በጋምቤላ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ185 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ተመድ አስታወቀ

በጋምቤላ ክልል የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ቢያንስ 185 ሺህ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።
የክልሉ መዲናን ጨምሮ 12 ወረዳዎች ላይ ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ ባለው ወቅት ከባድ ዝናብ መዝነቡን የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) አስታውቋል።
በዚህም 185 ሺህ 200 ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ያስተወቀው ተቋሙ በፈታኝ ሁኔታም ውስጥ ይገኛሉ ብሏል።
በአሁኑ ወቅት በተጨናነቀ ሁኔታ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት ላይ ተጠልለው እንዲሁም ውጭ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የምግብ እጥረት የተከሰተ ሲሆን ተፈናቃዮቹ በህይወት ለመቆየት ቅጠሎች እና ስሮች እየተመገቡ ነው ብሏል።
በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በአማካኝ በክልሉ ያለው 72 በመቶ ሰብል በአብዛኛው የበቆሎ ተክል መጎዳቱን እንዲሁም የእርባታ ዶሮዎችና የቀንድ ከብቶች መሞታቸውን አትቷል።
ተመድ የጎርፍ አደጋው የነዋሪዎችን ንብረት እንዳወደመና መሰረተ ልማቶችም እንደተጎዱ ጠቅሷል።
በአካባቢው የከፋ ሁኔታ መግጠሙን ያስታወቀው የተመድ ሪፖርት የጎርፍ አደጋው የውሃ አቅርቦቱን እንዳስተጓጎለውና መተላለፊያ መስመሮቹም ተበላሽተዋል ብሏል።
በአስራ ሁለቱ ወረዳዎች በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከ77 ያላነሱ የጤና ተቋማት ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ነዋሪው የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል ብሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በፈጠረው የጤና እክል በውሃ ወለድ በሽታዎች የመያዝ እድሉን ከፍ አድርጎታል።
በተጨማሪም ጊዜያዊ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፖቹ በመጨናነቃቸው ምክንያት የእከክ፣ የኩፍኝ እና የመተንፈሻ አካላት ህመሞች የመከሰታቸውን ስጋት ጨምሮታል።
የጋምቤላ ክልል ሰፊው አካባቢ ወንዞች የሚያልፉበት ሲሆን ለድንገተኛ የጎርፍ አደጋም ተጋላጭ ናቸው።
በአካባቢው ካሉት ዋና ዋናዎቹ ወንዞች መካከል አኮቦ፣ ኦልዎሮ፣ ባሮ (ኦፔኖ) እና ጊሎና ገባር ወንዞች ይገኙበታል። እነዚህ ወንዞች አብዛኛውን ጊዜ በክረምትና ከባድ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ከአፍ ገደፋቸው በመሙላት ባለፈ አካባቢውን በማጥለቅለቅ የአካባቢውን ማህበረሰብ ህይወት በመቅጠፍና የንብረት መውደም ያደርሳሉ።












