በየጎዳናው ምጽዋት ከመጠየቅ ወጥቶ በ16 ዓመቱ ማንበብ የተማረው ዶክተር

የፎቶው ባለመብት, Dr Li Chuangye
ሊ ቹአንጌይ የ37 ሐኪም ሲሆን መከራን ታግሎ ያሸነፈበት ታሪኩ እና ተራራ ወጪነቱ በቻይና መነጋገሪያ ሆኗል።
በፖሊዮ በሽታ ምክንያት በልጅነቱ ወደ ልመና ጎዳና ለመውጣት የተገደደው ሊ በ16 ዓመቱ ነበር ማንበብ የተማረው።

የፎቶው ባለመብት, Dr Li Chuangye
እ.አ.አ በ1988 በሄናን ግዛት ከደሃ አርሶ አደሮች የተወለደው ሊ ቻንጊይ፤ የሰባት ወር ጨቅላ ሳለ ነበር በፖሊዮ የተጠቃው። በሽታው ቁጢጥ ካላለ በቀር መራመድ እንዳይችል አድርጎታል።
ሊ ልጅ እያለ እንደ ሌሎች ልጆች በጀርባው ቦርሳ አንጠልጥሎ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ሕልሙ ነበር። ይሁን እንጂ መሳለቂያ መሆኑ አንገቱን አስደፋው። አንዳንድ ልጆች "ብክነት" ነህ፤ "ምግብ ከመብላት የዘለለ ሌላ ጥቅም የለህም" አሉት።
"ይህ በጣም ጎዳኝ" ይላል ሊ።
ሊ የዘጠኝ ዓመት ልጅ እያለ ወላጆቹ እግሩ ላይ ቀዶ ሕክምና ቢደረግለት መራመድ ይችላል ተብሎ ሲነገራቸው ለሕክምናው ገንዘብ ተበደሩ።
ሊ በዚህ ቀዶ ሕክምና ትልቅ ተስፋ ነበረው። "እያገገምኩ እያለ ሌሎች ልጆች ያለቅሳሉ፤ እኔ ግን ፈገግ እያልኩ ነበር። ምክንያቱም እንደ ማንኛውም ሰው በቅርቡ መራመድ እችላለሁ የሚል ስሜት ነበረኝ" ይላል።
ነገር ግን ሕክምናው አልተሳካም። የሊን ቆሞ የመራመድ ተስፋ በመንጠቅ፤ ጥልቅ ድብርት ውስጥ ከተተው። ሕይወቱ ትርጉም አልባ ሆኖ ተሰማው። እናም ለእናቱ ሞት እንደሚሻለው ነገራት።
እናቱ ተስፋ እንዳይቆርጥ ነገረችው። "እያሳደግንህ ያለው እኛ ስናረጅ የሚያጫውተን እንድናገኝ ነው። ውሻ ወይም ድመት መናገር አይችሉም፤ አንተ ግን ትችላለህ" አለችው።
እነዚህ ቃሎች በልቡ ታተሙበት። "ወላጆቼ እና ቤተሰቦቼ ለእኔ ምን ያህል መስዋዕት እንደከፈሉ አሰብኩ፤ እናም ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ። በሕይወት መኖር እንዳለብኝ ተረዳሁ፤ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለእነርሱም" ይላል ሊ።
ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በቤተ መቅደስ ጭሳ ጭስ የሚሸጥ አካል ጉዳተኛ ፍለጋ መንደራቸው የመጣ እንግዳ ሰው ሕይወቱን ባላሰበው መልኩ ቀየረው።
"ቤተሰቦቹ በጣም ተቃወሙት፤ እኔ ግን ገንዘብ ማግኛ እና የቤተሰብ ጫናን ማቃለያ መንገድ አድርጌ ተመለከትኩት" የሚለው ሊ፤ እንግዳውን ሰው ተከትሎ ለመሄድ ተስማማ።

