ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕገ ወጥ ስደተኞች ለመቆጣጠር ደቡብ አፍሪካ አዲስ የድንበር ጥበቃ ኃይል አቋቋመች
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የአገራቸውን ድንበር ደኅንነት ጥበቃን ለማጠናከር አዲስ ወሰን ቁጥጥር ኃይል ይፋ አደረጉ።
የጥበቃ ኃይሉ ሥራ መጀመሩ ይፋ የደረገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ በሚደረግበት እና ደቡብ አፍሪካ ከዚምባብዌ ጋር በምትዋሰንበት ሙሲና ከተማ ነው።
በምርቃቱ ላይ ፕሬዝዳንቱ ሰንድ የሌላቸው የውጪ አገራት ዜጎች የደቡብ አፍሪካን ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮችን እያባባሱ መሆናቸውን ተናግዋል።
የስደተኞች ጉዳይ በደቡብ አፍሪካ አሳሳቢ ከሚባሉ የፖለቲካ ጉዳዮች አንዱ ነው።
ወደ ደቡብ አፍሪካ በተለይም ከሰሀራ በታች ካሉ አገራት የሚመጡ ሰዎችን ቁጥር እንዲቆታጠር መንግሥት ላይ ጫና የበረታ ሲሆን፣ ድንብሩንም በተቀናጅ መንገድ አልጠበቀም በሚል ይወቀሳል።
በዚህ ምክንያት ቅሬታ የገባቸው ደቡብ አፍሪካውያንን ድጋፍ ለማግኘት መጤ ጠል ፓርቲዎች በቀጣዩ ዓመት ለሚካሄደው ምርጫ ዘመቻቸውን አጠናክረው እያካሄዱ ነው።
አዲሱ የድንበር ጥበቃ ኃይል እስኪቋቋም ድረስ የደቡብ አፍሪካ ድንበሮች የሚጠበቁት በአራት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አማካኝነት ነበር።
ሆኖም አሁን በሚሊዮን ዶላሮች የወጪ ተቋቋመው የደንብር ዘብን የሚያስተዳድረው ባለሥልጣን ከአገሪቱ የመከላከያ ኃይል እና ፖሊስ በመቀጠል ሦስተኛው የፀጥታ አስከባሪ ተቋም ይሆናል።
ከዚህ ዘብ መቋቋም በኋላ የደቡብ አፍሪካ ድንበሮች በተቀናጀ አንድ የአስተዳደር ተቋም ስር በሚኖር ዕዝ እና ቁጥጥር ስር ይሆናል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለዚህ ዘብ የተመለመሉ ሲሆን፣ ከአገሪቱ የመከላከያ ጦር ጋር በቅንጅት ይሰራል ተብሏል።
አዲሱ ዘብ የደቡብ አፍሪካን 8 የባሕርና 52 የየብስ ድንብር መተላለፊያዎችን እንዲሁም 11 ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች ያስተዳድራል።
ከምርቃቱ ቀደም ብሎ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ጋር ውይይት ያደረጉት የዚምባቤዌው ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ታድመው ነበር።
ራማፎሳ አዲሱ የድንብር አስተዳደር ባለሥልጣን ሕገወጥ ስደትን እና የሰዎች ዝውውርን በመግታት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናን ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል።
በሌላ በኩል በበርካታ ሚሊዮን ዶላሮች በደቡብ አፍሪካ እና ዚምባብዌ የተገነባው የኤሌክትሪክ አጥር መፍረሱ ሕገወጥ ዝውውርን የመቆጣጠር ሥራውን አስቸጋሪ አደርጎታል ተብሏል።
በርካታ የሕግ አስከባሪ አባላት ደግሞ ከስደተኞች ጉቦ በመጠየቅ ታስረዋል።
ደቡብ አፍሪካ ባለፈው ዓመት የሕዝብ ቆጠራ ያካሄደች ሲሆን፣ ውጤቱ በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በአወሮፓውያኑ 2011 የተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ሰንድ የሌላቸውን ጨምሮ 3.96 ሚሊዮን የውጭ አገር ዜጎች በደቡብ አፍሪካ እንሚኖሩ ያመለከተ ሲሆን ይህም ከጠቅላላው የአገሪቱ ሕዝብ 6 በመቶ የሚሸፍን ነው።
መንግሥት ድንብር አካባቢ ሰንድ የሌላቸውን ሰዎች በመቆጣጠር ደካማ እንደሆነ የሚጠቀስ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት የስደተኞች ቁጥር ከተጠቀሰው እጅግ ከፍ ያለ እንደሆነ የሚያምኑ በርካቶች ናቸው።
ፀረ ስደተኛ ንቅናቄን በይፋ እንደሚያራምዱት ዶዱላ የተባለው አይነት ፓርቲዎች እና ተቋማት ደግሞ ሕገ ወጥ ስደት በአገሪቱ ለተንሰራፋው ከፍተኛ ወንጀል አስተዋጽኦ አለው ሲሉ ይከሳሉ።
በደቡብ አፍሪካ ያለው የፀረ ስደተኞች እንቅስቃሴ በጥቃት፣ በጥላቻ እና በሐሰተኛ መረጃ የተሞላ ነው።
ሥራ አጥ ደቡብ አፍሪካውያን ሥራቸው ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት በመጡ ሰነድ አልባ ስደተኞች እንደተወሰደባቸው እንዲያምኑ ይነገራቸዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዘመቻ ዶዱል የተባለው እንቅስቃሴ በፈጠረው ጫና በደቡብ አፍሪካዋ ሱዌቶ በሌላ አገር ዜጎች የሚተዳደሩ እና የተያዙ ሱቆች ተዘግተዋል።
ይህ የሆነው ሁለት ሕጻናት መንደር ውስጥ ከሚገኝ ሱቅ ብሰኩት ገዝተው ከበሉ በኋላ መሞታቸውን ተከትሎ ነው።