ከቀናት በፊት አልሞትኩም ብለው ሬሳ ሳጥን ያንኳኩት ኢኳዶሯዊት ‘የእውነት’ ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት ሊቀበሩ ሲሉ ሬሳ ሳጥን አንኳኩተው ሞትን ለጥቂት ያመለጡት የ76 ዓመቷ አዛውንት በድጋሚ ሬሳ ሳጥን ውስጥ ገብተዋል።
ሐዘንተኞችን ባስደነገጠ ሁኔታ አልሞትኩም ብለው ከሬሳ ሳጥን የወጡት እኚህ ሴት አሁን ሬሳ ሳጥን ውስጥ የተከተቱት መሞታቸው በሐኪም በማያሻማ ሁኔታ ከተረጋገጠ በኋላ ነው።
በኢኳዶር ባባሆዮ በምትባል ከተማ ነዋሪ የሆኑትና እማማ ቤላ ሞንቶያ በሚል ስም የሚታወቁት እኒህ ሴት ከሬሳ ሳጥን ከወጡ በኋላ መኖር የቻሉት ለጥቂት ቀናት ብቻ ነው።
በለቀስተኞች መሀል ‘ሞትን እምቢኝ ብለው የተነሱት የእማማ ቤላ ሞንቶያ ከተከተቱበት የሬሳ ሳጥን አንኳኩተው መውጣታቸው ታላቅ ዜና ሆኖ የነበረው ባለፈው ሳምነት ነበር።
ከሬሳ ሳጥኑ ከወጡ በኋላ ሆስፒታል በጽኑ ሕሙማን ክፍል የቆዩት ሴት ከሰባት ቀናት በኋላ በጨረፍታ ወደተመለከቱት ሞት ጠቅልለው ተመልሰዋል።
በዚህ ወቅት ሞታቸው በሐኪሞች ብቻ ሳይሆን በኢኳዶር ጤና ሚኒስቴር ጭምር ነው የተረጋገጠው።
የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴርም አሁን ሞታቸው 'የእውነት' ነው ብሏል።
የሟች ልጅ ጊልበርት ባርበራም ቢሆን ለአገሬው ጋዜጣ “አሁን እናቴ መሞቷ እርግጥ ነው፤ ከዚህ ኋላ ሕይወቴ እንደ ቀድሞው በፍጹም አይሆንም” ሲል በሐዘን ተናግሯል።
እማማ ቤላ ሞንቶያ በሚል ስም የሚታወቁት ሟች በፈረንጆቹ ሰኔ 16 ቀን ከሬሳ ሳጥን ከወጡ በኋላ በተደረገላቸው ምርመራ ያጋጠማቸው ነገር ምንድን ነበር የሚል ምርመራ ተደርጎ ነበር።
ሐኪሞች 'ካታለፕሲ' የሚሉት እክል እንደሆነ ነው የደረሱበት።
'ካታሌፕሲ' ሰዎች ራሳቸውን የሚስቱበትና ሰውነታቸው የሚደርቅበት የጤና እክል ነው።
የኚህን ሴት ከሬሳ ሳጥን መውጣትን ተከትሎ በኢኳዶር የተቋቋመው ልዩ የሐኪሞች አጣሪ ግብረ ኃይል ነው ይህን ያረጋገጠው።
ሟች በሰኔ 1/2015 ዓ.ም. ሞተዋል ተብለው ሬሳ ሳጥን ውስጥ የቆዩት ለአምስት ሰዓታት ብቻ ነበር።
እማማ ቤላ ሞንቶያ ትንፋሽ ፍለጋ ሲንፈራገጡ እና ቀባሪዎች ሳጥኑን ሲከፍቱ አንድ የሆነበት አጋጣሚ የተፈጠረው በአጋጣሚ ሲሆን ቀባሪዎቹ ‘እኛ ሬሳ ሳጥኑን የከፈትነው ልብስ ልንቀይርላቸው እንጂ ድምጽ ሰምተን አልነበረም’ ሲሉ ተናግረው ነበር።
ክስተቱን ተከትሎ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ደርሰው ሴትዬዋን ወደነበሩበት ሆስፒታል ወስደዋቸው ለቀስተኛውም ጉድ እያለ ተበትኖ ነበር።
ሞተዋል ተብለው ወደ ሕይወት ሲመለሱ እማማ ቤላ ሞንቶያ የመጀመርያዋ አይደሉም።
ከዚህ ቀደም በየካቲት ወር በአሜሪካ የ82 ዓመት አዛውንት እንዲሁ ከዚህ ዓለም በድካም አረፉ ተብሎ ከታወጀ በኋላ ከአስክሬን ክፍል ከሦስት ሰዓት በኋላ እስትንፋሳቸው ተሰምቶ ነበር።












