በካሊፎርኒያ በሦስት ቀናት ውስጥ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ሰባት ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ ካሊፎርንያ ትላንት ሰኞ የታጠቀ አንድ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ ሰባት ሰዎችን ገድሏል። ይህ ከመሆኑ ሁለት ቀናት አስቀድሞ በተመሳሳይ ግዛት በታዋቂ የመዝናኛ አዳራሽ ሌላ ግለሰብ ተኩስ ከፍቶ የ11 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።
የትላንቱ ጥቃት ከሳን ፍራንሲስኮ ደቡባዊ ክፍል 50 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው እና በባሕር ዳርቻዋ ከተማ ሃፍ ሙን ቤይ ውስጥ በሁለት የተለያዩ ቦታዎች የተፈጸመ ነው።
ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ የ67 ዓመት ዕድሜ ያለውና ዛሆ ቹንሊ የተባለ የአከባቢው ነዋሪ ነው ተብሏል።
ይህ ጥቃት የተሰማው ግዛቱ ኤዢያን ሞንተሪ በተባለው መናፈሻ ውስጥ የእስያውያን አዲስ ዓመት እየተከበረ በነበረበት ወቅት ለሟቾች የሐዘን ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ሳለ ነበር።
ተጠርጣሪው ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሁለት ሰዓታት በኋላ ለሕግ አስከባሪዎች እጁን ሰጠ ሲሆን ይህንንም ሁነት መገናኛ ብዙኃን ሲቀርጹት ታይተዋል።
በጥቃቱ ሕይወታቸውን ያጡት የመጀመሪያዎቹ አራት ሰዎች አስክሬን በእንጉዳይ እርሻ ውስጥ ተገኝቷል። የተቀሩት ሦስት ሰዎች ደግሞ የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት በሚሰጠበት ስፍራ አቅራቢያ ተገኝቷል።
ተጠርጣሪው ጥቃቱን ለመፈጸም የተነሳሳበት ምክንያት እስካሁን ይፋ አልሆነም።
የሳን ማቲዎ ካውንቲ የሕግ አስከባሪ ሃላፊ ክርስቲና ኮርፐስ ተጠርጣሪው ራሱ እያሽከረከረ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከመጣ በኋላ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጸዋል።
ግለሰቡ ጥቃቱን ፈጽሞበት ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ከፊል አውቶማቲክ መሣሪያ የተገኝበት ሲሆን እጁን ሲሰጥ ግብግብ እንዳልፈጠረም ጨምረው ተናግረዋል።
ኃላፊዋ አክለውም የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ሌሎች 8 ሰዎች በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ እና ለሕይወት አስጊ በሆነ ሁኔታ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
“የጥቃቱ ዓይነት ዘግናኝ ነው። ይህንን ዓይነት ጥቃት ብዙ ጊዜ በጣም ከሩቅ ነበር የምንሰማው ዛሬ ግን ቤታችን ደርሷል” ሲሉም ገልጸዋል።
ኃላፊዋ ይህንን ክስተት ከትምህርት እረፍት ላይ የሚገኙና ወደ ገጠር የሄዱ ሕጻናትን ጨምሮ ሰዎች መመልከታቸውንም አንስተዋል።
“ሕጻናት ይህንን ክስተት መመልከታቻውን ለመናገር ያስቸግራል” ሲሉለም አክለዋል።
የካሊፎርኒያው ገዢ ጋቪን ኒውስዎም በትዊተር ገጻቸው “በተከፈተባቸው ተኩስ የተጎዱ ሰዎችን ሆስፒታል እየጎበኘሁ ባለሁበት ሰዓት ጉብኝቴ ተቋርጦ ሌላ ጥቃት መከፈቱ ተነገረኝ። በሃፍ ሙን ቤይ በአሳዛኝ ክስተት ላይ አሳዛኝ ክስተት ተደርቧል” ብለዋል።
የሃፍ ሙን ቤይ ምክር ቤት አባል ዴቢ ሩዶክ የጥቃቱ ሰለባዎች እርሻ ላይ የተሰማሩ ቻናውያን ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ጥቃቱ የተፈጸመው “በተበሰጨ ሠራተኛ” ሲሉ የካውንቲው ተቆጣጣሪ ቦርድ ፕሬዝዳንት ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።












