አምነስቲ የሰላም ስምምነቱ ለተጎጂዎች ፍትሕ መስጠት አለበት አለ

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በፌዴራል መንግሥቱ እና በህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ፍትሕ መስጠት አለበት አለ።

ተዋጊ አካላቱ በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ የአምንስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ኃላፊ ሙሌንያ ማዋያናዳ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ትክክለኛ እርምጃ ነው ብለዋል።

ሆኖም ስምምነቱ ተጠያዊነትን በተመለከተ ያለበትን ጉድለት ለመሙላት ተጫማሪ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ብለዋል።

በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት በጅምላ እና ከፍርድ ውጭ በሆነ ግድያ እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃትን ጭምሮ የሰብአዊ መበት ጥሰት መፈጸማቸውን ያስታወሱት ኃላፊዋ፤ የሰላም ስምምነቱ ግን ይህንን በቀላሉ የማይታለፍ ድርጊት የፈጸሙ አካላት የሚጠየቁበትን ሁኔታ በተመለከተ ያለው ነገር የለም ብለዋል።

የጦር ወንጀል እና ሰብዓዊነት ላይ ያነጣጠረ ወንጀል የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ስለሚሆኑበት ሁኔታ ግልጽ ዕቅድ የለውም ሲል አምንስቲ ኢንተርናሽናል ገልጿል።

“አሁን ላይ፣ ስምምነቱ ለተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች እና ሰብዓዊነት ላይ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነትን በተመለከተ ግልጽ ፍኖተ ካርታ አላስቀመጠም” ያሉት ሙሌንያ ማዋያናዳ ይህ አለመሆኑ መሰል ጥሰቶች በአገሪቱ እንዲደገሙ ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ኃላፊዋ ጨምረውም ጦርነቱን ተከትሎ ለተፈጸሙ አሰቃቂ ድርጊቶች ሰለባ ለሆኑ እና ለተጎጂዎች ፍትህን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራዎች ያለተገደበ ፍቃድ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።