ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ዋንጫ ማን ያነሳል? የዘንድሮው ውድድር ዓመት የመጨረሻ ግምት
እሑድ በተመሳሳይ ሰዓት እንዲከናወኑ ቀጠሮ የተያዘላቸው የአንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች የሊጉን አሸናፊ ቡድን ይለያሉ።
በመጨረሻው ጨዋታ ከማንቸስተር ሲቲ እና ከአርሰናል አንዱ የሊጉን ዋንጫ በማንሳት 2023/24 የፕሪሚየር ሊጉን ክብር ይደፋል።
በርንሌይ እና ሼፊልድ ዩናይትድ መውረዳቸውን አረጋግጠዋል።
የቢቢሲው እግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን የ38ኛ ሳምንት የሊጉን ጨዋታዎች ግምት እንደሚከተለው አስቀምጧል።
እሑድ
አርሰናል ከ ኤቨርተን
ኤቨርተን በጥሩ አቋም ላይ ቢገኝም ይህ ጨዋታ በአርሰናል አሸናፊነት ይጠናቀቃል።
ካላቸው አቋም አንጻር የሊጉ ዋንጫ ቢገባቸውም መድፈኞቹ ከኮሚዩኒቲ ሺልድ ሌላ ዋንጫ ሳያሳኩ የውድድር ዓመቱ ይጠናቀቃል።
መድፈኞቹ የቀድሞ ተጨዋቾቻቸውን መጋበዛቸው ዋንጫውን ቢያጡ እንኳን የሚያስደስታቸው ነገር ይኖራቸዋል።
ግምት፡ 3 – 0
ብሬንትፎርድ ከ ኒውካስል
በመሻሻል ላይ የሚገኘው ብሬንትፎርድ ውድድር ዓመቱን በድል ማጠናቀቅ ይፈልጋል።
የአሰልጣኝ ቶማስ ፍራንክ ስም ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር መያያዙ የሠሩትን መልካም ነገር ያሳያል።
ኒውካስል ሰባተኛ ሆኖ የውድር ዓመቱን ለማጠናቀቅ የማንቸስተር ዩናይትድን ውጤት ቢጠብቅም፤ ይሄ ከባድ ጨዋታ ይሆንበታል።
ግምት፡ 2 – 2
ብራይተን ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
ደካማው የየሮቤርቶ ዲዘሪቢ እና የቡድናቸው አቋም ረቡዕ ዕለትም ከቼልሲ ጋር ቀጥሏል።
ከሊጉ ደረጃ አጋማሽ በላይ ሆነው ለማጠናቀቅ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ከኒውካስል ጋር መልካም ውጤት አስመዝግቧል።
አሁን ባሉበት 8ኛ ደረጃ ላይ ሆነው ቢያጠናቅቁ የውድድር ዓመቱን በትክክል የሚገልጽላቸው ይሆናል።
ግምት፡ 2 – 1
በርንሌይ ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ይህ ወራጅ ቡድን የሚለይ ከባድ ጨዋታ መሆን የነበረበት ቢሆንም፤ በርንሌይ ቀድሞ መውረዱ እና ኖቲንግሃም ፎረስት ያለው ሰፊ የጎል ልዩነት ለመትረፍ ሰፊ ዕድል ፈጥሮለታል።
ዘንድሮ ጥሩ የነበረው ብርንሌይ ቡድኑን አስጠብቆ መቀጠል ከቻለ በቅርቡ ወደ ሊጉ ይመለሳል።
የነጥብ ቅነሳ ለገጠማቸው ፎረስት የዘንድሮው ውድድር ዓመት መጥፎ የሚባል ነው።
ግምት፡ 1 – 1
ቼልሲ ከ በርንመዝ
በርንመዝ በቅርቡ አቋሙ ቢወርድም በአሰልጣኝ አዶኒ አራኦላ ስር ድንቅ ዓመት አሳልፈዋል።
በተከታታይ አራት ጨዋታዎችን ላሸነፉት ቼልሲዎች ይህንን ጨዋታ አሸንፈው 6ተኛ በመሆን ማጠናቀቅ ከአጀማመራቸው አንጻር ድንቅ የሚባል ነው።
