍሱ ነው። የራቁት ዳንስ ክለቦችን ያዘወትራል። ታድያ ይህን የሚያደርገው በወርቅ አጊጦ ነው።

ጉዝማን በጂኦሎጂ መስክ ብዙ ዓመት የሠራ ባለሙያ ሲሆን ኢንዶኔዥያ ሄዶ ሕይወቱን እንደሚቀይር አምኗል።

በ1990ዎቹ ኢንዶኔዥያ እምቅ የወርቅ ሀብት ያላት እና በርካቶች ተፈጥሯዊ ማዕድን አውጥተው ራሳቸውን ለመቀየር የሚጓዙባት ሀገር ነበረች።

ጆን ፌልደርሆፍ የተሰኘው የደች ዜጋ ቡሳንግ በተሰኘችው የኢንዶኔዥያ ገጠር እምቅ ወርቅ እንዳለ አምኖ ወደ ሥፍራው ተጓዘ። ነገር ግን ወርቁን ቆፍሮ ለማውጣት ብር ያስፈልገው ነበር።

በ1993 ጆን እና የብሬ-ኤክስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዴቪድ ዋልሽ ስምምነት ፈፀሙ። በስምምነቱ መሠረት ዋልሽ ኢንቨስተሮችን አምጥቶ የተቀበረውን ማዕድን ሊያወጣ ቃል ገባ።

ጆን መሬት ያለውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ነበር ሥራው። ይህ ለማድረግ ደግሞ ጂኦሎጂስቱ እና ጓደኛው ደ ጉዝማን ወሳኝ ሰው ነበር።

ነገር ግን ጆን፣ ጉዝማን እና የሥራ አጋሮቻቸው እስከ መስከረም 18/1993 ድረስ ባለው ጊዜ የሙከራ ቁፋሮ አካሂደው እውን ሥፍራው ወርቅ አዝሏል የሚለውን ጥያቄ የመመለስ ግዴታ ነበረባቸው።

እስከዚህ ጊዜ ድረስ ወርቅ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ካልቻሉ የኢንዶኔዥያ መንግሥት የሰጣቸው ፈቃድ ከጥቅም ውጭ ይሆናል።

ይህ ጊዜ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ቢቀሩትም፤ ሁለት የቁፋሮ ሥፍራዎች ቢመሠረቱም ሰዎቹ ወርቅ የሚባል ነገር ማግኘት አልቻሉም።

ይሄኔ ነው ጉዝማን በሕልሜ ባየሁት መሠረት ወርቅ ያለበት ትክክለኛ ሥፍራ ሄደን መቆፈር አለብን ሲል ለዋልሽ የነገረው ትላለች ጋዜጠኛዋ ሱዛን።

የቁፋሮ ቡድኑ ልክ ጉዝማን በሕልሜ ታይቶኛል ባለው መሠረት የተላኩበት ሥፍራ ሄደው ቁፋሮዋቸውን ጀመሩ። ትንሽ ዘለቅ እንዳሉ የሚያብረቀርቅ ድንጋይ ይታያቸው ጀመር።

አራተኛ ቁፋሮ ሲካሄድ ሌላ ወርቅ ብቅ አለ።

ይህ ታሪክ ከዓለማችን የማጭበርበር ታሪኮች አንዱ ነው። ብዙዎች በዚህ ማጭበርበር ምክንያት ሕይወታቸውን ተመሰቃቅሏል። እውን የተፈጠረው ነገር ምንድነው?

ለሚቀጥሉ ሶስት የቁፋሮ ቡድኑ ወርቅ ማውጣቱን ተያያዘው። እንደተገመተው ሥፍራው እምቅ ወርቅ አዝሏል። የኢንቨስተሮችም ቁጥር እያደገ መጣ።

የብሬ-ኤክስ ኩባንያ የአክሲዮን ገበያ እየደረ መጣ። የኩባንያው የአክሲዮን ዋጋ ከ20 ሳንቲም ወደ 280 የካናዳ ዶላር አደገ። በወቅቱ ኩባንያው ቢሸጥ 6 ቢሊዮን የካናዳ ዶላር ያወጣል ተባለለት።

በርካታ ካናዳዊያን ያጠራቀሙትን በሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮች እያወጡ ኢንቨስት ማድረግ ጀመሩ።

