ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤል ጦር ካቢኔ ሚኒስትር ከጦርነቱ በኋላ ለጋዛ የተዘጋጀ ዕቅድ ከሌለ ከኃላፊነት እንደሚለቁ ገለጹ
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ ለጋዛ ሰርጥ የተዘጋጀ ዕቅድ ካላወጡ ስልጣን እንደሚለቁ የጦር ካቢኔ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ ዝተዋል።
ጋንትዝ በጋዛ የሐማስ አገዛዝን ማብቃትን እና ለግዛቱ ዓለም አቀፍ ሲቪል አስተዳደር መመስረትን ጨምሮ ስድስት “ስትራቴጂካዊ ግቦችን” ለማሳካት የሚያስችለው ዕቅድ እስከ ሰኔ 8 እንዲዘጋጅ ቀነ-ገደብ አስቀምጠዋል።
“አገራዊውን ከግል ጥቅም በላይ ብታስቀምጡ እኛን የመሰሉ የትግል አጋሮች ታገኛላችሁ። ነገር ግን የአክራሪዎችን መንገድ መርጣችሁ መላውን ህዝብ ወደ ገደል ከመራችሁ ካቢኔውን ለመልቀቅ እንገደዳለን” ብለዋል።
ኔታንያሁ አስተያየቱን “ለእስራኤልን ሽንፈት ማለት ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።
አለመግባባቱ እየጨመረ የመጣው በጋዛ ሰርጥ በሁለቱም ጫፎች ላይ ውጊያ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው። የእስራኤል ወታደሮች በደቡባዊ ራፋህ ከተማ እና የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች በብዛት በሚገኙባት እና የእስራኤል ጦር ከዚህ በፊት የሐማስ ተዋጊዎች እንደሌሉ በተናገሩባት በሰሜናዊቷ የጃባሊያ ከተማ ውጊያው እየተካሄደ ነው።
ሌላኛው የጦር ካቢኔ አባል የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንትም ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እስራኤል በጋዛ የሲቪል ሆነ ወታደራዊ አገዛዝን የመቆጣጠር ዕቅድ እንደሌላት በይፋ መናገራቸው ይታወሳል።
ጋላንት ጉዳዩን ለወራት በተደጋጋሚ ቢያነሱም ምላሽ እንዳላገኙ ተናግሯል።
እሳቸውም ሆኑ ጋንትዝ በጋዛ ወታደራዊ ቁጥጥርን ማስፈን የእስራኤልን የፀጥታ ስጋት እንደሚያሳድገው ተናገረዋል። በኔታንያሁ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙት የጥምር መንግስት አባላትን ጨምሮ የቀኝ አክራሪዎች ሐማስን ለማሸነፍ ቀጣይነት ያለው ቁጥጥር አስፈላጊ ነው ሲሉ ያምናሉ።
ጋንትዝ ቅዳሜ ዕለት በቴሌቭዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር "የእስራኤል ህዝብ እርስዎን እየተከታተሉ ነው" ሲሉ መልእክታቸውን ለኔታንያሁ አስተላልፈዋል።
"ከጽዮናዊነት እና ከሳይኒዝም፤ ከአንድነት እና ከክፍፍል፤ ከኃላፊነት እና ከህግ-የለሽነት፤ ከድል እና ከአደጋ መካከል አንዱን መምረጥ አለብዎት" ብለዋል።
ካስቀመጣቸው ስድስት ስትራቴጂካዊ ግቦች መካከል በሐማስ የተያዙት ሁሉም ታጋቾችን ማስመለስ እና የተፈናቀሉ የፍልስጤም ሲቪሎች እስከ መስከረም 1 ድረስ ወደ ሰሜናዊ ጋዛ መመለሳቸው ማረጋገጥ ይገኙበታል።
በተጨማሪም እስራኤል ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላትን ግንኙነት መደበኛ በማድረግ “ከምዕራቡ ዓለም ጋር ግንኙነቱን በማሳደግ በኢራን እና በተባባሪዎቿ ላይ ጥምረት መፍጠር” አለባት ብለዋል።
ለንግግሩ ምላሽ የሰጡት ኔታንያሁ የጋንትዝን ፍላጎት ማሟላት ማለት “ጦርነቱ መፈጸም እና ለእስራኤል ሽንፈት፤ አብዛኛዎቹን ታጋቾች መተው እና ሐማስ እንዳይነካ እና የፍልስጤም መንግስት መመስረትን ያስከትላል” ብለዋል።
የእስራኤል የጦር ካቢኔ የተቋቋመው ሐማስ መስከረም 26 በእስራኤል ላይ ጥቃት በመፈጸም አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደለ እና በርካቶችን ከማረከ በኋላ ነው።
