ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኳታር አደራዳሪነት በኢራን ታስረው የነበሩት አምስት አሜሪካውያን ነጻ ሊወጡ ነው
በኢራን በቁጥጥር ሥር የነበሩ አምስት የአሜሪካ እና የኢራን ጥምር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በኳታር አደራዳሪነት ነጻ ሊወጡ ነው።
አምስቱ ግለሰቦች ከእስር የሚለቀቁት አሜሪካ ዜጎቿን ነጻ ለማውጣት ስትል እንዳይንቀሳቀስ አድርጋ የነበረው የኢራን 6 ቢሊዮን ዶላር እንዲለቀቅ በኳታር አደራዳሪነት ከተስማማች በኋላ ነው።
በአሜሪካ ማዕቀብ ምክንያት በደቡብ ኮሪያ እንዳይንቀሳቀስ ታግዶ የቆየው የኢራን ገንዘብ የኳታር ባንክ መድረሱ እንደተረጋገጠ አምስቱ ግለሰቦች አውሮፕላን ተሳፍረው ጉዟቸውን ይጀምራሉ ተብሏል።
አሜሪካ አምስቱን ግለሰቦች ነጻ ለማውጣት ገንዘቡ እንዲለቀቅ ከመፍቀዷም በተጨማሪ በአሜሪካ በእስር ላይ የነበሩ አምስት ኢራናውያንን ለመልቀቅ ተስማምታለች።
ዛሬ ከኢራን እስር ቤት ነጻ ይወጣሉ ከተባሉ አሜሪካውያን መካከል የ51 ዓመቱ ሲያማክ ናማዚ፣ የ59 ዓመት የንግድ ሰው ኢማድ ሻርጊ እና የ67 ዓመት የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ ሞራድ ታግባዝ ይገኙበታል።
የጆ ባይደን አስተዳደር እነዚህን ዜጎቿን ለማስለቀቅ በእግድ የተያዘው ገንዘብ እንዲለቀቅ መስማማቱ ብዙ ትችት አስከትሎበታል።
አንድ የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የባይደን አስተዳደር “በዓለም ላይ ሽብር በመደገፍ ለሚታወቅ መንግሥት የእገታ ማስለቀቂያ ገንዘብ እየሰጠ ነው” ሲሉ ውሳኔውን ተችተዋል።
የባይደን አስተዳደር ግን ኢራን ወደ ኳታር ማዕከላዊ ባንክ የሚገባውን ገንዘብ መጠቀም የምትችለው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ወጪዎችን ለመሸፈን ብቻ ሰለሆነ ከገንዘቡ የምታገኘው ጥቅም የተገደበ ነው ይላል።
ኢራን በመላው ዓለም ከነዳጅ ሽያጭ ማግኘት የነበረባትን ገንዘብ ሳትሰበስብ እአአ 2018 ላይ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምዕራባውያኑ ከኢራን ጋር ደርሰውት የነበረውን የኒውክለር ስምምነት ጥለው መውጣታቸው ተከትሎ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ሳይከፈላት ቀርቷል።
አሁን የአሜሪካ መንግሥት ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ ማንሳቱ በአውሮፓ፣ ኢሲያ እና መካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ባንኮች የኢራንን ገንዘብ ወደ ኳታር ማዕካለዊ ባንክ እንዲያዘዋውሩ ይፈቅድላቸዋል።