ነገር ግን ጊዜው እየገፋ ሲመጣ የወርቁ ብርቅርቅነት መደብዘዝ ያዘ።

በ1997 መባቻ የወቅቱ የኢንዶኔዥያ ፕሬዝደንት የነበሩት ሱሃርቶ እንደ ብሬ-ኤክስ ያለ አነስተኛ ኩባንያ ሥፍራውን ተቆጣጥሮ ወርቅ እየሸጠ ትርፉን ማፈስ የለበትም አሉ። የፕሬዝደንት ዕቅድ ኩባንያው ከመንግሥት ጋር ሆኖ የተሻለና ዘመናዊ ማዕድን አውጭ ኩባንያ መጥቶ ወርቅ እንዲቆፍር ነበር።

ይሄኔ ነው ፍሪፖርት-ማክረሞራን የተሰኘው የአሜሪካው ኩባንያ ስምምነት ፈፅሞ የመጣው።

ይህ ኩባንያ ውዱን ብርቅርቅ ድንጋይ መቆፈር ከመጀመሩ በፊት የራሱን ፍተሻ ለማድረግ ወሰነ። የኩባንያው ጂኦሎጂስቶች በቡሳንግ ግዛት ሁለት ጉድጓዶች እንዲቆፍሩ ተላኩ። የሚቆፈሩት ጉድጓዶች እዚያው ወርቅ ተገኘበት ከተባለት ሥፍራ አቅራቢያ ናቸው።

ይህ በማዕድን ማውጣት መስክ የተለመደ ሂደት ቢሆንም ብሬ-ኤክስ ኩባንያ ግን ይህን አላደረገም።

የአሜሪካው ኩባንያ ጂኦሎጂስቶች ከሥፍራው ያገኙት ድንጋይ ወደ ቤተ-ሙከራ ቢልኩም ውጤት ወርቅ የሚል የሚያሳይ አልሆነም።

ዋልሽ እና ጆን ስለሆነው ነገር ተነገራቸው። ይሄኔ ነው ለስብሰባ ቶሮንቶ የሚገኘው ጉዝማን ወደ ቡሳንግ በፍጥነት መጥቶ ሁኔታውን እንዲያስረዳ የተጠራው።

ጉዝማን ከካናዳ ሲንጋፖር አቀና። ሚስቱ ጂኒ ሲንጋፖር ነው የምትኖረው። አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ልጅ አላቸው።

ደ ጉዝማን የመጨረሻዎቹን ሰዓታቱን ያሳለፈው ባሊከፓፓን በተሰኘችው ከቡሳንግ 161 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ሥፍራ ነው። እዚያ የብሬ-ኤክስ ሚኒራልስ ሠራተኛ የሆነው ሩዲ ቬጋ ይገኛል።

ቬጋ የኩባንያው የፈሊፒንስ ክንፍ አባል ሲሆን የፍሪፖርት-ማክሞራን ሰዎችን ለማግኘት ከጉዝማን ጋር ሄሊኮፕተር ተሳፍሮ ለመሄድ ጓዙን እየሸከፈ ነበር።

ቬጋ ከክስተቱ በኋላ ለኢንዶኔዥያ ፖሊስ በሰጠው ቃል መሠረት ከጉዝማን ጋር ወደ ካራኦኬ ባር አቅንተዋል። ነገር ግን ወደ ሆቴላቸውን ሲመለሱ ጉዝማን ራሱን ለማጥፋት ሞክራል ይላል የቬጋ ቃለ-ምልልስ።

በቀጣዩ ንጋት ደ ጉዝማን እና ቬጋ ሄሊኮፕተር ተሳፍረው ወደ ሳማሪንዳ ከተማ ተጓዙ። ሳማሪንዳ ለቡሳንግ ቅርብ የሆነች ከተማ ናት።

ከዚህች ከተማ ነው ጉዝማን ሄሊኪፕተር ተሳፍሮ ወደ ቡሳንግ ያቀናው። ቬጋ ግን አልተሳፈረም።

ነገር ግን ሄሊኮፕተሯ ላይ ሌሎች ሁለት ሰዎች ከጉዝማን ጋር ነበሩ። የጥገና ባለሙያ እና አብራሪው። አብራሪው የኢንዶኔዥያ አየር ኃይል አባል እንጂ ከዚህ ቀደም ወደ ቡሳንግ የሚጓዘው አብራሪ አልነበረም።

