አሜሪካ የሱዳን ጦርነትን አባብሰዋል ባለቻቸው ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጣለች

ተዋጊዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

አሜሪካ በሱዳን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት እያባበሱ ነው ባለቻቸው በርካታ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታወቀች።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት የተጣላቸው ማዕቀቦች በሱዳን እየተዋጉ ያሉት የሁለቱ ኃይሎች ዋና የገቢ ምንጭ እንዲቋረጥ ያደርጋል ይላል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አንተኒ ብሊንከን ባወጡት መግለጫ የሱዳንን ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋትን አደጋ ላይ የጣሉት የሱዳን ጦር ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እንዲሁም በቁጥጥራቸው ስር የሚገኙ ተቋማትን የጆ ባይደን አስተዳደር ተጠያቂ ያደርጋል ብለዋል።

በዚህም የባይደን አስተዳደር ተጠያቂነትን ለማስፈን በሁለቱ ኃይሎች እና በሚመሯቸው ተቋማት ላይ ሦስት ዓይነት እግዶችን ጥሏል። የቪዛ ክልከላ፣ የኢኮኖሚ ማዕቀብ እና የአሜሪካ የንግድ እንቅስቃሴ በሱዳን ዳግም እንዲጤን ያደርጋል ተብሏል።

አሜሪካ በሱዳን ጦር ኃይሎች እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ላይ ይህን ማዕቀብ የጣልኩት በሳዑዲ አረቢያ ጀዳ የተደረሰውን ስምምነት በመጣሳቸው ነው ብሏል።

“ዘረፋ፣ የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ ቤት እና መሠረተ ልማቶች ላይ መስፈር እንዲሁም ማጥቃት፣ የአየር ጥቃቶችን መሰንዘር እና ከባድ መሳሪያ መጠቀም፣ ያልተፈቀዱ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እና የሰብዓዊ እርዳታ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዳይጀመሩ እክል ማድረግ” የሚሉ ክሶች ቀርቧል።

አሜሪካ በሱዳን ጦር ኃይሎች እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አመራሮች እንዲሁም በቀድሞ የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አል-በሽር አስተዳደር ወቅት ባለስልጣን የነበሩ እና አሁን ላይ ግጭቱን እያባባሱ ናቸው በተባሉ መግለጫው ላይ በስም ባልተጠቀሱ መሪዎች ላይ የቪዛ ክልከላ ጥላለች።

ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ግንኙነት ያለው እና በዳርፉር ግዛት ወርቅ አውጪ በሆነው አል ጁናይድ ኩባንያ ላይ ማዕቀብ ተጥሏል። አሜሪካ ይህ በፈጥኖ ደራሽ መሪው ጀነራል መሐመድ ዳጋሎ ቁጥጥር ሥር ያለው ኩባንያው ከሚያስተዳድራቸው ወርቅ ማውጫ ማዕድናት ከሚያገኘው ገቢ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለተዋጊዎቹ መሳሪያ ይገዛል ይላል።

ከዚህ በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስ በሱዳን መንግሥት በሚተዳደረው ሱዳን ማስተር ቴክኖሎጂ ተብሎ በሚጠራ ኩባንያ ላይ ማዕቀብ ጥላለች። ይህ ኩባንያ ለሱዳን ጦር ኃይሎች ጦር መሳሪያ እና ተሸከርካሪዎች በሚያቀርቡ ሦስት ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ የባለድርሻ ባለቤት አለው ትላለች።

ዲፌንስ ኢንደስትሪስ ሲስተም የተባለ ኩባንያም ለአገሪቱ ጦር መሳሪያዎችን ይገዛል በሚል ማዕቀብ ተጥሎበታል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ፣ ግምጃ ቤት፣ ንግድ እና የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ድርጅት የሆነው ዩኤስኤይድ በሱዳን በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የአሜሪካ እና የአሜሪካውያን የንግድ እንቅስቃሴን የማይጎዳ ስለመሆኑ አስራራቸው ላይ ማሻሻያ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

የሱዳኑን ጦርነት ተከትሎ በግጭቱ ተሳታፊ በሆኑ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ማዕቀቦች ቢጣሉም፤ በአሜሪካ ማዕቀብ ስር ረዥም ጊዜን ባሳለፈችው ሱዳን የአሜሪካ አዲሱ ማዕቀብ የሚኖረው ጫና አነስተኛ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

አሁን ላይ ለብዙዎች ስጋት የሆነው የሱዳኑን ግጭት እንዴት ማቆም እንደሚችል መልስ ያለው አካል አለመኖሩ እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እየጨመረ መሆኑ ነው።