በኢራን በጎዳና ላይ ሲደንሱ የታዩት ጥንዶች የ10 ዓመት እስር ተፈረደባቸው

ጥንዶቹ ሲደንሱ የሚያሳይ ምስል

በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ኢራናዊያን ጥንዶች በጎዳና ላይ ሲደንሱ የሚያሳይ ቪዲዮ ካጋሩ በኋላ የ10 ዓመት እስር ተፈረደባቸው።

ጥንዶቹ ፍርዱ የተላለፈባቸው ሙስናን፣ ዝሙትን እና ፕሮፖጋንዳን አስተዋውቀዋል በሚል ነው።

ቪዲዮው ጥንዶቹ የቴህራን ምልክት በሆነው አደባባይ አዛዲ ታዎር ወይም የነጻነት ታወር አካባቢ ሲደንሱ ያሳያል።

በኢራን አንዲት ሴት ሒጃብሽን በትክክል አልበስሽም በሚል ተይዛ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለች መሞቷን ተከትሎ ባለሥልጣናት በተቃውሞ በሚሳተፉ ሰዎች ላይ ከባድ ውሳኔዎችን እያስተላለፉ ነው።

ይሁን እንጂ እነዚህ ጥንዶቹ ሲደንሱ የሚያሳየውን ቪዲዮ በአገሪቷ እየተካሄደ ካለው ተቃውሞ ጋር አላያያዙትም።

ምንጮች ለቢቢሲ ሞኒተሪንግ እንዳረጋገጡት ጥንዶቹ የታሰሩት ሁለት ሚሊየን የሚጠጉ ተከታዮች ባለው የኢንስታግራም ገጻቸው ቪዲዮውን ከለጠፉ በኋላ ነው።

ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ የ22 ዓመቷ ማህሻ አሚኒ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለች ሕይወቷ ካለፈ በኋላ የተቀሰቀሰው እና መንግሥት “ አብዮት” ያለው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ በመላ አገሪቷ ተስፋፍቷል።

ማህሻ በቴህራን በቁጥጥር ሥር የዋለችው ሴቶች ፀጉራቸውን በሂጃብ ወይም በስካርፍ እንዲሸፍኑ የሚያዘውን ሕግ ጥሳለች በሚል ነበር።

አስር ዓመታት በእስር እንዲያሳልፉ የተፈረደባቸው የ21 ዓመቷ አስቲያዝ ሃቂቂ እና እጮኛዋ አሚር መሐመድ አህማዲ ውሳኔው የተበየነባቸው በብሔራዊ ደህንነት ላይ በመመሳጠር እና በተቋሙ ላይ ፕሮፖጋንዳ በመስራት ሙስናን እና ዝሙት አስተዋውቀዋል በሚል ነው።

የሃቂቂ ቤተሰቦች፣ ሃቂቂ በሙያዋ የፋሽን ዲዛይነር እንደሆነች ገልጸው፣ በቁጥጥር ሥር ከመዋሏ በፊት ከበባ ተፈፅሞባት እንደነበር ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ እስካሁን ጥንዶቹ እያንዳንዳቸው የስንት ዓመት እስር እንደተፈረደባቸው ግልጽ አይደለም።

ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ጥንዶቹ ለሁለት ዓመት ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ እና ከአገር እንዳይወጡ ታግደዋል።

በኢራን የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ የቴህራን መንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጣበት እንደ አውሮፓውያኑ 1979 አብዮት በኋላ ትልቅ ፈተና ሆኖበታል።

ተቃውሞውን ለማስቆምም መንግሥት በተቃውሞ ላይ የተሳተፉ አራት ሰዎች በሞት እንዲቀጡ ማድረግን ጨምሮ ከባድ ቅጣት እያስተላለፈ ነው።

ለዚህ ተቃውሞ በመላ አገሪቷ መቀጣጠል የማሂሳ አሚኒ ሞት ምክንያት ቢሆንም ለረዥም ጊዜ በቆየ ድህነት ፣ የሥራ እጦት፣ እኩልነት አለመኖር፣ ኢፍትሃዊነት እና ሙስና መንስኤ ሆኗል።

ይህ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለእስር ተዳርገዋል።