የሕንድ ፍርድ ቤት ዶክተሮች የእጅ ጽሑፋቸውን እንዲያስተካክሉ አዘዘ

የፎቶው ባለመብት, Chilukuri Paramathama
ብዙ ሰዎች ለመጻፍ ኮምፒውተሮችን በሚጠቀሙበት በዚህ ጊዜ የእጅ ጽሑፍ በእርግጥ አሳሳቢ ነው?
የሕንድ ፍርድ ቤቶች ለዚህ መልሳቸው ጸሐፊው ዶክተር ከሆነ አዎ የሚል ነው።
በሕንድ በፋርማሲ ባለሙያዎች ብቻ ሊነበብ የሚችለው የዶክተሮች እጅ ጽሑፍ ለበርካታ ቀልዶች መነሻ ነው።
ይህ የዶክተሮች የእጅ ጽሑፍ ጉዳይ ግን የሕንድ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ችግር ይመስላል።
ነገር ግን ቁልጭ ያለ የእጅ ጽሑፍን አስፈላጊነት የሚያጎላው የፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰማው ከሕንዷ ፑንጃብ እና ከሃሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው።
ውሳኔው "የሚነበብ የሕክምና ማዘዣ መሠረታዊ መብት ነው" ምክንያቱም በሕይወት እና በሞት መካከል ልዩነት ሊፈጥር ይችላል።
የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የመጣው ከተፃፈ ማዘዣ ጋር ምንም ግንኙነት በሌለው ጉዳይ ነው።
አንዲት ሴት ተፈጽሞብኛል ስትል ባቀረበችው የአስገድዶ መድፈር፣ የማጭበርበር እና የሀሰት ውንጀላዎችን የሚያዩት ዳኛ ጃሳጉርፐርት ሲንግ ፑሪ የተከሳሹን የዋስትና ይፈቀድልኝ ጥያቄ እየሰሙ ነበር።
ሴትዮዋ ግለሰቡ የመንግሥት ስራ እንደሚያስቀጥራት ቃል ገብቶ ገንዘብ የተቀበላት ሲሆን፣ ከእርሷ ጋር ሐሰተኛ የሥራ ቃለ መጠይቅ በማድረግ እና ጾታዊ ብዝበዛ እንደፈፀመባት ተናግራለች።
ተከሳሹ ክሱን ውድቅ አድርጎ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንደነበራቸው ተናግሯል።
አሁን ክስ የመሠረተችውም በገንዘብ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ነው ባይ ነው።
ዳኛ ፑሪ ለፍርድ ቤቱ የቀረበውን ሕክምና ማስረጃ በተመለከቱ ወቅት ምርምራ ያደረገላት ዶክተር የእጅ ጽሑፍን ለመረዳት አዳጋች እንደሆነባቸው ጠቅሰዋል።
በውሳኔያቸው ላይ "አንድ ቃልም ሆነ ፊደል እንኳን የማይነበብ በመሆኑ የዚህን ፍርድ ቤት መርህ አናውጧል" ሲሉ ጽፈዋል።
ቢቢሲ የፍርዱን ውሳኔ ግልባጭ እና ባለ ሁለት ገጽ የምርመራ ውጤት ያገኘ ሲሆን ከውሳኔው ጋር የተያያዘው የምርመራ ውጤት ላይ የዶክተሩ የእጅ ጽሑፍ ፈጽሞ ማንበብ አይቻልም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ቴክኖሎጂ እና ኮምፒውተሮች በቀላሉ ተደራሽ በሆኑበት በአሁኑ ወቅት በመንግሥት የሕክምና ተቋማት የሚሠሩ ዶክተሮች አሁንም ምናልባት ከአንዳንድ የፋርማሲ ባለሙያዎች በስተቀር ማንም ሊያነብበው የማይችለውን የመድሃኒት ማዘዣ በእጅ እየፃፉ መሆናቸው አስደንጋጭ ነው" ሲሉ ዳኛ ፑሪ ጽፈዋል።
ፍርድ ቤቱ መንግሥት በሕክምና ትምህርት ቤት ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የእጅ ጽሑፍ ትምህርቶችን እንዲያካትት የጠየቀ ሲሆን በኮምፒውተር የመድሃኒት ማዘዣዎችን ለመጻፍ የሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ አስቀምጧል።
