"በፍፁም የማያላውስ ነገር ካለ ወደ ግል ሥራዬ እመለሳለሁ" አዲሱ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ

የፎቶው ባለመብት, EHRC
አዲሱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ሥራቸውን በጫና ምክንያት መፈፀም ካልቻሉ እንደሚለቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ ኃላፊነቱን በተረከቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከ10 ዓመት በፊት ስለተሰናበቱት ፖለቲካ ጉዟቸው፣ በኢሰመኮ ምን ሊሠሩ እንዳሰቡ እና ሌሎች ጉዳዮችንም ዳሰዋል።
"ወደ ኋላ አይመለስም" ሲሉ በተቋሙ ነፃነት እና ገለልተኛነት ላይ ስጋት ላላቸው አካላት ምላሽ የሚሰጡት አዲሱ ኮሚሽነር፤ የሰብዓዊ መብቶች ኢንስቲትዩት ማቋቋም ይሻሉ።
አቶ ብርሃኑ የቀድሞውን ዋና ኮሚሽነርን ጫማ ለመሙላት "እውቀቱ እና ልምዱ" አለኝ ብለዋል።
1995 ዓ.ም. ገደማ በንቃት ወደ ፖለቲካው ዓለም መግባታቸውን የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ በ2007 ዓ.ም. "በፍላጎታቸው" ከፖለቲካ መውጣታቸውን ተናግረዋል።
ጅማሮ እና ውዝግብ
አዲሱ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ከሕግ መምህርነት ጀምሮ በቀድሞው ደቡብ ክልል የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ፣ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እንዲሁም በፌደራል ተቋማት ውስጥም ሠርተዋል።
በአወዛጋቢው ምርጫ 1997 የትውልድ አካባቢያቸውን ቦንጋን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆኑት አቶ ብርሃኑ 12 ዓመት ገደማ የዘለቀ የፖለቲካ ጉዞ አላቸው።
ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስርት፣ ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ የአዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ዳይሬክተር በመሆን የሠሩ ሲሆን፣ ከከፍተኛ የሥራ ኃላፊነታቸው "በሕዝብ ቅሬታ" እንደተነሱ በወቅቱ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበው ነበር።
ሆኖም አዲሱ የኢሰመኮ ኮሚሽነር "በሕዝብ ቅሬታ" ከሥራቸው ተሰናብተዋል መባሉን "መሠረተ ቢስ" ሲሉ ያጣጥሉታል።
"ከሕዝብ የተነሳብኝ ቅሬታ የለም" የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ ከሥራቸው የተሰናበቱት በምርጫ በመሸነፋቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
"ምርጫውን ተከትሎ ካቢኔ ሪሻፍል (ድልድል) ይደረግ ነበር። ካቢኔ ሲደለደል በወቅቱ የካቢኔ ጉዳዮች መደብ ላይ የሥራ አስፈፃሚ ደረጃ ላይ የደረሰ እንዲመጣ ተደረገ። እኔ ወደ አዕምሯዊ ንብረት ተመደብኩ" ብለዋል።
ከፖለቲካ እና ከመንግሥት ሥራ "በግል ፍላጎታቸው" እንደለቀቁ የሚያሰምሩት አዲሱ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር፤ "ከ2002 በኋላ የፖለቲካ ተሳትፎዬ መዘጋት አለበት ብዬ ነው የዘጋሁት" በማለት ወደ ቀጣዩ የሕይወታቸው ምዕራፍ ለመሸጋገር ሲሉ ውሳኔው ላይ መድረሳቸውን ገልፀዋል።
"በፖለቲካው ዓለም ዕድሜ ልክ ተቆይቶ እንዴት ነው ጡረታ የሚወጣው? አንድ ሙያ [ሥራ] ላይ ረጅም ጊዜ ሲቆይ አሰልቺ ነው የሚሆነው። ወይ ተምሮ አንዱ ላይ መጨመር ያስፈልጋል" ሲሉ ለተሻለ ሕይወት ሲሉ ከፖለቲካ ወጥተው ወደ ግል ሥራ ፊታቸውን ማዞራቸውን ተናግረዋል።
ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 10 ዓመታት ደግሞ በጥብቅና እና በማማከር ሥራ ላይ በግላቸው ተሰማርተው ቆይተዋል።
ከ10 ዓመት በኋላ መመለስ