ሄሊኮፕተሯ ሳማሪንዳ ማረፏ የተለመደ አይደለም። ለወትሮው ከባሊክፓፓን ወደ ቡሳንግ ቀጥታ ነበር የምትበረው።

ስለተፈጠረው ነገር ቃሉን የሰጠው አብራሪ ስለሁኔታው ከዚያ በኋላ ተናግሮ አያውቅም ትላለች ሱዛን። በተፈጠረው ነገር ላይ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌለው እና ጉዝማን ከሄሊኮፕተሯ ሲጠፋ እንዳልተመለከተ ነው የሚያስረዳው።

መጋቢት 19/1997 ጥዋት 4፡30 ደ ጉዝማን ላይመለስ አሸለበ።

ሄሊኮፕተሩ ውስጥ በእጅ የተፃፈ ደብዳቤ ተገኘ። ሬሳው ደግሞ ከአራት ቀናት ፍለጋ በኋላ ጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ ተገኘ።

ደ ጉዝማን ከሞተ ከስድስት ሳምንታት በኋላ የቡሳንግ የወርቅ ሕልም ቅዠት ሆነ። ኢንቨስተሮች ሜዳ ላይ ቀሩ። የብሬ-ኤክስ ሚኔራልስ ዋጋ ከ6 ቢሊዮን ወደ ምንም ዝቅ አለ።

ገለልተኛ ተቋም ያዋቀረው ዘገባ እንደሚያሳየው በቡሳንግ ምንም ዓይነት ወርቅ አልነበረም። ከ1995 እስከ 97 የወጡ "ወርቆች" ወርቅ ሳይሆኑ 'ሳልቲንግ' በሚባል መንገድ ወርቅ እንዲመስሉ የተደረጉ ድንጋዮች ሆነው ተገኙ።

ይህ ማጭበርበር 30 ዓመታት ቢሞልቱም ማንም ለጉዳዩ ተጠያቂ ሆኖ አልተገኘም።

ዋልሽ በ1998 እስኪሞት ድረስ ስለጉዳዩ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ነው የሚናገረው። በ2007 የካናዳ ፍርድ ቤት ደቹ ጀኦሎጂስት ጆን ስለሁኔታው የሚያውቀው ነገር የለም ሲል በነፃ አሰናበተው። ጆን በ2019 ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

እውን ደ ጉዝማን የዚህ ማጭበርበር ሂደት ጉድ እንዳይወጣ በሚል ራሱን አጥፍቶ ይሆን? ጋዜጠኛዋ ዙሳን ከመሞቱ በፊት ፃፈው የተባለው ደብዳቤ ብዙ ጥያቄ ያጭራል ትላለች።

ደብዳቤው ላይ በሽታ እንዳለበት ይናገራል። ነገር ግን ወዳጅ ዘመዶቹ ስለዚህ በሽታ ሲናገር ሰምተውት አያውቁም።

የደ ጉዝማን ቤሰተቦች የቀጠሩት የፊሊፒንስ የግል መርማሪ ቡድን ሬሳው ሲገኙ የተነሱ ፎቶዎችን መርምረው አንገቱ አካባቢ ምልክት በማየታቸው የሞተው በሰው ታንቆ ነው ሲሉ ደምድመዋል።

የተገኘውስ ሬሳ የጉዝማን ነው?

መጀመሪያ ላይ የወጡ ሪፖርቶች ሬሳው ከአራት ቀናት በላይ ጫካ ውስጥ የቆየ እንደሆነ አሳይተዋል። የጉዝማን ሚስት የሆነችው ጂኒ እንደምትለው ደግሞ ሬሳው ላይ የግለሰቡ ጥርሶች ጥቅጥቅ ብለው ይታያሉ፤ ነገር ግን ጉዝማን ሰው ሰራሽ ጥርስ ነበር የሚጠቀመው።

የጂኒ ጓደኛ የሆነው ጂኦሎጂስቱ ማንሱር ጋይገር እንደሚለው ጂኒ ባሏ ጉዝማን እንዳልሞተና ደቡብ አሜሪካ ካይመን አይላንድስ ውስጥ ተደብቆ እየኖረ እንደሆነ እንደምታምን ነግራኛለች ይላል።

ይህ ታሪክ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ያዘለ ነው። የጉዝማን ልጅ ልክ እንደአባቱ ጂኦሎጂስት ነው። እናቱ በነገረችው መሠረት አባቱ ሞቷል ብሎ አያምንም። የአባቱን ሌጋሲ ለማስቀጥል የቆረጠ ይመስላል። በትክክለኛው መንገድ።