የቻይናው የመከላከያ ሚኒስትር ከአሜሪካ ጋር የሚደረግ ጦርነት ‘ለዓለም እልቂት’ ይሆናል አሉ

የቻይና መከላከያ ሚንስትር ሊ ሻንግፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቻይና መከላከያ ሚኒስትር ሊ ሻንግፉ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር ጦርነት ብትገጥም ዓለም “መቋቋም የማትችለው እልቂት” ይሆናል አሉ።

ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን ከያዙ በኋላ ትልቅ ግምት በተሰጠው የመጀመሪያ ይፋዊ ንግግራቸው “አንዳንድ አገራት” በእስያ አህጉር የጦር መሳሪያ መታጠቅ እሽቅድምድም ይዘዋል ብለዋል።

ጄኔራል ሊ ሻንግፉ አሜሪካ እና ቻይና በማያግቧቧቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ ዓለም በቂያቸው ነች ብለዋል።

ቀደም ሲል የቻይና ጦር መርከብ በታይዋን ሰርጥ “አደገኛ” በሆነ ሁኔታ ከአሜሪካ እና ከካናዳ የጦር መርከቦች ጋር ከመላተም ለጥቂት ነበር የተረፈችው ተብሎ ነበር።

ቻይና ግን ለክስተቱ ሁለቱን አገራት ወቅሳለች። ቻይና፣ አሜሪካ እና ካናዳ ሆነ ብለው ጠብ የሚያጭር ተግባር ፈጽመዋል ብላለች።

ሁለቱ የሰሜን አሜሪካ አገራት ደግሞ ዓለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት መርከቦቻችን በዓለም አቀፍ የውሃ ክልል ውስጥ እየቀዘፉ ነበር ብለዋል።

ባለፈው ኅዳር ወር ላይ የቻይና መከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ጄኔራል ሊ፤ አሜሪካ ‘የቀዝቃዛው ጦርነት አመለካከትን’ ታራምዳለች ሲሉ የተቹ ሲሆን፣ ይህም ከፍተኛ ‘የደኅንነት ስጋtእን የሚደቅን’ ነው ብለዋል።

ጄኔራሉ የታይዋን ስርጥ ላይ ስላጋጠመው ክስተት ሲጠየቁ፤ በቀጠናው የደኅንነት ስጋት እየፈጠሩ ያሉት ከቀጠናው ውጪ ያሉ አገራት ናቸው ካሉት ባሻገር ዝርዝር ነገር ከመናገር ተቆጥበዋል።

በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባቸው የሚገኙት የቻይና መከላከያ ሚኒስትር ይህን ያሉት በሲንጋፖር በተከናወነ የእስያ-ፓሲፊክ ዓመታዊ የደኅንነት ስብሰባ ላይ ሲሆን፣ በዚህ ስብሰባ ላይ የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ተሳታፊ ነበሩ።

ጄኔራል ሊ ማዕቀብ የተጣለባቸው እአአ 2018 ላይ ከሩሲያ የጦር መሳሪያ ከተፈጸመ ግዢ ጋር በተያያዘ ነው።

አሜሪካ ይህን በመቃወም በጉዳዩ ላይ ከቻይና ጦር ጋር ቀጥተኛ ንግግር ለማድረግ ብትጠይቅም፣ ቤይጂንግ ጥያቄውን ውድቅ አድርጋለች።

ጄኔራል ሊ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የቻይና መከላከያ ሚኒስትር ሆነው የሚቀጥሉ ሲሆን፣ ተጥሎባቸው የሚገኘው ማዕቀብ ወደ አሜሪካ እንዳይጓዙ ያደርጋቸዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቻይና የታይዋን የይገባኛል ጥያቄ እንዲሁም በደቡብ ቻይና ባሕር የድንበር ግጭት የዋሽንግተን እና የቤይጂንግ ግንኙነት ካሻከሩ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።