የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ የኢትዮጵያ ቆይታ

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው ከፌደራል ባለስልጣናት፣ ከትግራይ አመራሮች፣ ከኦሮሚያ ተቃዋሚዎች እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት ዲፕሎማቶች ጋር ተገናኝተው በአገሪቱ ጸጥታና ሰላም ላይ መክረዋል።

ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨውን የፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም ስምምነት እንዲፈረም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል የሚባልላቸው ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ የተገኙትም ስምምነቱን አስመልክቶ ያደሩ ጉዳዮች ከግጭት መለስ በፖለቲካዊ ውይይት እንዲፈቱ ለማድረግ ነው።

በኢትዮጵያ ቆይታቸው የፕሪቶሪያን ስምምነት አፈጻጸም ከመገምገም በተጨማሪ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የበርካታ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፉ ያሉ ግጭቶች በድርድር እልባት እንዲያገኙ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መመርመር አስፈላጊነት ላይ ለመወያየት ነው።

ልዩ መልዕክተኛው ከሚያዝያ 30 እስከ ግንቦት 11 በሚያደርጉት ቆይታ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ናይሮቢ አቅንተው ከኬንያ ባለስልጣናት ጋር የጋራ ቀጣናዊ ተግዳሮቶች ላይ እንደሚመክሩ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ማይክ ሐመር ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ከሆነው የአሜሪካው አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ጋር ወደ መቀለ አምርተው ከትግራይ ክልል አመራሮች ጋር ተገናኝተው የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም ላይ ያሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች እና ቀጣይ እርምጃዎችን መወያየታቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በአፋጣኝ ለመፍታት የእስካሁኑን ሂደት መገምገም እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ መደረሱንም በዚሁ መልዕክታቸው ተጋርቷል።

ግንቦት አጋማሽ 2014 ዓ.ም የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ማይክ ሐመር የፕሪቶሪያን የስምምነት አፈጻጸም አስመልክቶ ከፌደራል ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን ባለስልጣናቱ አጠር ባሉ የኤክስ መልዕክቶቻቸው አጋርተዋል።

ጦርነቱ መቋጨቱን ተከትሎ የፌደራል እና የትግራይ አመራሮችን እያወዛገበ ያለውን የትጥቅ መፍታት፣ ተዋጊዎችን ማሰናበት እና መልሶ ከማህበረሰቡ ጋር የማዋሃድ ጉዳዮችን ከብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጋር ተገናኝተው መክረዋል።

ትጥቅ መፍታት፣ ተዋጊዎችን በመበተን እና መልሶ ለማህበረሰቡ ጋር ለማዋሃድ በሚደረገው የሰላም ግንባታ ጥረት አሜሪካ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን አቶ ተመስገን በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

በዚህም በገንዘብ፣ ቴክኒካል በሚደረጉ ድጋፎች ንቁ አጋርነትን ከአሜሪካ እንደሚጠብቁ አቶ ተመስገን በዚሁ መልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።

አምባሳደር ማይክ ከአቶ ተመስገን በተጨማሪም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ምስጋኑ አርጋ ጋር ባደረጉት ቆይታ የፕሪቶሪያን ስምምነት በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር የአለም አቀፉ ድጋፍ አስፈላጊነት ላይ መወያየታቸው ተጠቁሟል።

በተጨማሪም ሚኒስቴር ዲኤታው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ አዲስ መዋቅራዊ ግንኙነት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

ማይክ ሐመር ስለ ፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ከፌደራሉ እና ከትግራይ ባለስልጣናት በተጨማሪ ከአፍሪካ ህብረት ተወካዮች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ከአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና የደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶየ ጋር ባደረጉት ውይይት በአፍሪካ ቀንድ በተለይም የፕሪቶሪያ ስምምነት ተግባራዊነትን ትኩረት እንደሰጡ አምባሳደሩ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

በፕሪቶሪያው ስምምነት እና የናይሮቢ የትግበራ ሰነድ የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከትግራይ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ እንደሆነ ጠቅሷል።

ከዚህ ቀደም የከባድ መሳሪያዎች ርክክብ መደረጉ የተገለጸ ቢሆንም ከትጥቅ መፍታት፣ ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋም መዘግየት ጋር ተያይዞ በትግራይ አመራሮች እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል አለመግባባቶች መፈጠራቸው አልቀረም።