የፎቶው ባለመብት, Dr Li Chuangye
ምጽዋት መጠየቅ
ትሰራለህ ተብሎ የተገባለት ቃል ማጭበርበሪያ ነበር።
ሊ መንደራቸው የመጣው ሰው ልመና ተግባር ላይ በሰፊው የተሰማራ እንደነበር ይናገራል።
እናም ለቀጣይ ሰባት ዓመታት ከሌሎች አካል ጉዳተኛ ሕፃናት እና አዋቂዎች ጋር መንገድ ላይ እንዲለምን ተገድዷል።
ሊ ያለ ካናቲራ ሳንቲም ያለው ጎድጓዳ ሳህን ተሰጥቶት፤ ሐዘኔታ በሚያስገኝ መልኩ እግርና ሆዱ ተላትመው መንገድ ዳር ተቀመጠ፤ ነዳይ ሆነ።
ሊ አንድ መንገደኛ ትምህርት ቤት ከመሄድ ይልቅ መንገድ ላይ ለምን እንደሚለምን እስኪጠይቀው ድረስ ሰዎች በሳህኑ ላይ ገንዘብ ለምን እንደሚሰጡት መረዳት አልቻለም ነበር።
ሊ በቀን ጥቂት መቶ ይዋን ከልመና ያገኝ የነበረ ሲሆን፤ ይህም በ1990ዎቹ ትልቅ ገንዘብ ነው። ይሁን እንጂ ሁሉንም ገንዘብ "ለአለቃው" ነበር የሚሰጠው።
"ከሌሎች ልጆች ያነሰ ገንዘብ ካገኘሁ፤ በስንፍናዬ እንደሆነ ይነግረኛል፤ አንዳንዴም ይደበድበኛል። እናም እነዚህ ዓመታት ለእኔ በጣም ከበድ ነበሩ" ይላል።
ሊ ሌሎች ልጆች ጠፍተው ሲሄዱ ወይም በፖሊስ እንዲመለሱ ሲደረግ ቤተሰቦችን ለመርዳት ሲል የፖሊስን እርዳታ ለመቀበል አልፈቀደም ነበር።
ለሰባት ዓመታት፤ ክረምት እና በጋ፤ ሊ በመላው አገሪቱ እየተዟዟረ ለምኗል።
"ገሃነም ውስጥ እየኖርኩ እንደሆነ ነበር የሚሰማኝ። ሰው ቀና ብዬ አላይም፤ ከሰዎች ሀዘኔታ ለማግኘት እግሮቼ ከሆዴ ተላትመው ይውላሉ። ለልመና ላለመውጣት ዝናብ እና ጨለማ እንዲሆን እፀልይ ነበር" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
በየዓመቱ ለአዲስ ዓመት ለቤተሰቦቹ ደውሎ ደኅና መሆኑን እና እንዳይጨነቁ ይነግራቸዋል።
ከ20 ዓመታት በኋላ ቁስሉ አሁንም አልደረቀም። "ልመና ጥልቅ የስነ ልቦና ጠባሳ ጥሎብኛል። አሁንም ድረስ ያቃዠኛል. . ."።

የፎቶው ባለመብት, Dr Li Chuangye
ትምህርት የከፈተው አዲስ መንገድ
ሊ ከመንገድ ጋዜጣ አንስቶ ሲመለከት ማንበብ የሚችለው የስሙን ፊደላት ብቻ እንደሆነ ተረዳ፤ ሁሉም ነገር የተቀየረው በዚህ ቅፅበት ነው ይላል። በ16 ዓመቱ ወደ ትውልድ መንደሩ ተመልሶ ትምህርት ቤት ለመግባት ወሰነ።
"ማንበብ እና መፃፍ አልችልም። እናም ሕይወቴን መቀየር የምችለው በትምህርት ብቻ ነው" ብሎ እንዳሰበ ይናገራል።
በዚህ ጊዜ የአገሪቱ መንግሥት አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን ለልመና መጠቀምን ወንጀል ያደረገ አዲስ ፖሊሲ አውጥቶ ነበር። ሊ ወላጆቹ የገንዘብ አቅምም መሻሻሉን ሰማ። አለቃውን ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ መሄድ እንደሚፈልግ ነግሮ ወደ መንደሩ ገባ።
በወላጆቹ እርዳታ ሊ በ10 ዓመት ከሚያንሱ ተማሪዎች ጋር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ጀመረ።
ሊ የአካል ጉዳተኛ በመሆን መሰናክሎች ቢበዙበትም ትምህርቱ ላይ ለማተኮር ቆርጦ በመነሳት ከዘጠኝ ዓመት በኋላ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቋል።
ለኮሌጅ ትምህርት ሲያመለክት አካላዊ ሁኔታው ምርጫዎቹን የገደቡበት ቢሆንም "ሐኪም መሆን እችላለሁ፤ ምን አልባት የራሴን እክል መመራመር እችላለሁ፤ እና ቤተሰቦችን መርዳት፣ ሕይወት መታደግ እና ለማኅበረሰቡ ማበርከት እችላለሁ" የሚል ሀሳብ አቃጨለበት።

