ኢራን የብሪታኒያ ዜግነት ያላቸውን የቀድሞ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሯን በስቅላት ልትቀጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, twitter
ጥምር ዜግነት ያላቸውና ቀደም ሲል የኢራን ምክትል መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ግለሰብ በስቅላት ሊቀጡ ነው።
አሊሬዛ አክባሪ የተባሉት እኚህ የብሪታኒያ እና የኢራን ጥምር ዜግነት ያላቸው ሰው በስቅላት ሊቀጡ እንደሆነ የገለጹት ቤተሰቦቻቸው ናቸው።
የግለሰቡ ባለቤት ማሪያም ለቢቢሲ ፐርሺያ እንደተናገሩት ቤተሰቡ የመጨረሻ ስንብት እንዲያደርግ ተነግሯቸዋል።
“ቶሎ ብላችሁ ተሰናበቱት፣ ሞቱን ወደሚጠብቅበት የብቻ ክፍል ሊወሰድ ነው ተብለናል” ብለዋል ማሪያም።
የቀድሞው የኢራን ምክትል መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አሊሬዛ አክባሪ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በ2019 ነበር።
የታሰሩት ለዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ሲሰልሉ ነበር በሚል ነው።
ዩኬ ኢራን ግልሰቡን በስቅላት እንዳትቀጣ፣ ይልቁንም በአፋጣኝ ከእስር እንድትፈታው ጠይቃለች።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄምስ ክሌቨርሊ እንዳሉት ይህ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የሚወሰድ ኋላቀር የጭካኔ ቅጣት ነው፤ ኢራን ሰብአዊ መብት ግድ አይሰጣትም” ሲሉ ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረዋል።
የዩኬ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከዚህ ቀደም ዜጋዬ ነው ለምትላቸው አሊሬዛ አክራባሪን ከእስር ለማስፈታት ከኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ገልጾ ነበር።
የዩኬ ኤምባሲም ግለሰቡን ለመጎብኘት እንዲፈቀድለት ጥያቄ ቀርቧል።
ይሁንና ኢራን ዜጎቼ የምትላቸውን ሰዎች ጥምር ዜግነት አትቀበልም።
ቢቢሲ ፐርሺያ በቅርቡ ከእስር ቤት ሾልኮ የወጣ የአሊሬዛ አክባሪ የድምጽ ቅጂ ለሕዝብ አስተላልፎ ነበር።
በዚህ መልዕክታቸው ፍርደኛው ከፍተኛ ግርፋት እና ድብደባ እንደደረሰባቸው እንዲሁም ለዩናይትድ ኪንግደም ሲሰልሉ እንደነበረ በግድ እንዲያምኑ መደረጋቸውን አብራርተዋል።
ውጭ አገር ኑሮ በጀመርኩበት ወቅት ወደ ኢራን እንድመጣ በአንድ ከፍተኛ የኢራን የኑክሊየር ተደራዳሪ በኩል ተጋብዤ ነው ወደ ኢራን የተመለስኩ ብለዋል አክባሪ።
ለ10 ወራት በእስር ቤት ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸውና ለ3 ሺህ 500 ሰዓታት ምርመራ እንደተደረገባቸው የገለጹት አክባሪ፣ “ይህ ሁሉ ሲደረግ በካሜራ እየተቀረጽኩ ነበር። የሆሊውድ ፊልም የሚሰሩብኝ ነው የሚመስለው” ሲሉ ያሳለፉትን ስቃይ ሾልኮ በወጣው የድምጽ ቅጂ ተናግረዋል።
አክባሪ ኢራን እኔን በስቅላት በመቅጣት ዩናይትድ ኪንግደምን መበቀል ትፈልጋለች ብለዋል።
ኢራን በበኩሏ ግለሰቡ ከዩኬ የስለላ ድርጅት ኤም16 ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ሲሰራ ነበር ትላለች።
ኢራን ከቅርብ ወራት በፊት የማያባራ አመጽ ከተቀሰቀሰባት በኋላ የምዕራብ አገራት ቋሚ መኖርያ ያላቸውና ድርብ ዜግነት አለን የሚሉ በርካታ ሰዎችን አስራለች።
አሁን በስቅላት ሊቀጡ ይችላሉ የሚባሉት አክባሪ በፕሬዝዳንት መሐመድ ኻታሚ ዘመን የኢራን ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።