ቼልሲም በአሸናፊነቱ፤ ኮል ፓልመርም በጎል አግቢነቱ እንደሚቀጥል እገምታለሁ።
ግምት፡ 3 – 1
ክሪስታል ፓላስ ከ አስቶን ቪላ
ክሪስታል ፓላስ ትልቁ ፈተና ድንቅ ጥምረት የፈጠሩትን ማይክል ኦሊሴ፣ ኤበረቺ ኤዜ እና ዢን-ፊሊፔ ማቴታን ማቆየት ነው።
በቅርቡ ያሳዩትን ድንቅ ብቃት እሑድም ይደግሙታል ብዬ አስባለሁ።
አስቶን ቪላ በሚቀጥለው ዓመት በሻምፒዮንስ ሊግ እንደሚሳተፍ አረጋግጧል።
ከቶተንሃም ሽንፈት በኋላ ደስታቸውን ሲገልጹ በመቆየታቸው ይህንን ጨዋታ ፓላስ እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።
ግምት፡ 2 – 1
ሊቨርፑል ከ ዎልቭስ
በዚህ ጨዋታ ሞሐመድ ሳላህ ጎል አስቆጥሮ ሊቨርፑል በከፍተኛ የጎል ልዩነት በማሸነፍ ርገን ክሎፕን በፈገግታ ይሸኛሉ።
ባለፉት አስር ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፉት ዎልቭሶች በጥሩ አቋም ላይ አይገኙም።
ይህ ጨዋታ የሊቨርፑል እና ክሎፕ ጉዳይ ነው። የአሰልጣኙ መሄድ ለክለቡ ብቻ ሳይሆን ለፕሪሚየር ሊጉም ኪሳራ ነው።
ሊቨርፑል ካነሳው ዋንጫ በተጨማሪ ማንቸስተር ሲቲን እስከመጨረሻው በመፎካከርም ትልቅ ውድድርን ፈጥረዋል።
ግምት፡ 4 – 0
ሉተን ከ ፉልሃም
ከ17 ጨዋታዎች አንዱ ብቻ ማሸነፋቸው ሉተኖችን ከሊጉ ለመውረድ ጫፍ ላይ እንዲገኙ አድርጓቸዋል።
በሒሳባዊ ስሌት የመትረፍ ዕድል ቢኖራቸውም ከፎረስት ጋር ያላቸውን የጎል ልዩነት ማጥበብ የሚቻል አይደለም።
የሮብ ዊሊያም ቡድን አሸንፎ ከሊጉ ይወርዳል? አያሸንፍም።
ፉልሃም የሚጫወትበት ምክንያት ባይኖረውም ይህንን ጨዋታ ያሸንፋል።
ግምት፡ 1 – 2
ማንቸስተር ሲቲ ከ ዌስት ሃም
ሲቲ የሊጉን ዋንጫ ካነሳባቸው ሰባት ዓመታት አራቱን በመጨረሻው ቀን ማሳካቱ ብቻ ሳይሆን በሦስቱ ከመመረት ተነስተው ነው ያሸነፉት።
ይህንን ጨዋታ ሲቲ በፍጥነት ጎሎችን አስቆጥሮ ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ የሊጉ ባለክብር በመሆን ክብረ ወሰኑን ይሰብራል።
በየቦታው ያላቸው ተጫዋቾች ጥራት ያላቸው ከመሆኑም በላይ በየጊዜውም ራሳቸውን እየለወጡ ነው።
ሊጉ የዓለማችን ጠንካራው ቡድን መሆኑ ይነገራል። ሲቲ ዘንድሮም ጠንካራ ጨዋታዎችን ማለፍ ተገዷል።
ዴቪድ ሞዬስ በመጨረሻው የዌስት ሃም ጨዋታቸው ውጤት ማስመዝገብ አይችሉም።
ግምት፡ 5 – 0
ሼፊልድ ዩናይትድ ከ ቶተንሃም
አንጅ ፖስተኮግሉ አሸናፊ ቡድን ለመስራት ቢጥሩም ቡድኑ ውስጥ ተመሳሳይ አስተሳሰብ የለም።
አሸናፊ ቡድን ለመገንባት ደግሞ አርሰናል ዋንጫ እንዳያነሳ በሚል ቡድናቸው እንዲሸነፍ የሚፈልጉ ደጋፊዎች ሊኖሩ አይገባም።
አሰልጣኙ በመጀመሪያው ዓመት የቶተንሃም ቆይታቸው ከሚጠበቅባቸው በላይ አሳክተዋል።
ውድድር ዓመቱን መውረዱን ያረጋገጠውን ሼፊልድን በማሸነፍ ማጠናቀቅ ይፈልጋሉ።
ግምት፡ 0 – 2