የሽብር ወንጀል ተከሳሾች የፍርድ ቤት ክርክር ታግዶ እንዲቆይ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታዘዘ

ገነት አስማማው፣ ዳዊት በጋሻው እና መስከረም አበራ።
የምስሉ መግለጫ, በቁጥጥር ስር ከሚገኙት 23 ተከሳሾች መካከል የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ የሆኑት ገነት አስማማው፣ ዳዊት በጋሻው እና መስከረም አበራ ይገኙበታል።

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እተካሄደ የሚገኘው የ23 የሽብር ወንጀል ተከሳሾች የክርክር ሂደት ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ “ባለበት ሁኔታ እንዲቆይ” ትዕዛዝ ተሰጠ።

ትዕዛዙን ትላንት ሰኞ ህዳር 24፤ 2016 ዓ.ም የሰጠው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ይግባኝ ችሎት ነው።

ለትዕዛዙ መነሻ የሆነው ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ነው። ቢቢሲ የተመለከተው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ሳምንት ሰኞ ህዳር 17፤ 2016 ዓ.ም የይግባኝ አቤቱታ ማስገባቱን ይገልጻል።

ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ የጠየቀው ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተላለፈ ትዕዛዝ ላይ ነው። ከአንድ ወር ገደማ በፊት የተላለፈው ትዕዛዝ በተመሳስይ መዝገብ ክሰ ተመስርቶባቸው ያልተያዙ ተከሳሾችን ይመለከታል።

በዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ ስም በሚጠራው መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው ግለሰቦች 51 ቢሆኑም፤ በፖሊስ ተይዘው ክሳቸውን በአካል እየተከታተሉ የሚገኙት ግን 23 ተከሳሾች ብቻ ናቸው። ቀሪ ተከሳሾችን በተመለከተ የፌደራል ፖሊስ “አማራ ክልል ካለው የጸጥታ ችግር አንጻር የተቀሩትን ተከሳሾች ለማቅረብ እንደማይችል ለፍርድ ቤቱ መግለጡን” የተከሳሾች ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም የከፍተኛው ፍርድ ቤት፤ “ከጸጥታው ችግር አንጻር ሊመጡ የማይችሉ ከሆነ እንዲቀርቡ በሌላ አይነት መንገድ ማስታወቂያ ማስነገር እና ጥሪ ማድር አያስፈልግም” የሚል አቋም መያዙን ጠበቃ ሄኖክ አክለዋል።

በመሆኑም በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸውን 28 ተከሳሾች በተመለከተ ፍርድ ቤቱ፤ “[ክሳቸው] በተገኙ ጊዜ የሚንቀሳቀስ ሆኖ ለጊዜው ተቋርጧል” የሚል ትዕዛዝ ሰጥቷል። ዐቃቤ ሕግ በዚህ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ቅር በመሰኘት ነው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኙን ያቀረበው።

ዐቃቤ ሕግ በይግባኙ፤ “የቀረቡ እና ያልቀረቡ ተከሳሾች ጉዳይ ተነጣጥሎ መታየቱ በዋናው ክርክር ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ይግባኙ ታይቶ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ በስር ፍርድ ቤት እየተካሄደ ያለው ክርክር ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ እንዲሰጥልን” ሲል ጠይቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ይህን የዐቃቤ ሕግ ጥያቄ በመቀበል በስር ፍርድ ቤት እየተካሄደ ያለው የክርክር ሂደት ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ይህ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 25፤ 2016 ዓ.ም ረፋድ ላይ በነበረው የስር ፍርድ ቤት የችሎት ውሎ በዐቃቤ ሕግ በኩል ለፍርድ ቤቱ እና ለተከሳሾች ቀርቧል።

በቃሊቲ እና በቂሊንጦ ማረሚያ ቤቶች ከሚገኙት 23 ተከሳሾች መካከል የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎቹ መስከረም አበራ፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ ዳዊት በጋሻው እና ገነት አስማማው ይገኙበታል።

ተከሳሾችን ወክለው ችሎት ፊት የቀረቡት ጠበቆች፤ “ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያለው ጉዳይ ባለበት እንዲቆይ ስለተባለ እና ተከሳሾችን በተመለከተ ምንም ነገር ስላልተባለ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን ሊያሰናብታቸው ይገባል” ማለታቸውን ጠበቃ ሄኖክ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በተጨማሪም “የጠቅላይ ፍርድ ቤት በእስር ላይ ይቆዩ ስላላለ ሕጉ በሚለው መሰረት ከማረሚያ ቤት ሊፈቱ ይገባል” የሚል መከረከሪያ በጠበቆች በኩል መነሳቱን ጠበቃ ሄኖክ ገልጸዋል።

ዐቃቤ በበከሉ ጠበቆች ፍርድ ቤቱ ደንበኞቻቸውን እንዲያሰናብታቸው ያቀረቡትን ጥያቄ መቃወሙን ጠበቃ ሄኖክ ተናግረዋል። ዐቃቤ ሕግ ተቃውሞውን ሲያሰማ “የጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከሳሾችን በተመለከተ በማረሚያ ቤት ይቆዩ ባይልም ነገር ግን ‘አጭር ቀጠሮ ሰጥተናል’ የሚለው [በማረሚያ ቤት] እንዲቆዩ የሚያመላከት ነው” የሚል ሙግት ማቅረቡን ጠበቃው ገልጸዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ላይ ቅሬታቸውን ያሰሙት ግን የተከሳሾች ጠበቆች ብቻ አልነበሩም። ተከሳሾችም ራሳቸው “ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ” ለችሎቱ ማሰማታቸውን ጠበቃቸው አውስተዋል።

ተከሳሾች የጠቅላይ ፍርድ ቤት ትዕዛዝን ከመቃወም ባለፈ፤ “ ‘የሚያስረንም፥ የሚፈታንም፥ የሚፈርድብንም ፖለቲካው ነው ይሄ ፍርድ ቤት አይደለም” በሚል ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን ማሰማታቸውን ጠበቃ ሄኖክ ገልጸዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ከፍተኛው ፍርድ ቤት የጠቅላይ ፍርድ ቤትን የክርክር ውጤት ለመጠባበቅ ለታህሳስ 15 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አራት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተካተቱበት የክስ መዝገብ ዐቃቤ ሕግ ክሱን የመሰረተው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነበር። ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾች ፈጽመውታል ባለው የወንጀል ድርጊት 217 ሰዎች ላይ የሞት፣ 297 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው በክሱ ዝርዝር ላይ አስፍሯል።

ዐቃቤ ሕግ በሰው ላይ ደረሰ ካለው የሞት እና የአካል ጉዳት በተጨማሪ 1.29 ቢሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ወድመት መድረሱንም በክሱ ላይ አካትቶ አቅርቧል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ህዳር 12፤ 2016 ዓ.ም በነበረው የችሎት ውሎ ዐቃቤ ሕግ ተፈጸመ ባለው የወንጀል ድርጊት የደረሰውን የጉዳት መጠን በዝርዝር በማካተት ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ በፍርድ ቤት መታዘዙ ይታወሳል።