ሱዳን ካርቱም ውስጥ በተፈጸመ የሮኬት ጥቃት 18 ሰዎች ሲገደሉ ከ100 በላይ ቆሰሉ

ካርቱም ውስጥ ቀደም ሲል በተደረገ ውጊያ የወደሙ መኪኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካርቱም ውስጥ ቀደም ሲል በተደረገ ውጊያ የወደሙ መኪኖች

በሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያ ቀጥሎ በዋና ከተማዋ ካርቱም ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት 18 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።

ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በስተደቡብ በሚገኝ አንድ የገበያ ስፍራ ላይ በተፈጸመ የሮኬት ጥቃት ከተገደሉት 18 ሰዎች በተጨማሪ ከ100 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን የአገሪቱ ዶክተሮች ማኅበር አረጋግጧል።

ረቡዕ ዕለት በተፈጸመው ጥቃት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ጦርነቱ በሱዳን ውስጥ ከተቀሰቀሰ በኋላ በካርቱም ውስጥ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተገደሉበት ነው።

ይህ የሮኬት ጥቃት የተፈጸመው በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተወካዮች መካከል ግጭቱን ለማስቆም ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ድርድር መቋረጡን ተከትሎ ነው።

ባለፈው ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም. ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ካርቱምን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ውስጥ ከፍተኛ ውጊያዎች እየተካሄዱ በመሆናቸው ሰላማዊ ነዋሪዎች ለአደጋ ተጋልጠዋል።

በካርቱም ደቡባዊ ክፍል ውስጥ በሚገኘው ማዮ በተባለ የገበያ ስፍራ 18 ሰዎች የተገደሉበት የሮኬት ጥቃት ያጋጠመው ተፋላሚዎቹ ኃይሎች በከባድ መሳሪያ እና በአየር ጥቃት ባካሄዱት ውጊያ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

የጄኔራል አል ቡርሐን እና የጄኔራል ዳጋሎ ኃይሎችን ለማሸማገል በአሜሪካ እና በሳዑዲ አረቢያ አማካይነት ሲካሄድ የቆየው ድርድር መቋረጡን ተከትሎ ውጊያው ተባብሶ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

አሜሪካ ሁለቱ ወገኖች ጦርነቱን ለማቆም ፍላጎቱ ካላቸው የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ድርድር በማድረግ ከስምምነት እንዲደርሱ የሚያስችል ሚና ለመጫወት ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።

ነገር ግን የጦር ሠራዊቱ እና ፈጥኖ ደራሹ ኃይል አንዳቸው በሌላኛው ላይ የበላይነትን ለመያዝ በጦርነቱ ለመቀጠል የቆረጡ መስለዋል።

የሱዳን ዶክተሮች ቡድን በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መረጃ ማዮ በሚባለው አካባቢ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በተፈጸመ አሰቃቂ የከባድ መሳሪያ ድብደባ 17 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ106 በላይ መቁሰላቸውን አመልክቷል።

ሁለት ወር ሊሞላው በተቃረበው የሱዳን ጦር ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል መካከል እየተካሄደ ባለው ውጊያ አስካሁን ቢያንስ 883 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል።

ተዋጊ ኃይሎቹን የሚመሩት የአገሪቱ ኃያልን ጄኔራሎች በአገሪቱ የሥልጣን መንበር ላይ የቆዩ ሲሆን፣ የበላይነትን ለመያዝ በተፈጠረ የሥልጣን ሽኩቻ ነው ወደ እርስ በርስ ጦርነት የገቡት።

ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ሁለቱ ወገኖች ተኩስ ለማቆም እና ለመደራደር ለበርካታ ጊዜያት ቢስማሙም አስካሁን ድረስ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ ነው።

ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል ሱዳንን የመሩት አልበሽር በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የተመሠረተው የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትርን በመፈንቅለ መንግሥት በማስወገድ አሁን ጦርነት ውስጥ የገቡት የጦር መሪዎች አገሪቱን እየመሩ ቆይተዋል።

የጦር ኃይሉ አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀ መንበር፣ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) ደግሞ ምክትል ሊቀ መንበር ነበሩ።