ሩሲያ ከዩክሬን የተቃጣባትን ከባድ ጥቃት መመከቷን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ከባድ የዩክሬን ጥቃት መከላከሉንና 250 ዩክሬናዊያንን መግደሉን ገለጸ።
እስካሁን ከኪይቭ የተሰጠ መግለጫ የለም። የሩሲያ መግለጫም በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።
ሚኒስቴሩ እንዳለው ዩክሬን እሑድ መልሶ ማጥቃት ጥቃት የከፈተችው በዶኔትስክ ግዛት ሲሆን ስድስት ሜካናይዝድ ሁለት የታንክ ክፍለ ጦር ይዛ ነው የመጣችው።
ምንም እንኳ ዩክሬን መልሶ ማጥቃት እንደምትፈፅም ቀድማ የገለጸች ቢሆንም እሑድ ዕለት ስለጥቃቱ ምንም ያለችው ነገር የለም።
ዩክሬን በሩሲያ የተወሱዳበትን መሬቶች ለማስመለስ ጥቃት ትክፈት አትክፈት ግልጥ አልሆነም።
“ግንቦት 27 (2015 ዓ.ም) ንጋት፤ ጠላት በደቡብ ዶኔትስክ በኩል በአምስት አቅጣጫዎች ከባድ ጥቃት ከፍቷል” ይላል የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በቴሌግራም የለቀቀው መግለጫ።
መግለጫው አክሎ የዩክሬን ጦር የሩሲያን ጦር ሰብሮ ለመግባት ሞክሮ ነበር።
“ጠላት ግድያውን በድል አልተወጣም። ያሰበው አልተሳካለትም።”
ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ከሰማይ ውርጅብኝ ሲወርድባቸው አንዳንድ ተንቀሳቃሽ ምስሎች አሳይተዋል።
ሩሲያ እንደምትለው ዩክሬን 250 ወታደሮች አጥታለች፤ 16 ታንኮች ደግሞ ወድመውባታል።
ዩክሬን የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ለመወሰድ ለወራት ስታወጣ ስታወርድ ቆይታለች።
ነገር ግን ወታደሮች ለማሰልጠንና ከምዕራባዊያን ሃገራት ዕርዳታ ለመሰብሰብ ብዙ ጊዜ ወስዶባታል።
“መልሶ ማጥቃቱ መቼ እንደሚጀመር አናስታውቅም” ይላል የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር እሑድ ዕለት በቴሌግራም የለቀቀው መልዕክት።
የዩክሬን መንግሥት ለሕዝቡና ለምዕራባዊያን ወዳጆቹ የሩሲያን ጦር ሰብሮ ገብቶ የተወሰደበትን መሬት ማስመለስ እንደሚችል ማስመስከር አለበት።
በሌላ ዜና የሞስኮውን መንግሥት የሚቃወሙ ታጣቂዎች ዩክሬን ድንበር በምትገኘው ቤልጎርድ አቅራቢያ የሩሲያ ወታደሮችን መማረካቸውን አስታውቀዋል።
ሊበርቲ ኦፍ ራሺያ ሌጊዮን የተሰኘው ታጣቂ ቡድንና ራሺያን ቮሉንቲር ኮር ናቸው ይህን ያሉት።
ሁለቱም ቡድኖች የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን መንግሥት መገልበጥ ይፈልጋሉ።
ፑቲን ባለፈው የካቲት ዩክሬን ላይ የከፈቱትን ክተት ይቃወማሉ።
ሩሲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድንበር አካባቢ እየተፈጠሩ ላሉ ጥቃቶች ዩክሬንን ተወቃሽ ብታደርግም የኪይቭ መንግሥት ይህን ክዷል።