ጥቃቱን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በሐማስ ላይ ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ 35 ሺህ 386 ሰዎች መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የአገሪቱ ጦር ሃይል ዋና አዛዥ ሄርዚ ሃሌቪ በበኩላቸው ኔታንያሁ “ከጦርነቱ በኋላ” ስትራቴጂ አስፈላጊ መሆኑን አጥብቀው መግለጻቸውን የእስራኤል ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ቀደም ሲል ከሐማስ ነጻ መሆናቸው የተነገረላቸው እንደ ጃባሊያ ባሉ አካባቢዎች የእስራኤል ጦር መመለሱ ቡድኑን ለማስወገድ መንግስት በዛየው ስትራቴጂ ላይ ጥርጣሬን ፈጥሯል።
ከሐማስ ውጭ ሆነ የበላይ አካል ለማቋቋም ዲፕሎማሲያዊ ሂደት ከሌለ ጦሩ የቡድኑን ጥቃት ለመከላከል ተደጋጋሚ ዘመቻዎችን ለማድረግ ይገደዳል ሲሉ ሃሌቪ ተከራክረዋል።
ጋንትዝ ለወደፊቱ ተለዋጭ መንግስት መሠረት የሚጥል እና በጋዛ የሲቪል ጉዳዮችን በበላይነት የሚያስተዳድር የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የአረብ እና የፍልስጤም አስተዳደርን ሃሳብ አቅርበዋል።
እስከዚያው ድረስ እስራኤል "የደህንነት ቁጥጥር" ደረጃዋን መጠበቅ እንደምትችልም አክለዋል።
የእስራኤል ጦር በጃባሊያ ከፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች ጋር ውጊያ ላይ ይገኛል። የፍልስጤም የህክምና ባለሙያዎች እንደተናገሩት ከሆነ በአንዱ የእስራኤል ጥቃት 15 ሰዎች ተገድለዋል።
ሐማስ በበኩሉ እስራኤል በጃባሊያ ላይ ባካሄደችው “አሰቃቂ ወረራ” በደርዘን የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎችን መግደላቸውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል ብሏል።
ቅዳሜ ማምሻው የታጠቁ ቡድኖች ወደ ግዛቷ ሮኬቶችን መተኮሳቸውን በመግለጽ እስራኤል ከሰሜን ጋዛ አንዳንድ ክፍሎች እንዲለቁ ትዕዛዝ አውጥታለች።
የሐማስን የመጨረሻ ምሽግ ለማጥቃት በሚል ባለፈው ሳምንት እስራኤል በደቡባዊው ራፋህ ከተማ ዘመቻዋን ጀምራለች። ከተማዋ ቀደም ሲል ከጋዛ የተሰደዱ ሰላማዊ ሰዎች የተጠሉባት ናት።
ቅዳሜ ዕለት ከከተማዋ በስተምስራቅ አቅጣጫ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ የአየር ድብደባ እና ዘመቻ ጀምራለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ሥራዎች ኤጀንሲ ኃላፊ ፊሊፕ ላዛሪኒ 800 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ከራፋህ ወጥተው በወደመችው ዃን ዩኒስ ከተማ ወይም በባህር ዳርቻው መጠለያ ፍለጋ መውጣታቸውን ተናግረዋል።
"የጋዛ ጦርነት ከጀመረ ወዲህ ፍልስጤማውያን ያላገኙትን ደኅንነት ፍለጋ ብዙ ጊዜ ለመሰደድ ተገደዋል” ብለዋል።
"ሰዎች ሲንቀሳቀሱ ያለአስተማማኝ ማለፊያ እና ጥበቃ በመሆኑ ለጥቃት ይጋለጣሉ። በሚሰደዱበት ጊዜ ሁሉ እንደፍራሾች፣ ድንኳኖች እና የማብሰያ ዕቃዎች ያሉትን መሠረታዊ ቁሳቁሶች ለማጓጓዣ መክፈል ስለማይችሉም ትተው ለመሰደድ ይገደዳሉ።”
"በጋዛ ያሉ ሰዎች ወደ 'ደህንነቱ የተጠበቀ’ ወይም 'ሰብአዊ' አካባቢዎች ሊዛወሩ ይችላሉ የሚለው አባባል ውሸት ነው። እያንዳንዱ ጊዜ የዜጎችን ህይወት ከባድ አደጋ ላይ ይጥላል።”
የፕሬዚዳንት ባይደን የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ከኔታንያሁ ጋር ለመነጋገር እሑድ ወደ እስራኤል ያቀናሉ። በዚህም ሲቪሎችን ለመጠበቅ ዕቅድ በሌለበት በራፋህ ላይ የሚፈጽመውን ማንኛውንም የእስራኤል ጥቃት ተቃውሞ በድጋሚ ይገልጻሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሱሊቫን ከሳዑዲ አልጋወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ሲነጋገሩ ቆይተዋል። የሳዑዲ መንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ ለጋዛ የሚደርሰውን እርዳታ ለማሳደግ እና የፍልስጤም አገርነትን መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።