ኢራን በስለላ የከሰሰቻቸውን የቀድሞ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሯን በሞት ቀጣች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኢራን ውስጥ የሞት ፍርድ የተበየነባቸው የብሪታኒያ እና የኢራን ጥምር ዜግነት የነበራቸው አሊሬዛ አክባሪ መገደላቸውን የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
ባለፈው ረቡዕ የአክባሪ ቤተሰቦች “ለመጨረሻ ጉብኝት” ወደ እስር ቤት ሄደው እንዲጠይቋቸው ተነግሯቸው እንደነበር እና አክባሪ ለብቻቸው ታስረው እንደቆዩ ሚስታቸው ገልጸው ነበር።
የቀድሞው የኢራን ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር አሊሬዛ አክባሪ የታሰሩት ከሦስት ዓመት በፊት ነበር። እሳቸው ቢያስተባብሉም ለዩናይትድ ኪንግደም በመሰለል ተከሰው ሞት ተፈርዶባቸዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ኢራን በአሊሬዛ አክባሪ ላይ ልትፈጽም ያቀደችውን የሞት ፍርድ በመተው በአስቸኳይ ግለሰቡን እንድትለቅ ስትጠይቅ ቆይታለች።
አርብ ዕለት የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ጄምስ ክሌቨርሊ “ኢራን ጭካኔ በተሞላበት የግድያ ማስፈራሪያዋ መቀጠል የለባትም” ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።
ባለፈው ረቡዕ ክሌቨርሊ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሉት “ይህ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የሚወሰድ ኋላቀር የጭካኔ ቅጣት ነው፤ ኢራን ሰብአዊ መብት ግድ አይሰጣትም” ሲሉ ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረው ነበር።
በዚህ ሳምንት በግዳጅ በሚመስል ሁኔታ አሊሬዛ አክባሪ የተከሰሱበትን ጥፋት ሲያምኑ የሚያሳይ ቪዲዮ ኢራን ይፋ አድርጋለች።
ነገር ግን የቢቢሲ ፐርሺያ ቋንቋ አገልግሎት በቅርቡ ከእስር ቤት ሾልኮ የወጣ የአሊሬዛ አክባሪ የድምጽ ቅጂን ለሕዝብ አቅርቦ ነበር።
በዚህ መልዕክታቸው ፍርደኛው ከፍተኛ ግርፋት እና ድብደባ እንደደረሰባቸው እንዲሁም ለዩናይትድ ኪንግደም ሲሰልሉ እንደነበረ በግድ እንዲያምኑ መደረጋቸውን አብራርተዋል።
ከዩናይትድ ኪንግደም በተጨማሪ አሜሪካ፣ ኢራን በአክባሪ ላይ ግድያውን እንዳትፈጽም በዲፕሎማቷ ቬዳንት ፓቴል በኩል ጠይቃ ነበር።
ፓቴል ትናንት አርብ እንዳሉት “በአሊሪዛ አክባሪ ላይ የቀረቡት ክሶች እና የሞት ቅጣቱ ፖለቲካዊ ናቸው” በማለት ተቃውመውታል።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ በዚህ ሳምንት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ መንግሥታቸው ለአክባሪ ቤተሰብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን እና በጉዳዩ ላይ ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር በተደጋጋሚ እየተናጋገረ መሆኑን ገልጸው ነበር።
ዩኬ ለእስረኛው አስቸኳይ የማማከር ድጋፍ ለመስጠት ጥያቄ ብታቀርብም፣ ኢራን ዜጎቿ ጥምር ዜግነት እንዲኖራቸው ስለማትፈቅድ ጥያቄው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢራን ጥምር ዜግነት እና በሌላ አገር ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውን ዜጎቿን በስለላ እና በብሔራዊ ደኅንት ስጋትነት በቁጥጥር ስር አውላለች።
የብሪታኒያ ዜጋ የሆኑት ኢራናውያኑ ናዛኒን ዛጋሪ-ራትክሊፍ እና አኑሼህ አሹሪ በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ ዩናይትድ ኪንግደም ለኢራን መክፈል የነበረባትን እዳ ከዘጋች በኋላ ግለሰቦቹ ተለቀው ከኢራን እንዲወጡ ተፈቅዶላቸዋል።
አሁንም ቢያንስ ሁለት ትውልደ ኢራናዊ የሆኑ የብሪታኒያ ዜጎች በአስር ላይ ይገኛሉ። አንደኛው ሞራድ ታህባዚ ደግሞ የአሜሪካ ዜግነትም እንዳለው ተነግሯል።












