ትራምፕ ዓለም አቀፉ የጦር የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ማዕቀብ ጣሉ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።

ትራምፕ "በአሜሪካ እና የቅርብ አጋሯ እስራኤል ላይ ቅቡለነት እና መሠረት የሌለው ተግባር እየፈጸመ ነው" ሲሉ የከሰሱት ዓለም አቀፉ የጦር የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ላይ ማዕቀብ የጣሉበት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ላይ ፈርመዋል።

ትራምፕ አይሲሲ ላይ የጣሉት ዕቀባ እና ቪዛን የሚያጠቃልል ነው።

የቪዛ ዕቀባው የአሜሪካ ወይም የአጋሯቿ ዜጎች ላይ ምርመራ የሚያደረጉትንና የሚረዱ ግለሰቦች እና ቤተሰቦቻችን ዒላማ ያደረገ ነው።

ታራምፕ ይህንን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ የፈረሙት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ዋሽንግተንን እየጎበኙ ባሉበት ወቅት ነው።

ባለፈው ጥቅምት ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ኔታኒያሁ በጋዛ ፈጽመውታል ባለው የጦር ወንጀል ምክንያት የእስር ትዕዛዝ አውጥቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ይህንን ክስ እስራኤል አትቀበለውም። በተመሳሳይ ፍርድ ቤቱ የሐማስ የጦር አዛዥ ላይ የእስር ትዕዛዝ አውጥቷል።

አሜሪካ የዚህ ዓለም አቀፍ ተቋም አባል አይደለችም። በተደጋጋሚም በአሜሪካ ዜጎች ላይ በፍርድ ቤቱ የሚተላለፍ ውሳኔዎችን ውድቅ አድርጋለች።

አይሲሲ እስራኤል ራሷን የመካለከል መብቷ ላይ እንቅፋት ፈጥሮ ኢራን እና ጸረ እስራኤል የሆኑ በድኖችን ችላ ብሏል ሲል ዋይት ኃውስ ገልጿል።

ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው አሜሪካ በአፍጋኒስታን የጦር ወንጀል ፈጽማ እደሆነ ምርመራ ሲያደረጉ የነበሩ የአይሲሲ ባለስለጣናት ላይ ማዕቀብ ጥለው ነበር። ሆኖም ማዕቀቦቹ በተኳቸው ጆ ባይደን ተሽረዋል።

ባለፈው ወር የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አይሲሲ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ድምጽ ሰጥቷል። ሆኖም ረቂቁ ላይ የሕገ መወሰኛው ምክር ቤት ሳይስማማበት ውድቅ ሆኗል።

ሐሙስ ጥር 29/2017 የተሰራጨ የዋይት ኃውስ የውስጥ መልዕክት (ሜሞ) ሄግ የሚገኘውን ዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት "አሳፋሪ የሆነ የሞራል እኩልነት" በሐማስና እስራኤል መካከል በመፍጠር በተመሳሳይ ጊዜ የእስር ትዕዛዝ አውጥቷል ሲል ይከሳል።

የትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ደግሞ የአይሲሲ ድርጊት አሜሪካን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነው ይላል።

በአውሮፓ የሚገኙ በርካታ ሀገራትን ጨምሮ ፍርድ ቤቱ 120 አባል ሀገራት ቢኖሩትም አሜሪካም ሆነ እስራኤል የተቋሙ አባል አይደሉም።

አይሲሲ በዓለም ዙሪያ የፍርድ ሂደት የመጨረሻው ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን የሀገራት መሪዎች ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ወደ ፍርድ ማምጣት ሲያቅታቸው ወይም ሳያመጡ ሲቀሩ ተጠያቂነት ለመፈጠር ይሰራል።

የትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ አሜሪካም ሆነች እስራኤል በጦርነት ህግ በጥብቅ የሚመራ ሠራዊት ያላቸው ዲሞክራሲያዊ ሀገራት ናቸው ሲል አስፍሯል።

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም በሥልጣን ዘመናቸው የመጨረሻ ሳምንታት የአይሲሲን ውሳኔ የታቀወሙ ሲሆኑ እስራኤልና ሐማስ በእኩል የሚታዩ አይደሉም ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።

ትራምፕ ይህንን ትዕዛዝ የፈረሙት ሀገራቸው ጋዛን የመቆጣጣር ፍላጎት እንዳላት ከገለጹ በኋላ ነው።