ባለፈው ዓመት መጨረሻ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለን ለመተካት የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አስመራጭ ኮሚቴ አቋቁሞ ዕጩዎችን ሲቀበል፤ ተቋሙን ለሰባት ወራት ያህል በምክትል ዋና ኮሚሽነት ራኬብ መሰለ ሲመሩት ቆይተዋል።
ለኮሚሽነርነት "በሕዝብ በተሰጠ ጥቆማ" እንደታጩ ለቢቢሲ የተናገሩት አቶ ብርሃኑ፤ በማን እና እንዴት የሚለውን በዝርዝር እንደማያውቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዕጩነታቸው ሲነገራቸው የተደበላለቀ ስሜት እንደተሰማቸው የተናገሩም ሲሆን፤ መጀመሪያ ላይ "እቀበላለሁ፤ አልቀበለም ለማለት የሚያስቸግር" እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከመንግሥት ሥራ ርቀው የቆዩት አቶ ብርሃኑ አዴሎ ዕድሉን ካገኙ "አገር እና ሕዝብን ማገልገልን" እንደ ጥሩ አጋጣሚ በማየታቸው ኃላፊነቱን ለመቀብ እንደወሰኑም ጠቁመዋል።
ተቋሙን በዋና ኮሚሽነርነት ለመመራት ጥር 22/2017 ዓ.ም. በቀጥታ ባልተላለፈ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ዕጩ ሆነው ሲቀርቡ የገለልተኛነታቸው ጉዳይ ጥያቄ ተነስቶበታል።
በተለይም ከተቃዋሚ የም/ቤቱ አባላት 'የፖለቲካ ሰው ናቸው' በሚል ገለልተኛነታቸው ላይ እና የኮሚሽኑ ገፅታ ላይ ጥያቄ ተነስቷል።
አቶ ብርሃኑ "የፖለቲካ ሥራ [ምደባ] ቢሆን ኖሮ ሌላ ውሳኔ እወስን ነበር" ሲሉም ኃላፊነቱን 'በፖለቲካ ሹመት' ሳይሆን በሙያቸው ለቦታው ይመጥናሉ ተብለው እንደተሹሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአምስት ዓመት የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ከትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ልምድ ባለፈ ስመ-ጥር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ስለመሆናቸው ብዙዎች ይመሰክራሉ።
ምትካቸው አቶ ብርሃኑ አዴሎ 'የቀድሞውን ዋና ኮሚሽነር ጫማ አይሞሉም' የሚል ስጋትም በአንዳንዶች ሲሰነዘር ይሰማል።
ነገር ግን አዲሱ ኮሚሽነር "ስጋት አይግባችሁ" በማለት የኮሚሽኑን ሥራዎች አጠናክሮ ለመቀጠል "እውቀቱ፤ አቅሙም አለኝ" ብለዋል።
በቀድሞው ዋና ኮሚሽነር የተጀመሩ ሥራዎችን እንደሚያስቀጥሉ የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በእርሳቸው የሥራ ዘመን የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ "አንድ ደረጃ" ለማሳደግ መወጠናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, EHRC
ትኩረቶቻቸው እና "ወደ ኋላ አንመለስም"
ሦስት መሠረታዊ ሥራዎችን ለመሥራት እንደወጠኑ የተናገሩት አቶ ብርሃኑ፤ "እዚህም እዚያም" የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን "ለማስቆም" ትምሕርት እና ግንዛቤ ላይ "ሰፋፊ ሥራዎችን" መስራት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ ገልፀዋል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን "በአግባቡ መመርመር" ሁለተኛው የትኩረታቸው ጉዳይ መሆኑን ያነሱም ሲሆን፤ "በገለልተኝነት፣ ያለማንም ተፅዕኖ የምርመራ ሥራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።
በሦስተኛው የትኩረት ሥራቸው ከምርመራዎች በመነሳት "አጥፊዎች እንዲታረሙ፤ ጉዳት የደረሰባቸው አካላት [ደግሞ] እንዲካሱ ማድረግ" መሆኑን ገልፀዋል።
"የተጀመሩ ሥራዎች በየትኛውም መንገድ ወደ ኋላ ይመለሳሉ የሚል ስጋት በማንኛውም አካል ሊፈጠር አይገባም" በማለት ይልቁንም ተቋሙን የማጠናከር ሥራ እንደሚሠሩ መተማኛ ሰጥተዋል።
