በአትላንቲክ ባሕር ላይ የስደተኞች ጀልባ ሰጥማ ቢያንስ 30 ሰዎች ሳይሞቱ አይቀርም ተባለ

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አውሮፓ ለመድረስ አደገኛውን የባሕር ላይ ጉዞ ያደርጋሉ።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አውሮፓ ለመድረስ አደገኛውን የባሕር ላይ ጉዞ ያደርጋሉ።

በአትላንቲክ ባሕር ላይ ስደተኞች ሲጓዙባት የነበረች ጀልባ ሰጥማ ከ30 የማያንሱ ስደተኞች መሞታቸውን ሁለት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ገለጹ።

ዎልኪንግ ቦርደርስ እና አላርም ፎን የተባሉት ተቋማት በካናሪ ደሴቶች አቅራቢያ አትላንቲክ ባሕር ላይ ስትጓዝ የነበረችው ጀልባ 60 ስደተኞችን ጭና ነበር ብለዋል።

የስፔን ባለስልጣናት በበኩላቸው በአካባቢው የነበሩ የእርዳታ ድርጅት ሰራተኖች የአንድ ሕጻን እና የአንድ የአዋቂ ሰው አስክሬን ማግኘታቸውን እንዲሁም 24 ሰዎችን መታደጋቸውን ገልጾ በጀልባዋ ላይ ስንት ሰዎች ተሳፍረው እንደሚገኙ አልታወቀም ብሏል።

ይህ አደጋ ያጋጠመው ከሳምንት በፊት በተመሳሳይ በርካታ ስደተኞችን የጫነች መርከብ በግሪክ ከሰጠመች በኋላ ነው። አውሮፓውያን አገራት ሆነ ብለው አደጋ ላይ ለሚገኝ የስደተኞች ጀልባ ድጋፍ አይሰጡም እየተባሉ ይተቻሉ።

ዎልኪንግ ቦርደርስ የተባለው ተቋም ባልደረባ የሆነችው ሄሌና ማሌኖ ጋርዞን 39 ሰዎች ሰጥመዋል ብላለች። እንደ ሄሌና ከሆነ ከእነዚህ መካከል አራት ሴቶች እና አንድ ጨቅላ ይገኝበታል።

አላርም ፎን የተባለው ድርጅት ደግሞ 35 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም ብሏል።

እነዚህ ድርጅቶች በጀልባ ላይ ተሳፍረው ከሚገኙ ወይም ከቤተሰቦቻቸው የሰልክ ጥሪን በመቀበል የስደተኞች እንቅስቃሴን በመከታተል ይታወቃሉ።

ጀልባዋ የሰጠመች ከትናንት በስቲያ ረቡዕ በምዕራብ አፍሪካ አቅጣጫ ግራና ካናሪያ ከተባለች ደሴት በደቡብ ምስራቅ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።

“ሴቶች እና ጨቅላ ሕጻንን ጨምሮ 60 ሰዎች ልትሰጥም በተቃረበች ጀልባ ላይ ሆነው እርዳታ እስኪያገኙ 12 ሰዓታትን ማስጠበቅ ከባድ ማሰቃየት ነው” ብላለች ሄሌና ጋርዞና።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በበኩሉ የስፔን መርከብ ችግር ከገጠማት የስደተኞች ጀልባ የነበረው ርቀት የአንድ ሰዓት ጉዞ ብቻ ነበር ሲል የሰፔን ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

የካናሪ ደሴቶች መሪ የሆኑት አንጅል ቪክተር ክስተቱን አሳዛኝ ብለው ገልጸው የአውሮፓ ኅብረት ስደተኞች አደጋ ላይ ሲወድቁ እርዳታ እና ድጋፍ መስጠት የሚያስችል ፖሊሲ መቅረጽ ይኖርበታል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ካናሪ ደሴቶች የሰፔን አካላት ሲሆኑ መነሻቸውን ምዕራብ አፍሪካ ያደረጉ ስደተኞች አውሮፓ ለመድረስ በደሴቶቹ አቅጣጫ ያልፋሉ።

ይህ የምዕራብ አፍሪካ-አትላንቲክ የስደተኞች መተላለፊያ መንገድ እጅግ አደገኛው ተደርጎ ይወሰዳል። እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሰደተኞች ድርጅት አሃዝ ከሆነ እአአ 2022 ብቻ በዚህ መስመር ሲጓዙ የነበሩ 543 ስደተኞች ሕይወታቸው አልፏል ወይም የደረሱበት አልታወቀም።

በዚህ አቅጣጫ የሚጓዙት መርከቦች መነሻቸው ብዙ ግዜ ከሞሮኮ፣ ማሊ፣ ሴኔጋል እና ኮት ዲቯር ያደረጉ ናቸው።