የፎቶው ባለመብት, Dr Li Chuangye
ሊ በ25 ዓመቱ የሕክምና ትምህርት ቤት መግባት የቻለ ቢሆንም የተቋሙ ተደራሽነት ግን ፈተና ጣለበት። በተለይም የተግባር ትምህርቱ ከባድ ነው፤ ታካሚዎችን ለማየት እንደ ሌሎቹ ተማሪዎች ከሆስፒታል ክፍሎች እየተሯሯጠ መስራት ከባድ መሆኑ ሌሎች በአንድ ቀን የሚማሩት ትምህርት ለእርሱ ከዚያ በላይ ይፈጅበታል።
ይህም ጠንካራ መሆን እንዳለበት እንዳስገደደው የሚናገረው ሊ፤ ተራራ መውጣት እንዲጀምር ውሳኔ ላይ አስደርሶታል። ታይ ተራራን ለመውጣት አምስት ቀን እና ምሽት ፈጅቶበታል። እጆቹ እና እግሮቹ ሲፈረካከሱ እና ሲደሙ ወደ ኋላ አላለም።
ዛሬም ድረስ ተራራ የመውጣት ፍቅሩ ያለው ዶ/ር ሊ፤ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች የሚያጋራቸው ቪዲዮዎች ተደራሽነታቸው ሰፍቷል።
ዢንጂያንግ በተባለ ገጠር ውስጥ ክሊኒክ የከፈተም ሲሆን፤ ታካሚዎቹን ቀን እና ሌሊት በማገልገል "ታምረኛው ዶክተር" የሚል ስም አግኝቷል።
"በራሴ እጆች ታካሚዎቼን መንከባከብ፤ የጎረቤቶቼን ጤና ማሻሻል ከምንም ነገር በላይ እርካታ ይሰጠኛል" ይላል።
የሕይወት ታሪኩ በመላው የቻይና ማኅበረሰብ መድረሱ እንዳስገረመው የማይደብቀው ዶ/ር ሊ፤ ይህም አስተሳሰብን ለመቀየር ይረዳል የሚል ተስፋ አለው።

የፎቶው ባለመብት, Dr Li Chuangye
ዓላማ እና በራስ መተማመን
በርካታ ሰዎች ዶ/ር ሊ የበዘበዘውን እና ለልመና የተጠቀመበትን ሰው ለምን ለሕግ አካል እንደማያቀርበው ይጠይቁታል። "የኋላ ታሪኬ ኋላ እንዲቀር ወስኛለሁ" ይላል።
"እነዚያ ሰባት ዓመታት ከባድ ነበሩ፤ ነገር ግን የሕይወቴ አካል ናቸው"።
የሕይወት ጉዞው እይታውን ቀርፆታል። "ትምህርት ቤት መሄድ ከጀመርኩ በኋላ ሌሎች ምን እንደሚሉ መጨነቄን አቆምኩ። እነዚህ ነገሮች ትርጉም አልባ እንደሆኑ ተረዳሁ። ጊዜዬን እና ኃይሌን ትምህርቴ ላይ ብቻ በማድረግ፤ የሕይወቴን ዓላማ ማሳካት ፈለግኩ" ይላል።
በርካታ አካል ጉዳተኞች ወደፊት ተራምደው ሕይወታቸውን ለመቀየር ይቸገራሉ፤ ምክንያቱም ሰው እንዳይፈርድባቸው እና እንዳይሳለቅባቸው ይፈራሉ ይላል።
"ለእኔ ግብ ይህ ነጥብ የለውም። በዩኒቨርስቲ ግቢ እና ከተማ ውስጥ ቁጢጥ ወይም እየተንቦራቸቸሁ እንቀሳቀሳለሁ። በመቶዎች አካል ጉዳተኛ ጓደኞቼን በሥራዬ አግዛለሁ። ይህንም ሳደርግ በራስ መተማመን ውስጥ እንደሆንኩ አስባለሁ። ስለ ሌሎች ሰዎች እይታ መጨነቅ ካቆምኩ ቆይቻለሁ"።
ለማኅበረሰቡም ይህን ጥበብ ያጋራል፤ "ሕይወታችን ልክ እንደ ተራራዎች ነው። አንዱን እንወጣለን፤ ሌላ ከፊታችን የሚጠብቀን አለ። ያለማቋረጥ ለማደግ እንጥራለን።
"ሰው ሁሌም አዎንታዊ፣ ተስፈኛ እና ለህልሙ ወደ ኋላ የማይል መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ"።















