ቦይንግ ከኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ አውሮፕላን አደጋዎች ጋር በተያያዘ በማጭበርበር ክስ ለፍርድ ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቦይንግ በማጭበርበር ክስ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ነው።
በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዥያ ተከስክሰው ለ346 ሰዎች ሕልፈት ምክንያት የሆኑትን አውሮፕላኖች በተመለከተ ነው የማጭበርበር ክስ የተመሠረተበት።
ሁለቱም አደጋዎች የተከሰቱት ከቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን መቆጣጠሪያ ሥርዓት ጋር በተያያዙ ግድፈቶች ሲሆን፣ ቦይንግ ስለነዚህ የመቆጣጠሪያ ሥርዓቶች መረጃ ሳይሰጥ መቅረቱ ተገልጿል።
ለተጎጂዎች ካሳ እንዲሁም በቅጣት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማምቶ የፍርድ ቤት ሂደት ሳይካሄድ ቀርቶ ነበር።
ቤተሰቦቻቸውን በአደጋው ያጡ ሰዎች ስምምነቱ በድጋሚ እንዲታይ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።
በዚህም መሠረት አውሮፕላን አምራቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ፍርድ ቤት ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃል ይሰጣል።
ከዚህ ቀደም ቦይንግ ከአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስትር ጋር ስምምነቱን በድጋሚ ከፍቶ ለመቃኘት ሳይፈቅድ ቀርቷል። ዳግመኛ የመክፈት ጥያቄውን “ያልተጠበቀ፣ የማይተገበር እና ኢ-ፍትሐዊ” ሲል ነበር የገለጸው።
ስለጉዳዩም አስተያየት ለመስጠት አልፈቀደም።
ከሁለቱ አውሮፕላን አደጋዎች በኋላ ከበረራ ታግዶ የነበረው ቦይንግ እአአ በ2020 በአሜሪካ፣ በ2021 ደግሞ በአውሮፓ ወደ በረራ ተመልሷል።
ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሊጓዝ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 302 በረራው ተጀምሮ ከደቂቃዎች በኋላ ተከስክሶ ተሳፋሪዎችና የበረራ ሠራተኞችን ጨምሮ 157 ሰዎች መሞታቸው አይዘነጋም።
አደጋው ከ737 ማክስ አዲስ ዲዛይን ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ከዚህ አደጋ ከወራት በፊት የኢንዶኔዥያው አየር መንገድ ላየን ኤር አውሮፕላን ከጃካርታ ወደ ፒናንግ ሲጓዝ ጃጃ ባሕር ላይ ተከስክሶ ተሳፋሪዎችና የበረራ ሠራተኞችን ጨምሮ 189 ሰዎች ሞተዋል።
የካሳና ቅጣት ክፍያው የገጠመው ተቃውሞ
በተደረጉ ምርመራዎች መሠረት ሁለቱ አደጋዎች የተከሰቱት ኤምሲኤኤስ ከተባለው የበረራ መቆጣጠሪያ መተግበሪያ ጋር በተያያዘ ስህተት ምክንያት ነው።
ይህ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ዲዛይን የተደረገው ቀድሞ የነበረውን 737 ያበሩ የነበሩ አውሮፕላን አብራሪዎች ተጨማሪና ገንዘብ የሚያስወጣ ሥልጠና ሳያስፈልጋቸው አዲሱን አውሮፕላን ማብረር እንዲችሉ ነው።
ሆኖም ግን መቆጣጠሪያው ሳይሠራ ቀርቶ በሁለቱም አውሮፕላኖች የነበሩ አብራሪዎች አውሮፕላኖቹን መቆጣጠር ሳይችሉ ቀርተው አደጋዎቹ ተከስተዋል።
በአሜሪካ የተደረገ ምርመራ እንደሚያሳየው ቦይንስ ስለ ኤምሲኤኤስ ሥርዓት መረጃ በአውሮፕላን አብራሪዎች ማሠልጠኛ ውስጥ አላካተተም። ከአሜሪካ አቪዬሽን ተቆጣጣሪ ጋር ሲነጋገር ይህ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ያለውን ሚና ሆነ ብሎ አሳንሶ ገልጿል።
በ2021 የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስትር ቦይንግን በማጭበርበር ከሷል። ሆኖም ግን ቦይንግ ፍርድ ቤት ሳይሄድ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እና ቅጣት ለመክፈል ተስማምቷል።
ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ በደረሰው አውሮፕላን አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎችን አስቆጥቷል።
ስምምነቱ ያለእነሱ ዕውቅና የተደረገ፣ መብታቸውን የጣሰ፣ ቦይንግን ከተጠያቂነት የሚያሸሽ “የታይታ ስምምነት” እንደሆነ እየገለጹ ነው።
ቦይንግ የሚወክለውን “ትክክለኛ አካል” ወደ ፍርድ ቤት እንዲልክ ቢታዘዘም ማንን እንደሚልክ አልታወቀም።
በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎችም ለፍርድ ቤት ቃላቸውን ይሰጣሉ። ቦይንግን ፍርድ ቤት የማቅረቡ ጉዳይ በራሱ ለእነዚህ ሰዎች ትልቅ እርምጃ ነው።
“አሁን ገና ሰሚ አገኘን”
ጆሴፍ ዋታይካ የተባሉ አባቷን በአደጋው ያጣችው ዚፖራ ኩርያ፣ ቦይንግ ተጠያቂ እንዲሆን ከፍተኛ ንቅናቄ አድርጋለች።
በቴክሳሱ ፍርድ ቤት የምትገኝ ሲሆን፣ ለአባቷ ክብር የሚሰጥ ንግግር እንደምታደር ገልጻ “አሁን ገና ሰሚ እንዳገኘን ተሰምቶናል። የሞቱት 346 የምንወዳቸው ሰዎች አሁን ገና ዋጋ እንዳገኙ ይሰማኛል” ብላለች።
ሳም የተባለ ልጁን ያጣው ማርክ ፔግራም ቴክሳስ ሄዶ የፍርድ ሂደቱን መከታተል ባይችልም ቦይንግ ፍርድ ቤት በመቅረቡ ደስተኛ ነው።
“ለኛ ነገሩን ማደባበስና ቅጣት ፍትሕ አይደለም። በተመሳሳይ ሁኔታ ሌሎች ንጹኃን እንዳይሞቱ መከላከል ያሻል። ቦይንግ የሠራው ስህተት ያደረሰውን አስከፊ ጉዳት፣ የጎዳቸውን ቤተሰቦች መገንዘብ አለበት” ብሏል።
በዚህ የፍርድ ሂደት ምክንያት ቦይንግ ከአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስትር ጋር የገባው ስምምነት ዳግመኛ ይከፈት እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
እንዲህ ያለ ውሳኔ እምብዛም አልተለመደም።
በሌላ ክስ የሟቾችን ቤተሰቦች የሚወክለው ጠበቃ ሮበርት ኤ ክሊፎርድ እንደሚለው ግን፣ በግለሰቦች ላይ የሚወሰድ እርምጃን ጨምሮ ሌሎችም ውሳኔዎች ሊጠበቁ ይችላሉ።
“ቦይንግ ላይ ከፍተኛው ቅጣት እንዲጣል ነው ቤተሰቦቹ የሚፈልጉት። የቦይንግ ከፍተኛ አመራሮች ያለመከሰስ መብት እንዲነሳም ይፈልጋሉ” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለደረሰው አደጋ መንስኤው የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ችግር መሆኑን የኢትዮጵያ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር በያዝነው ዓመት ታኅሣሥ ላይ መግለጹ ይታወሳል።












