ቦይንግ 737 ማክስ፡ የተጎጂ ቤተሰቦች አሜሪካ 'ቦይንግ ከወንጀል ክስ ራሱን የሚከላከልበትን ስምምነት አዘጋጅታለች' ሲሉ ከሰሱ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ኢቲ302 ተከስክሶ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ኢቲ302 ተከስክሶ የ157 ሰዎች ሕይወት አልፏል

አወዛጋቢ በሆነው የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦች በአሜሪካ መንግሥት ላይ ሕጋዊ ጥያቄ አቀረቡ።

እነዚህ የተጎጂ ቤተሰቦች ዋሽንግተን የአውሮፕላን አምራቹ ኩባንያ ቦይንግ ራሱን ከወንጀል ክስ የመከላከል ዋስትና እንዲያገኝ የሚያስችለውን ስምምነት በምስጢር አዘጋጅታለች ሲሉ ከስሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ302 የሆነው አውሮፕላን ከሁለት ዓመታት በፊት መጋቢት ወር ላይ ከአዲስ አበባ በተነሳ በደቂቃዎች ውስጥ ነበር ተከስክሶ የሁሉም ተጓዦች ሕይወት ያለፈው።

ይህ የቦይንግ ዘመናዊና አዲስ ዲዛይን በሆነው 737 ማክስ አውሮፕላን ያጋጠመ ሁለተኛው አደጋ ነበር። የመጀመሪያው ኢንዶኔዢያ ውስጥ ባሕር ላይ ተከስክሶ መንገደኞቹ አልቀዋል።

በሁለቱ አደጋዎች በአጠቃላይ 346 ሰዎች የሞቱ ሲሆን አደጋዎቹን ያስከተለው የተሳሳተ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር እንደሆነ በኋላ ላይ ተረጋግጧል።

እስካሁን ግን ከአደጋው ጋር በተያያዘ የወንጀል ክስ የተመሰረተበት የቀድሞው የቦይንግ ዋና የቴክኒክ አብራሪ ማርክ ፎርክነር ብቻ ነው።

አብራሪው ክስ የቀረበበት ስለበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌሩ ሆነ ብሎ መረጃ በመደበቅ የአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት ተቆጣጣሪ የሆነውን የፌደራል አቪየሽን ባለሥልጣንን በማጭበርበር ነው።

በአደጋው ተጎጂ ቤተሰቦች በቴክሳስ ወረዳ ፍርድ ቤት ያቀረቡት አቤቱታ የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት በድርጅቱ ላይ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን በመደበቅ እና ለኢቲ302 ተጎጂ ቤተሰቦችን ምንም ዓይነት ምርመራ አለመኖሩን በመካድ ነው።

በተመሳሳይ መልኩ ምርመራውን ለማርገብ ከቦይንግ ጋር በመስራታቸው ነው የተጎጂ ቤተሰቦች ክስ ያቀረቡት።

ባለፈው ጥር ወር አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ሥራ ከመጀመሩ ከቀናት በፊት ነበር ቦይንግ ከወንጀል ክስ ራሱን የመከላከል ዋስትና እንዲያገኝ የሚያስችለው ስምምነት የወጣው።

በግዙፉ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተሰቦች 2.5 ቢሊየን ዶላር ቅጣትና ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።

በዚያን ጊዜ የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ "የቦይንግ ሠራተኞች የ737 ማክስ አውሮፕላን አሠራርን በሚመለከት ቁሳዊ መረጃን ከአሜሪካ ሲቪል አቪየሽ በመደበቅ እና በማታለል ለመሸፈን ጥረት በማድረግ ከቅንነት ይልቅ የትርፍ መንገድን መርጠዋል" ብሏል።

የተጎጂዎቹ ቤተሰቦች ጠበቆች የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ በስምምነቱ ላይ በመደራደርና ቦይንግን ወክሎ የመደራደር ኃላፊነት ያለውን የሕግ ድርጅት በመቀላቀሉ ተጠያቂ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የተጎጂ ቤተሰቦች ፍርድ ቤቱ የቦይንግን ያለመከሰስ መብት እንዲሰርዝ ጠይቀዋል።

ቦይንግ በዚህ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።