ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፓኪስታን ዜጎቿ የሻይ ፍጆታቸውን እንዲቀንሱ ጠየቀች
የፓኪስታን ዜጎች በአገሪቱ ያለውን የምጣኔ ሃብት ቀውስ ለማረጋጋት የሚጠጡትን የሻይ መጠን እንዲቀንሱ ተጠየቁ።
የፓኪስታን ከፍተኛ ሚኒስትር አህሳን ኢቅባል፣ በቀን ጥቂት ብርጭቆ ሻይ መጎንጨት ፓኪስታን የሻይ ቅጠል ምርትን ከውጪ ለማስገባት የምታወጣውን ወጪ ይቀንሳል ብለዋል።
በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከውጭ የሚገባ ማንኛውም ምርት ለመግዛት የሚበቃው ከሁለት ወር ላነሰ ጊዜ ብቻ ነው ተብሏል። ይህም አገሪቷን አስቸኳይ የገንዘብ እርዳታ እንድትፈልግ አስገድዷታል።
ፓኪስታን ባለፈው ዓመት ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ ሻይ ቅጠል ከውጭ በማስገባት ከዓለም ከፍተኛውን ሻይ ቅጠል አስመጪነት ቦታን ይዛለች።
እንደ ፓኪስታን ሚዲያ ከሆነ ሚኒስትር ኢቅባል “የአገሬው ሰው የሻይ ፍጆታውን ወደ አንድ ወይም ሁለት ብርጭቆ እንዲቀንስ እጠይቃለሁ። ምክንያቱም ሻይ ቅጠል የምናስገባው በብድር ነው” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ተቋማት የሚጠቀሙትን የኤሌክትሪክ ኃይል ለመቆጠብ የንግድ ቦታቸውን ምሽት 2፡30 ላይ እንዲዘጉ ሚኒስትሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ተማፅኖው ለፓኪስታን ሕዝብ የቀረበው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት በተከታታይ እና በፍጥነት እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ ነው።
ይህም በአገሪቱ፣ መንግሥት ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት የሚያወጣቸውን ወጪዎች በመቀነስ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ይዞ እንዲያቆይ አስገድዶታል።
የአገሪቷ ሕዝቦች የሻይ ፍጆታቸውን እንዲቀንሱ መጠየቃቸው በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኗል።
አብዛኛው ሰውም አገሪቷ የገጠማት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ቀውስ የሻይ ፍጆታን በመቀነስ ይፈታል የሚል እምነት የለውም።
የፓኪስታን የውጭ ምንዛሬ ክምችት የካቲት ወር ላይ ከነበረው 16 ቢሊየን ዶላር በሰኔ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ወደ ከ10 ቢሊየን ዶላር በታች አሽቆልቁሏል።
ባለፈው ወር የካራቺ ባለሥልጣናት በአገሪቷ ያለውን የውጪ ምንዛሬ ክምችት ለመጠበቅ በርካታ መሠረታዊ ያልሆኑ የቅንጦት እቃዎች እንዳይገቡ ገደብ ጥለው ነበር።
በአገሪቷ ያለው የምጣኔ ሃብት ቀውስ፣ ባለፈው ሚያዝያ ወር በተደረገው የምክር ቤት ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህንን ለተኩት ሸህባዝ ሸሪፍ መንግሥት ትልቅ ፈተና ሆኗል።
ሸሪፍ ሥልጣን ተረክበው ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ የአገሪቷ ምጣኔ ሃብት በአግባቡ አልተመራም፤ ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመመለስም ከባድ ነው ሲሉ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ከሰዋል።
ባለፈው ሳምንት ካቢኔው፣ የተቋረጠውን የ6 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራም እንዲጀመር ዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ)ን ለማሳመን የ47 ቢሊየን ዶላር በጀት አጽድቋል።
አይኤምኤፍ እአአ በ2019 በውጭ ምንዛሬ እጥረት እና ለዓመታት በዘገየ እድገት ምክንያት የሚፈጠር የምጣኔ ሃብት ቀውስን ለማቃለል የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም፣ አበዳሪዎች አገሪቷ ብድሩን ለመክፈል ያላትን የፋይናንስ አቅም ከጠየቁ በኋላ ቆሟል።