ይህ እስኪሆን ድረስ ሁሉም ዶክተሮች የመድሃኒት ማዘዣዎችን ጎላ ባሉ ፊደላት በግልፅ መፃፍ አለባቸው ሲል ዳኛ ፑሪ ወስነዋል።
ከ330,000 በላይ ዶክተሮችን በአባልነት ያቀፈው የሕንድ ሕክምና ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ዲሊፕ ብሀኑሻሊ ለችግሩ መፍትሄ ለማፈላለግ ፈቃደኛ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በትልልቅ ከተሞች ዶክተሮች ወደ ማዘዣዎችን በኮምፒውተር ወደ መፋፍ ተዛውረዋል ነገርግን በገጠር እና በትናንሽ ከተሞች የሐኪም ትእዛዝ ማግኘት በጣም ከባድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
"ብዙ ዶክተሮች ደካማ የእጅ ጽሑፍ እንዳላቸው የሚታወቅ እውነታ ነው፤ ነገር ግን አብዛኛዎቹ የሕክምና ባለሙያዎች በተለይም በተጨናነቁ የመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ በጣም በሥራ የተጠመዱ በመሆናቸው ነው[ይህ የተከሰተው]" ብለዋል።
"አባሎቻችን የመንግሥት መመሪያን በመከተል ለታካሚዎች እና ለፋርማሲ ባለሙያዎች ሊነበቡ የሚችሉ የመድሃኒት ማዘዣዎችን ጎላ ባሉ ፊደላት እንዲጽፉ እንመክራለን፤ በቀን ሰባት ታካሚዎችን የሚያይ ዶክተር ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን በቀን 70 ታካሚዎችን የሚመረምር ግን ማድረግ አይችሉም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Chilukuri Paramathama
የሕንድ ፍርድ ቤት በዶክተሮች የእጅ ጽሑፍ ምክንያት እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ሲያሳልፍ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ከዚህ ቀደም በኦዲሻ ግዛት የሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት "የዶክተሮች የተሞነጫጨረ አጻጻፍ ስልት" ሲሉ በገለፁት አንድ መዝገብ ላይ እና የአላባድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች "በእንዲህ ዓይነቱ የማይነበብ የእጅ ጽሑፍ የተፃፉ ሪፖርቶች ለመረዳት የማይቻሉ ናቸው" በማለት ምሬታቸውን ገልጸው ነበር።
ጥናቶች ግን የዶክተሮች የእጅ ጽሑፍ ከሌሎቹ የከፋ ነው የሚለውን የተለመደ ንግግር አይደግፉም።
ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚናገሩት በዶክተሮች የእጅ ጽሑፍ ላይ አፅንዖት የሚሰጠው ስለ ውበት ወይም ቅንጦት ሳይሆን የሕክምና ትእዛዝ ለአሻሚነት ወይም ለተሳሳተ አተረጓጎም ከፍተኛ፣ አሳዛኝም ጭምር፣ ክፍተት ስለሚተው ነው፥።
እአአ በ1999 ኢንስቲትዩት ኦፍ ሜዲስን ይፋ ባደረገው ጥናት በአሜሪካ መከላከል ከሚቻሉ 44,000 ሞቶች መካከል 7000ዎቹ የተከሰቱት በማይነበብ የእጅ ጽሑፍ የተነሳ የመጡ ናቸው።
በቅርቡ በስኮትላንድ አንዲት ሴት ለሚደርቅ ዓይን ችግር ምክንያት ባደረገችው ሕክምና የብልት መቆም ችግር ላለበት የሚሰጥ ክሬም በስህተት ተሰጥቷት ጉዳት አጋጥሟታል።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ የጤና ባለሥልጣናት "የመድኃኒት ስሕተቶች አስከፊ ጉዳቶችን እና ሞትን ያስከትላሉ" ሲሉ ተናግረው፣ አክለውም "በተጨማሪ ሆስፒታሎች ውስጥ ከኤሌክትሮኒክስ ማዘዣ ዘዴዎች መጠቀም ስህተቶችን በ 50 በመቶ ሊቀንስ ይችላል" ብለዋል ።