ትጥቅ መፍታት የዘገየባቸው ምክንያት ከፕሪቶሪያ ስምምነት በፊት ምንም ዓይነት የፖለቲካ ውይይት አለመካሄዱ እንደሆነ የብሔራዊ ከብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተስፋዓለም ይሕደጎ ከሰሞኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የትግራይ ሰራዊት አባላትን ወደ ማህበረሰቡ ለማዋሃድ የሚያስፈልግው በጀት በጣም ከፍተኛ እና በአገር ውስጥ አቅም ብቻ ሊሸፈን እንደማይችል ጠቅሰዋል።

በሰባት ክልሎች የሚገኙ 371,971 የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም ከ760 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከጥቂት ወራት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።

ከጄፍሪ ፌልትማን እና ዴቪድ ሳተርፊልድን በኋላ በሶስተኛ ልዩ መልዕክተኛነት የተሾሙት ማይክ ሐመር የኦሮሚያ እና የአማራ ግጭቶች በሰላም እንዲቋጩ ለማድረግ እየሞከሩ ይገኛሉ።

መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ለሁለተኛ ዙር ዳሬሰላም ባደረገው ድርድር አንደኛው አሸማጋይ መሆናቸው ይታወሳል።

ልዩ መልዕክተኛው በዚህ የኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች ጋር አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ተወያይተዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለቢቢሲ እንደተናገሩት ውይይታቸው በአጠቃላይ ያተኮረው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስላለው ውስብስብ ችግር ሲሆን በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በሚታየው ችግር ዙርያ ሰፊ ጊዜ ወስደው መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ማይክ ሐመር ከኦፌኮ እና ኦነግ አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የብሔራዊ ምክክር እና መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጦር ጉዳይ መነሳቱንም ፕሮፌሰር መረራ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የፕሪቶሪያን ስምምነት አስመልክቶ ከትግራይ እና ከፌደራል ባለስልጣናት፤ ኦሮሚያን በተመለከተ ከኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ቢያደርጉም የአማራን ግጭት በተመለከተ ከየትኛው አካል ጋር እንደተወያዩ የተጠቀሰ መረጃ የለም።

የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው ከአምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ ጋር በአገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።

አምባሳደር ማሲንጋ ከሰሞኑ “ሰብዓዊ መብቶችን እና ምክክሮችን የሚመለከት የፖሊሲ ንግግር” በሚል ርዕስ በአገሪቱ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲኖር እና ሰላም እንዲሰፍን አጽንኦት በሰጡበት ንግግራቸው ትጥቅ አንግበው እየታገሉ ላሉ እና አገሪቱን ለሚመሩ ባለስልጣናት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለኢትዮጵያ መንግሥት ባስተላለፉት መልዕክት “አገሪቱ ከጦርነት አውድማነት ይልቅ በሰላም የምታተርፈው ብዙ ነገር አለ። ጸጥታን በማስጠበቅ ላይ ያተኮረ አካሄድ ውስብስብ የፖለቲካ ጉዳዮችን አይፈታም። መንግሥትን የሚተቹትን ማሰርና ማዋከብ እልባት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን የሚፈታ አይደለም” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም ማዕዘን በጦር ሜዳ ፈጣ ድል አይኖርም በማለትም “የውይይት ጊዜው አሁን” ነው ብለዋል።

ይህንን የተቸው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለምአቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና አሠራር ውጪ የሚወጡ መግለጫዎች ተገቢነት የላቸውም ሲል ተችቷል።

“አገራችንን በምን መልክ ማስተዳደር እንደሚሻለንም በራሳቸው ተነሳሽነት ምክር ለመለገስ ሞክረዋል። ከዚህም አልፈው በህዝብ የተመረጠውን መንግሥት በሃይል ለመጣል የሚንቀሳቀሱ እና ሰላማዊ ዜጎችን በማዋከብ፣ በማፈን እና በማሸበር የሚታወቁ ቡድኖችን በመግለጫቸው በስም እየጠሩ ማጠቃለያ ሰጥተዋል።” ሲል ተችቷል።