ይህን ለማድረግም "አስቻይ ሁኔታ አለ" የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ ምክንያታቸው ደግሞ የተቋሙ ማሻሻያ እና የመንግሥት ቁርጠኝነት ነው።
ለሦስት አስርት ዓመታት ሥራ ላይ የቆየው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በተደጋጋሚ "መንግሥታዊ ጫና" ሥራውን ያቆመ ሲሆን፤ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ሥራቸውን ለመሥራት ምኅዳሩ እየጠበበ ነው ሲሉ ይደመጣሉ።
ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ ክልል በግፍ የተገደሉትን ፖለቲከኛ አቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ ለመርመር ያቀናው የኢሰመኮ መርማሪዎች ቡድን ከእማኞች ደኅንነት ስጋት ባለፈ መዋከብ እንደገጠመው እና ምርመራውን ለማቆም መገደዱን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ከ10 ወራት በኋላም የምርመራው ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ አልሆነም።
"እንደዚህ ዓይነት አደናቃፊዎች ቢከሰቱ እንኳ ባለኝ ልምድ ጫና አድርጌ የተቋሙን ነፃነት እና ገለልተኛነት [አስጠብቄ] ሥራው በአግባቡ እንዲሠራ አደርጋለሁ የሚል እምነት ለኝ" የሚሉት አቶ ብርሃኑ፤ ከሥራ አስፈፃሚው ጋር "በትብብር" እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, HOPR
"ምንጩን የማድረቅ ሥራ"
በሕንድ አገር ለሠሩት ሁለተኛ ዲግሪያቸው የመመረቂያ ፅሁፍ በኢሰመኮ ላይ ያተኮሩተረ አቶ ብርሃኑ አዴሎ ኢሰመኮ የተደራሽነት ጉድለት አለው ብለው ያምናሉ።
"በተወሰኑ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ነው የሚንቀሳቀሰው። ታች አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ መሆን ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር የተወሰኑ እጥረቶች እንዳሉ እገነዘባለሁ" ይላል።
በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተዋንያኑ ስለመበራከታቸው ተሟጋቾች ይናገራሉ።
ሆኖም ግን ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው መንግሥት ስለመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ሪፖርቶች ያመላክታሉ።
ዋና ኮሚሽነሩ የሚፈፀሙ ጥሰቶችን ለማስቀረት እና አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር "ስማቸው በተደጋጋሚ የሚነሱ" የመንግሥት ተቋማትን "መቅረብ፣ ትምህርት መስጠት፣ ማሠልጠን" ላይ አተኩረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
"ምንጩን የማድረቅ ሥራ" ሲሉ ለገለፁት እና የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ላሉት ትኩረታቸው የአጭር ጊዜ ዕቅድ እያዘጋጁ መሆኑንም አመልክተዋል።
ጠንካራ የሰብዓዊ መብት ትምህርት እና ሥልጠና የሚሰጥ "የሰብዓዊ መብቶች ኢንስቲትዩት" የማቋቋም ውጥን ያላቸው አቶ ብርሃኑ ይህ ተቋምም አሻራቸው እንዲሆን ይሻሉ።
አዲሱን ሥራቸውን ከጀመሩ ገና በጣት የሚቆጠሩ የቀናት ዕድሜ ያላቸው አቶ ብርሃኑ አዴሎ፣ በጫና እና በሌሎች ምክንያቶች የኮሚሽኑን ዓላማ መፈፀም ካልቻሉ ሥራቸውን እንደሚለቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የማያሠራኝ ነገር ከተፈጠረ . . . ወደ ነበርኩበት [የግል ሥራ] ነው የምመለሰው። ወደ ግሉ ዘርፍ ተመልሼ እሄዳለሁ። በፍፁም የማያላውስ ነገር ካለ የእኔ እዚህ መቀመጥ ትርጉም የለውም። የእኔ መቀመጥ ትርጉም እስከሌለው ድረስ ወደ ግል ሥራዬ ነው የምመለሰው" ብለዋል።












