ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምጣኔ ሃብት፡ በቱርክ የኑሮ ውድነት 70 በመቶ ገደማ መጨመሩ ተገለጸ
በቱርክ የኑሮ ውድነት በአንድ ዓመት ውስጥ 70 በመቶ ገደማ መጨመሩ ተገለጸ። ይህም በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
የመጓጓዣ፣ የምግብ፣ እና የቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎች ዋጋ በዓመቱ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቶባቸዋል።
በመላው ዓለም ያሉ አገራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የዋጋ ንረት ምክንያት እየተፈተኑ ነው።
በቱርክ የተከሰተው የዋጋ ንረት ግን ፕሬዚደንቱ የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የሚረዳውን 'የወለድ ምጣኔን መጨመር' ባለመፈለጋቸው የተከሰተ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።
በአገሪቱ የምግብ እና አልኮል የሌላቸው መጠጦች ዋጋ 89.1 በመቶ ዓመታዊ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው ሲሆን የቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎች እና ቁሳቁሶች ዋጋ እስከ 77.64 በመቶ ጨምሯል።
ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር በሚያዝያ ወር የዋጋ ንረቱ በ7.25 በመቶ ማሻቀቡን ከቱርክ ስታቲስቲክስ ኢንስቲቲዩት የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
ፕሬዚደንት ሬሲብ ጣይብ ኤርዶዋን የውጭ ምንዛሬን ከማረጋጋት ይልቅ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረጋቸው የቱርክ መገበያያ ገንዘብ ሊራ ዋጋም ወድቋል።
ፕሬዚደንት ኦርዶዋን የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የወለድ ምጣኔን ማስተካካል የሚለው አሠራር አይዋጥላቸውም። "የወለድ ምጣኔ የሁሉም መጥፎ ነገሮች እናት እና አባት" ሲሉ ነው የሚገልጹት።
በመሆኑም ፕሬዚደንቱ በውጭ ምንዛሬ ገበያዎች ውስጥ ጣልቃ መግባትን ጨምሮ የዋጋን ንረትን ለማረጋጋት ያልተለመደ ፖሊስ ተጠቅመዋል ሲሉ ባለሙያዎች ይተቻሉ።
የቱርክ ፕሬዚደንት ባለፈው ዓመት የአገሪቱን ማዕከላዊ ባንክ አመራር ያሻሻሉ ሲሆን ባንኩ ከመስከረም ወር ጀምሮ 19 በመቶ የነበረውን የወለድ ምጣኔ ወደ 14 በመቶ ዝቅ አድርጓል።
በሚያዝያ ወር በተከታታይ ለአራተኛ ወር የዋጋ ግሽበቱ እየተባባሰ ቢመጣም የወለድ ምጣኔው ባለበት ነው።
በብሉቤይ ንብረት አስተዳዳር የገበያ ባለሙያ የሆኑት ቲሞቲ አሽ "በቱርክ ውስጥ ያለው አስገራሚ የገንዘብ ፖሊስ ውድቀት ነው" ብለዋል።
"ዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል" የሚሉት ባለሙያው የምጣኔ ሐብት ፖሊሲን እንደገና ለመጻፍ መሞከር መሬትን ጠፍጣፋ ለማድረግ ከመሞከር ጋር ተመሳሳይ ነው" በማለት ለተከሰተው የዋጋ ንረት ፕሬዚደንቱን ከሰዋል።
በካፒታል ኢኮኖሚክስ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጃሰን ቱቪይ በበኩላቸው ፖሊሲ አውጭዎች እርምጃ እንደሚወስዱ እና የወለድ ምጣኔዎችን ሊጨምሩ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ምንም ምልክቶች የሉም ብለዋል።
በመሆኑም የዋጋ ግሽበቱ በዚህ ዓመትም ባለበት እንደሚቀጥል ተንብየዋል።
በዓለም ዙሪያ ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ የአቅርቦት ችግሮች እና በዩክሬን ባለው ጦርነት ምክንያት የመሠረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ በመላው ዓለም በፍጥነት እየጨመረ ነው።
በርካታ አገራት የወለድ ምጣኔን በመጨመር ግለሰቦችና ድርጅቶች ገንዘብ ተበድረው ጥቂት እንዲያጠፉ በማበረታታት ለተከሰተው ችግር ምላሽ ሰጥተዋል።
ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ከፍተኛ የሆነ የወለድ ምጣኔ መጨመሩን አስታውቋል።
ሕንድ እና አውስትራሊያን ጨምሮ ሌሎች አገራትም የወለድ ምጣኔን ጨምረዋል። ባንክ ኦፍ ኢንግላንድም የወለድ ምጣኔውን እንደሚጨምር አሊያም ባለበት እንደሚቀጥል ዛሬ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።