ቭላድሚር ፑቲን ለዩክሬን ጦርነት ከሦስት ወር በፊት የሾሟቸውን ጄኔራል አንስተው አዲስ ተኩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን በዩክሬን ውስጥ የሚካሄደውን ዘመቻ እንዲመሩ አዲስ የጦር አዛዥ ሾሙ።
አዲሱ የጦር አዛዥ የተሾሙት ከሦስት ወራት በፊት ይኸው ሹመት ተሰጥቷቸው የነበሩትን ሰርጌይ ሱሮቪኪን በማንሳት ነው።
ጄኔራል ሰርጌይ ላለፉት ሦስት ወራት በዩክሬን ላይ ሲዘንቡ የነበሩ የሚሳኤል ጥቃቶችን በበላይነት የመሩ ናቸው።
ይሁንና በርካታ ሩሲያ ከዩክሬን የያዘቻቸው ቦታዎችን በማጣቷ በጦሩ ውስጥ ቅሬታ ሰፍኖ ነበር።
አሁን ፑቲን የሾሟቸው አዲሱ የጦር አዛዥ ጄኔራል ቫለሪ ጌራሲሞቭ ይባላሉ።
ጄኔራል ጌራሲሞቭ ከ2012 ጀምሮ የሩሲያ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ሆነው አገልግለዋል።
ይህ የከፍተኛ መኮንኖች ለውጥ የመጣው ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት በአዲስ መንፈስ ድል እየቀናኝ ነው ባለች ማግስት ነው።
በተለይም በምሥራቅ ዩክሬን ሩሲያ አዳዲስ ከተሞችን ለመያዝ ተቃርቢያለሁ ትላለች።
ሩሲያ በጎረቤቷ ዩክሬን ሙሉ ወረራን የከፈተችው ከዓመት በፊት በየካቲት 24/2022 ነበር።
ጄኔራል ጌራሲሞቭ ከ2012 ጀምሮ ጠቅላይ አዛዥ የነበሩ ሲሆን በሩሲያ ከሶቭየት ኅብረት መፍረስ ወዲህ ረዥም አገልግሎት የሰጡ ጄኔራል ናቸው።
አሁን ከቦታው የተነሱት ጄኔራል ሰርጌይ ሶሮቪኪን የጄኔራል ቫለሪ ምክትል ሆነው ይቀጥላሉ ተብሏል።
ጄኔራል ሰርጌይ በተለይ በሶሪያ ላይ በፈጸሙት የጭካኔ ተግባራት የተነሳ ‘ጄኔራል አርማጌዶን’ የሚል ቅጽል አላቸው።
በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት በተፋፋመበት ወቅት አሌፖ ከተማ በከፍተኛ ሁኔታ ቀን ተሌት የተደበደበችው በጄኔራል ሰርጌይ የበላይ አመራርነት ነበር።
ይህን ተመሳሳይ ስልት በዩክሬን ላይ ለመጠቀም የሞከሩት ጄኔራል ሰርጌይ በተለያዩ የዩክሬን ከተሞች ላይ የኃይል መሠረተ ልማቶችን ለይቶ በመምታት ሚሊዮኖችን ያለመብራት ጨለማ ውስጥ አስቅርተዋል።
በዚህም ሳቢያ በአሁኑ ወቅት በበርካታ የዩክሬን ከተሞች ውስጥ ውሃ እና የውርጭ ማሞቂያም ቅንጦት ሆኗል።
ጄኔራል ሰርጌይ ሩሲያ ከቁልፍ ከተማ ኼርሶን በሽንፈት ስትወጣም በኃላፊነት ላይ ነበሩ።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ሹም ሽሩን “በተለያዩ የጦሩ ክፍሎች የመቀራረብ መንፈስን እና ቅንጅትን ለማምጣት የተደረገ ነው” ሲል ገልጾታል።
ሩሲያ በምሥራቅ ዩክሬን በኩል ሶሌዳር ከተማን ከሰሞኑ በእጄ አስገብቻለሁ እያለች ነው።
ዩክሬን በበኩሏ ሶሌዳር ሙሉ በሙሉ በሩሲያ እጅ አልወደቀችም ብላለች።












