ሳሙኤል ኤቶ ኳታር ውስጥ አንድን ሰው ሲማታ መታየቱ መነጋገሪያ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የካሜሩን እና የባርሴሎና የፊት መስመር ተጫዋች ሳሙኤል ኤቶ በኳታር አንድን ሰው ሲማታ መታየቱ መነጋገሪ ሆኗል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተሰራጨ ምስል ኤቶ ከብራዚል እና ከደቡብ ኮሪያ ጨዋታ በኋላ 974 በተባለው ስታዲየም አካባቢ ሰው ሲማታ አሳይቷል።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ ክስተቱ ከማጋጠሙ በፊት ኤቶ ከአድናቂዎች ጋር ፎቶግራፍ ሲነሳ እና በኤቶ የተደበደበው ግለሰብ ኤቶን እየተከታተለ ሲቀርጸው ያሳያል።
በአሁኑ ወቅት የካሜሮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሆነው ኤቶ፤ እየተከታተለ ቪዲዮ ሲቀርጸው ከነበረው ግለሰብ ጋር የቃላት ልውውጥ ሲያደርግ ይታያል።
ሳሙኤል ኤቶ በመጀመሪያ ግለሰቡን ለመማታ ሲሞክር አጠገቡ በነበሩ ሰዎች ቢገታም፣ በድጋሚ በኃይል ይዘውት የነበሩ ሰዎችን በማስለቀቅ በእግሩ የግለሰቡን አገጭ በመማታት ጥሎታል።
ኤቶ ግለሰቡ ምን ብሎት ለመማታት እንደተነሳ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
አራት ጊዜ የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው እና የኳታር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ አምባሳደር የሆነው እወቅ የእግር ኳስ ተጫዋች በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ቢቢሲ የኳታር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ እና የካሜሮን እግር ኳስ ፌዴሬሽንን አስተያየት ለማካተት ጥያቄ አቅርቦ እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
ሳሙኤል ኤቶ በተጫዋች ዘመኑ ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል።
ለአገሩ ብሔራዊ ቡድን 118 ጊዜ ተሰልፎ 56 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ከባርሴሎና በተጨማሪ ለሪያል ማድሪድ፣ ለማሎርካ፣ ለኢንተር ሚላን፣ ለቼልሲ እና ለኤቨርተን ተጫውቷል።












