ወታደራዊ ህግ በደነገጉት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ላይ ክስ እንዲመሰረት ፓርላማው ወሰነ

ደቡብ ኮሪያውያን ደስታቸውን እየገለጹ
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ወታደራዊ ህግ በደነገጉት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ላይ ክስ እንዲመሰረት ፓርላማው በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን ተከትሎ በርካቶች ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

የፕሬዚዳንት ዩን ሱክ ዮልን ከስልጣን የመውረድ እና የመከሰስ ዜናን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ኮሪያውያን በመዲናዋ ሴኡል ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

ምክር ቤቱ ቅዳሜ፣ ህዳር 5/ 2017 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ከ300 የፓርላማ አባላት ውስጥ አብላጫው 204ቱ ፕሬዚዳንቱ እንዲከሰሱ የድጋፍ ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

85ቱ የፓርላማ አባላት የተቃወሙ ሲሆን ሶስት ድምጸ ተአቅቦ እንደነበር የገለጹት አፈጉባኤ ው ዎን ሺክ ፓርላማው ክስ እንዲመሰረት በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል ሲሉ ስብሰባውን አጠናቀዋል።

"ለህዝቡ በዓመቱ መጨረሻ ዋዜማችሁ ደስተኛ እንደሚያደርጋችሁ ተስፋ እናደርጋለን። ሰርዛችሁት የነበረው የዓዲስ አመት ዝግጅታችሁ ወደነበረው ይመለሱ ይሆናል" ሲሉ አፈጉባኤው ተናግረዋል።

"የኮሪያ ሪፐብሊክ የወደፊት እጣፈንታ፣ ተስፋችን በህዝባችን እጅ ነው። ተስፋችን የጠነከረ ነው። በጣም እናመሰግናለን" ሲሉ ፓርላማው ስብሰባው ሲጠናቀቅ አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።

የፓርላማውን ውሳኔ ተከትሎ ፕሬዚዳንት ዩን ከስልጣናቸው የሚታገዱ ሲሆን ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ስልጣኑን ተረክበው አገሪቱን ይመራሉ።

ህገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ክስ ይመስረትባቸው በሚለው ላይ የመጨረሻውን ብያኔ ለማስተላለፍ ስድስት ወራት አሉት።

ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት አገራቸው በወታደራዊ ትዕዛዝ ስር እንድትሆን ድንጋጌ ማሳለፋቸውን ተከትሎ ፖለቲካዊ ቀውስ ተከስቶ ነበር።

ፕሬዚዳንቱ ለአጭር ጊዜ የቆየውን ይህንን ድንጋጌ በፓርላማው እምቢተኝነት ቢቀለብሱትም ክስ እንዲመሰረትባቸው ሂደት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም አልተሳካም ነበር።

ይህንንም ተከትሎ በርካቶች ከስልጣን እንዲወርዱ ከፍተኛ ተቃውሞ በአደባባይ እያሰሙ ነበር።

በፕሬዚዳንቱ እና አጋሮቻቸው ላይ አመጽ በማነሳሳት ክስ ምርመራ የተከፈተ ሲሆን በበርካቶቹ ባለስልጣናት ላይም የጉዞ እገዳ ተጥሏል።

ደቡብ ኮሪያውያን ደስታቸውን እየገለጹ

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ዲሞክራሲ በሰፈነባት አገራቸው በወታደራዊ ሕግ (ማርሻል ሎው) ስር እንድትሆን በድንገት ማክሰኞ፣ ኅዳር 24/2017 ዓ.ም. ማወጃቸው አገሪቱን ያስደነገጠ ክስተት ሆኗል።

ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ የዎል አገሪቱ በአምስት አስርት ዓመታት አይታው የማታውቀውን ይህንን አስደንጋጭ ውሳኔ ለመወሰን ምክንያታቸው "ፀረ መንግሥት ኃይሎች" እና የሰሜን ኮሪያን ስጋት በመጥቀስ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ከሰሜን ኮሪያ ኮሚኒስት ኃይሎች አገራቸውን ለመጠበቅ ወታደራዊ ሕጉ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናገሩ።

ነገር ግን ወታደራዊ ሕጉ በታወጀ ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የፓርላማ አባላቱ ፕሬዚዳንቱን ተቃውመው በምክር ቤት ከተሰበሰቡ በኋላ አስቸኳይ ድምጽ በመስጠት ውሳኔውን አግደዋል።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ሕግ እንዲያውጁ ምክንያት የሆናቸው እሳቸው እንዳሉት የውጭ ኃይሎች ስጋት ሳይሆን ውስጣዊ የፖለቲካ ችግሮች እንደሆኑ ግልጽ የሆነው ብዙም ሳይቆይ ነበር።

ወታደራዊ ሕግ (ማርሻል ሎው) የሲቪል ባለሥልጣናት ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንደማይችሉ በሚቆጠርበት ጊዜ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲመሩ የሚደረግበት ጊዜያዊ አገዛዝ ነው።

አንዲት አገር በወታደራዊ ሕግ ስር በምትሆንበት ወቅት የሲቪል መብቶች መታደግ እንዲሁም ወታደራዊ ሕጉ ሊራዘም የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል።

በደቡብ ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ወታደራዊ ሕግ የታወጀው በአውሮፓውያኑ 1979 ሲሆን፣ ወቅቱም አገሪቱን ለበርካታ ዘመናት የገዙት አምባገነኑ ፖርከ ቹንግ ሂ በመፈንቅለ መንግሥት መገደላቸውን ተከትሎ ነው።