ከተለቀቁት እስራኤላውያን ታጋቾች መካከል የአራት ዓመት ህጻን እንዳለችበት ተገለጸ

 የ4 ዓመቷ አቪጌል ኢዳን

የፎቶው ባለመብት, Family Handout

የምስሉ መግለጫ, የ4 ዓመቷ አቪጌል ኢዳን

በሶስተኛው ዙር በሐማስ ከተለቀቁት ታጋቾች መካከል የአራት ዓመት እስራኤላዊ አሜሪካዊት ህጻን እንደምትገኝበት ተገለጸ።

በትናንትናው ዕለት ሐማስ 17 ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል ደግሞ በልውውጡ 39 ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።

በትናንትናው ዕለት ከተለቀቁትም 17ቱ ታጋቾች መካከል የ4 ዓመቷ አቪጌል ኢዳን ትገኝበታለች።

የሐማስ ታጣቂዎች መስከረም መጨረሻ ላይ ባደረሱት ጥቃት ከታገቱት መካከል አቪጌል አንዷ ናት።

ቤተሰቦቿም በጥቃቱ ተገድለዋል። በወቅቱም ሶስት ዓመቷን እያጠናቀቀችው የነበረችው ህጻን በእገታ ላይም እያለች ነው አራት ዓመት የሞላት።

“ይህች ቀን እንድትመጣ ተስፋችን ከፍ ያለ ነበር፤ ጸሎትም አድርገናል” ሲሉ የአቪጌል ቤተሰቦች ተናግረዋል።

“አቪጌል ደህና መሆኗን እና ቤት እንደምትመጣ ስናውቅ የተሰማንን እፎይታም ሆነ ምስጋና በቃላት ለመግለጽ ይከብዳል” ሲሉም የአቪጌል አክስት ሊዝ ሂርሽ ናፍታሊ እና የአክስት ልጅ ኖዋ ናፍታሊ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።

የህጻኗ ቤተሰብ በአቪጌል መለቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ላሏቸው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የኳታር መንግሥት እና ሌሎችም ምስጋናቸውን ገልጸዋል። ሌሎችም ታጋቾች እንዲለቀቁ ቤተሰቡ ጠይቀዋል።

“ግፊት በማድረግ መቀጠል አለብን። አሁንም በእገታ ላይ ካሉ ቤተሰቦች ጎን ነን። ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም እንዲመለሱም እንጠይቃለን” ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን አቪጌል “በአስከፊ ሁኔታም” ላይ ነበረች ሲሉ ያለፈችበትን መንገድ ማሰብ እንደሚከብድ ገልጸዋል። ፕሬዚዳንቱ ህጻኗ ፍቅር እና እንክብካቤም እንደሚጠብቃት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

“ዛሬ ነጻ ሆናለች። እኔ እና ጂሊ (ቀዳሚዊት እመቤት) ከአሜሪካ ህዝብ ጋር ሆነን ሰላም እንድትሆን እንጸልይላታለን” ሲሉም ፕሬዚዳንት ባይደን ተናግረዋል።

እሁድ ዕለት የነበረውን የታጋቾች መለቀቅ በከፍተኛ ሁኔታ በተደረገ የአሜሪካ ዲፕሎማሲ የተገኘ ስኬት መሆኑን ገልጸው በቀጣዮቹ ቀናትም አሜሪካዊ ታጋቾች እንደሚለቀቁ ያላቸውንም ተስፋ አጋርተዋል።

“ሌሎች አሜሪካውያን ታጋቾች እንዲለቀቁ መጠበቃችንን እንዲሁም ጫና ማድረጋችን እንቀጥላለን” ብለዋል።

አክለውም “ ሁሉም ታጋቾች ተመልሰው ከሚወዷቸው ቤተሰቦች ጋር እስኪገናኙ ድረስ ስራችንን አናቆምም” ብለዋል።

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰውን የአራት ቀናት የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ ሐማስ 58 ታጋቾችን በሶስት ዙሮች ለቋል። እስራኤል በበኩሏ 117 ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች። የተኩስ አቁም ፋታው በዛሬው ዕለት የሚጠናቀቅ ሲሆን ስለመራዘሙ የተባለ ነገር የለም።