ሕንድ በማይነበብ የእጅ ጽሑፍ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት በተመለከተ ጠንካራ የተደራጀ መረጃ የላትም።
ነገርግን ከዚህ ቀደም ብዙ ሕዝብ ባለት አገር የመድኃኒት ማዘዣዎችን አለመነበብ ለድንገተኛ የጤና እክሎች እና ለብዙዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Chilukuri Paramathama
ከታዘዘላት የሕመም ማስታገሻ ጋር ተቀራራቢ ስም ያለው ለስኳር ሕመም የሚሆን መድሃኒት በስህተት ተሰጥቷት ከወሰደች በኋላ ለከፋ ጉዳት የተጋለጠችው ሴት ታሪክ በስፋት የተዘገበ ነው።
በደቡባዊ ሕንድ ቴልጋና ግዛት ናልጎንዳ ከተማ ውስጥ የመድሃኒት ቤት ባለቤት የሆኑት ቺሉኩሪ ፓራማትማ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እአአ በ2014 በኖይዳ ከተማ ለትኩሳት የተሳሳተ መርፌ ተወግታ ስለሞተች የሦስት ዓመት ልጅ ታሪክን ካነበቡ በኋላ የሕዝብ አቤቱታ ፊርማ ለሃይደራባድ ለሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማስገባታቸውን ተናግረዋል።
ሙሉ በሙሉ በእጅ የሚጻፉ የሕክምና ማዘዣዎች እንዲቀሩ የከፈተቱ ዘመቻ ፍሬ አፍርቶ በ2016 የሕንድ የሕክምና ምክር ቤት "እያንዳንዱ ሐኪም ተመሳሳይ ስም ያላቸውን መድኃኒቶች በሚነበብ እና ጎላ ባለጽሑፍ መጻፍ አለበት" ሲል ወስኗል።
እአአ በ 2020 የሕንድ ጤና ሚኒስትር አሽዊኒ ኩመር ቹበይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩት በክልሎች ውስጥ ያሉ የሕክምና ባለሥልጣናት "ትዕዛዙን በሚጥሱ ዶክተሮች ላይ የቅጣት እርምጃ እንዲወስዱ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል" ብለዋል ።
ነገር ግን ከአስር ዓመታት በኋላ ቺሉኩሪ እና ሌሎች ፋርማሲስቶች በማይነበብ የእጅ ጽሑፍ የተጻፉ የመድሃኒት ማዘዣዎች ወደ መደብሮቻችን መምጣታቸውን ቀጥለዋል ይላሉ።
ቺሉኩሪ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሊያነቧቸው ያልቻሏቸውን የመድሃኒት ማዘዣዎችን ለቢቢሲ አጋርቷል።
ከ28 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት እና በቀን ከ4,000 በላይ ደንበኞችን የሚያስተናግደው ዳንዋንታሪ የተባለው ታዋቂ ፋርማሲ አንዳንድ ጊዜ የሚገጥማቸው የመድኃኒት ማዘዣዎች የማይነበብ ብሎ ብቻ ማለፍ ከባድ መሆኑን ይገልጻል።
የመድሃኒት ቤቱ ኃላፊ ራቪንድራ ካንደልዋል "በዓመታት ውስጥ በከተማዎች ውስጥ በእጅ ከተፃፈ ወደ የታተመ የመድሃኒት ማዘዣ ሲቀየር አይተናል፤ ነገር ግን በከተማ ዳርቻዎች እና በገጠር አካባቢዎች አብዛኛዎቹ አሁንም በእጅ የተጻፉ ናቸው።"
ሠራተኞቻቸው በጣም ልምድ ያላቸው እና ደንበኞቻቸው ትክክለኛውን መድሃኒት እንዲያገኙ ለማድረግ አብዛኛዎቹን ማንበብ ይችላሉ ብለዋል።
"እንደዚያም ሆኖ፣ አንዳንድ ጊዜ ትክክለኛውን መድሃኒት መስጠት ለእኛ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ወደ ዶክተሮች መደወል አለብን።"















