በጄኔቫ እየተካሄደ ባለው የሱዳን የሰላም ውይይት ተፋላሚ ወገኖች ሳይገኙ ቀሩ

የተፈናቀሉ ሱዳናውያን

የፎቶው ባለመብት, AFP

ለአስራ ስድስት ወራት የዘለቀውን የሱዳን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለመቋጨት በስዊትዘርላንድ መዲና ጄኔቫ የሰላም ውይይት ቢጀመርም ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች እንዳልተገኙ ተገለጸ።

የአሸማጋይነቱን ሚና የያዘችው አሜሪካ ተፋላሚ ወገኖች ባይገኙም በሱዳን ያለውን አስከፊ ቀውስ ለመግታት የሚቻለው ሁሉ እንደሚደረግ አጽንኦት በመስጠት ውይይቱ ይቀጥል ብላለች።

የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ተፋላሚዎች የሆኑት በጦሩ መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል በሚደረገው ፍልሚያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ሲገደሉ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።

በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት “በዓለማችን እጅግ የከፋ የረሃብ ቀውስ” እንዳስከተለም የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

የአገሪቱ ጦሩ በውይይቱ ላይ እንደማይገኝ ከበርካታ ቀናት በፊት ያስታወቀ ሲሆን፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በመጨረሻዋ ሰዓት ወደ ስዊትዘርላንድ መሄዳቸውን ቢያሳዉቁም በውይይቱ ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል።

የአል ቡርሐን ጦር የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሳዑዲ አረቢያ ላይ የተስማማውን ተግባራዊ ባለማድረጉ በዚህ ውይይት ላይ እንደማይገኝ ማስታወቁን ተከትሎ የተኩስ አቁም ውይይቱን ተስፋ አጨልሞታል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ታጣቂዎቹን ከሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ አካባቢዎች እና የሕዝብ ተቋማት እንዲወጣ የተደረሰውን የጂዳ ስምምነት አለማክበሩን ጦሩ ከሷል።

“እያንዳንዱ ሚሊሻ እየዘረፏቸው እና ቅኝ እየገዟቸው ካሉ ከተሞች እና መንደሮች እስካልወጡ ድረስ ወታደራዊ ዘመቻ አይቆምም” ሲሉ አል ቡርሐን ገልጸዋል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እየቀረበበት ያለውን የሰላማዊ ሰዎች ጥቃት እና የዘረፋ ውንጀላ ውድቅ አድርጓል።

እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ የሱዳን ጦር በውይይቱ ላይ ይገኛል የሚል ተስፋ ተደርጎ ነበር።

በተጨማሪም የሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሮሎ “የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ልዑካን እስከ ምሽት 5፡30” ድረስ እየተጠበቁ እንደነበር ገልጸዋል።

ልዩ መልዕክተኛው አክለውም “ዓለም ይህንን እየታዘበ ነው” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ባልተገኙበት በዚህ ውይይት ሌሎች አሸማጋይ አካላት በሱዳን “የምግብ እና የመድኃኒት ተደራሽነት እንዲሁም የሰላማዊ ዜጎችን ጥበቃ በተመለከተ እየተወያየን ነው” ሲሉ ልዩ መልዕክተኛው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በበኩሉ ልዑካኑ ጄኔቫ መገኘታቸው “የሱዳንን ሕዝብ ስቃይ ለማቃለል ያላቸውን ጠንካራ ቁርጠኝነት ማሳያ ነው” ሲል ማክሰኞ ማታ አስታውቆ ጦሩ በዚህ ውይይት ተሳታፊ እንዲሆን ጠይቆ ነበር።

ነገር ግን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ልዑካን ረቡዕ በተጀመረው የሰላም ውይይት አልተገኘም። ቡድኑ ከዚህ ውይይት ራሱን ያገለለበትን ምክንያት አልገለጸም።

ውይይቱ ከመጀመሩ እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ራሱን ከማግለሉ በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሱዳን ዋና አስተባባሪ ሙኬሽ ካፒላ በተፋላሚዎቹ መካከል ያለው ስሜት የጨለመ መሆኑን ገልጸው ነበር።

“ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች እርስ በርስ ለመነጋገር ፍላጎት ያላቸው አይመስለኝም። ጦሩ እንደማይገኝ ያስታወቀ ሲሆን፣ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በውይይቱ ላይ ይሳተፋል ተብሎ አይጠበቅም” ብለዋል።

ልዩ ልዑኩ በበኩላቸው ጦሩ “የሱዳንን ሕዝብ ድምጽ” በመስማት የድርድር ልዑካኑን ወደ ጀኔቫ እንደሚልክ “ተስፋ አለኝ” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በሱዳን የተኩስ አቁም ለመድረስ በሳዑዲ አረቢያ እና በባህሬን የተደረጉ ውይይቶች ፍሬ አላፈሩም።

ረቡዕ በተጀመረው የሰላም ውይት አሜሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብፅ፣ አፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካዮቻቸውን ልከዋል።

በጂዳ ላይ የተደረሰውን ስምምነት ዋቢ በማድረግ ጦሩ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በዚህ ውይይት በታዛቢነት መገኘቷን ተቃውሟል ተብሏል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን የጦር መሳሪያ ታስታጥቃለች የሚል ክስ ቢቀርብባትም አገሪቷ ግን ይህንን ታስተባብላለች።

አሜሪካ በበኩሏ በሱዳን ጦርነት ውስጥ ተጽእኖ አላቸው ተብለው የሚታሰቡት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ግብፅ መገኘት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲኖር ለማገዝ ሚና ይጫወታል ብላለች።

በሱዳን ያለው ጦርነት እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ እገዳ ከቀጠለ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ሊከሰት እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ገልጿል።

በጄኔቫ ውይይቱ በተጀመረበት ወቅት የህክምና በጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው ኤምኤስኤፍ በከበባ ውስጥ ባለችው ኤልፋሽር ከተማ በብቸኝነት አገልግሎት እየሰጠ የነበረው ሆስፒታል በተፈጸመበት ከባድ የቦምብ ጥቃት ሊዘጋ እንደሚችል አስታውቋል።

እሁድ ዕለት የሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ክፍል በደረሰበት ጥቃት አንድ ህመምተኛ የተገደለ ሲሆን፣ በተጨማሪም አምስት ሰዎች መቁሰላቸውን ተቋሙ ገልጿል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ይህችን ከተማ ለመቆጣጠር ለወራት ያህል ከጦሩ ጋር ፍልሚያ ላይ ያለ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።

በምዕራብ ዳርፉር ግዛት የምትገኘው ኤልፋሽር በጦሩ ቁጥጥር ስር ያለች ብቸኛዋ ከተማ ናት። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዳርፉር ግዛት አረብ ባልሆኑ ማኅበረሰቦች ላይ መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰቶችን በመፈጸም ክስ ይቀርብበታል።