የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ከወንዶች በበለጠ ለምን ሴቶችን ያጠቃል? እንዴት መከላከል ይቻላል?

ሽንት ቤት ቁጭ ብላ የምታምጥ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሽንትዎ የመጣ መስልዎት ወደ መጸዳጃ ቤት ሲሄዱ ምንም የሚወጣ ነገር ሳይኖር ቀርቶ ያውቃል?

ይህ አንዱ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምክልት ነው። አንዳንዴ መቋቋም ከምትችሉት በላይ ሆኖ ሊያስጨንቃችሁም ይችላል።

በዓለም አቀፍ ቀደረጃ በየዓመቱ 400 ሚሊዮን ሰዎች የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ሕመም ይገጥማቸዋል።

ሕመሙ ሕጻናትን ጨምሮ ሁለቱንም ፆታዎች የሚጠቃ ቢሆንም ሴቶች ግን የበለጠ ተጠቂ ናቸው።

በዓለም ላይ ከሚገኙት ግማሽ ያህል ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው አንዴ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ያጋጥማቸዋል።

በዓለም ላይ እጅግ በጣም ከተለመዱ የኢንፌክሽን ዓይነቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ሕመም የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን የሚቋቋሙ ባክቴሪያዎች በበዙበት በዚህ ዘመን እንዴት አድርገን በተሳካ ሁኔታ መከላከል እንችላለን የሚለው አሁንም ጥያቄ ነው።

ቢቢሲ ስለ ሕመሙ ማወቅ ያለብንን እና እንዴት መከላከል እንዳለብን ባለሙያዎችን አናግሯል።

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምክንያት

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሽንት ሥርዓት አካላትን ማለትም ኩላሊትን፣ የሽንት ፊኛን እና የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦዎች አንዳንዴም ኩላሊትን የሚያጠቃ የኢንፌክሽን ዓይነት ነው።

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በአብዛኛው የሚከሰተው በሽንት ማስተላለፊያ ቱቦ (ዩሬትራ) በኩል በሚገባ ባክቴሪያ አማካኝነት ነው።

በተለይም ኢሽሪሺያ ኮላይ (E. coli) የተባለውና በተለምዶ በምግብ መፍጫ ሥርዓታችን ውስጥ የሚገኘው ባክቴሪያ ዋነኛው መንስዔ ነው።

ኢሽሪሺያ ኮላይ የተሰኘው ባክቴሪያ በትልቁ አንጀት (rectum) በኩል ወደ ውስጥ ሊገባ እና ሊወጣ ይችላል።

የሴቶች እና ልጃገረዶች የታችኛው የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦ (ዩሬትራ) ከወንዶች ይልቅ አጭር ስለሆነ ባክቴሪያው በቀላሉ ወደ ሽንት አካላት እንዲገባ በማድረግ የበለጠ ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

ሴቶች ካረጡ በኋላ የኦስትሮጂን መጠናቸው ስለሚወርድ ለሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው።

ኦስትሮጂን በሴቶች ብልት አካባቢ ጤናማ ባክቴሪያዎች ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

ስለዚህ የዚህ ሆርሞን መጠን መቀነስ ለኢንፌክሽን የበለጠ ተጋላጭ ያደርጋል።

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሕመም ምልክት ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ነገር ግን የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ያስቀመጣቸው የተለመዱት ምከልክቶች፡

  • ሽንት በሚሸኑበት ጊዜ ማቃጠል ወይም ሕመም
  • ፊኛ ባዶ ቢሆንም ቶሎ ቶሎ የሽንት መምጣት ስሜት
  • የደፍረሰ፣ መጥፎ ሽታ ያለው ወይም ከደም ጋር የተቀላቀለ ሽንት
  • ከእምብርት በታች ወይም በብሽሽት አካባቢ የቁርጠት ስሜት
  • ከፍተኛ ትኩሳት እና ብርድ ብርድ ማለት፣ ማንቀጥቀጥ
  • የድካም ስሜት

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ያጋጠማቸው አረጋውያን ግራ የመገባት ባሕሪ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ሕጻናት ደግሞ መኝታቸው ላይ መሽናት ወይም ማስመለስ የኢንፌክሽኑ ምልክቶች ናቸው።

ሆዷን የያዘች ሴት በእጇ መድሃኒት ይዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፀረ ባክቴሪያ መድሃኒት የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን ለማከም ይውላሉ

ኢንፌክሽኑ በራሱ ጊዜ ይጠፋል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለንደን በሚገኘው ዊቲንግተን ሆስፒታል የማህጸን እና ጽንስ ስፔሻል እና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ራጅቪንደር ካህስሪያ "የተወሰኑ ሴቶች ምንም ሕክምና አያስፈልጋቸውም። የራሳቸው በሽታ የመከላከል አቅም የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኑ እንዲድን ያደርጋል። የተወሰኑ ሴቶች ደግሞ መድኃኒት መውሰድ ያስፍለጋቸዋል" ብለዋል።

ለምን እነዚህ ሁለት ዓይነት መንገዶች እንደኖሩ ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም።

በዓለም ላይ ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶችን የሚቋቋሙ ባክቴሪያዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን ተከትሎ ተመራማሪዎች ይህንን ጥያቄ ይጠይቃሉ።

ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶች ከሚታዘዙላቸው ሕመሞች መካከል የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ቀዳሚው ሲሆን፣ ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ጥናቶች እየተሠሩ ነው።

ዶ/ር ካትሪን ኬናን በምሥራቅ አፍሪካ ታንዛኒያ፣ ኬንያ እና ኡጋንዳ ውስጥ መድኃኒት የሚቋቋም የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ላይ ጥናት አድርጋለች።

ወደ ሕክምና ተቋም ሕክምና ፈልገው ከመጡ እና ሽንታቸው ለምርመራ ከተወሰደ ሰዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ብቻ ለተለያየ መድኃኒትን በሚቋቋም ኢንፌክሽን ተይዘዋል።

ሐፍረት እና ነውር ነው ተብሎ መታሰቡ ስለ በሽታው እና ምልክቶቹ ከጓደኞቻቸው ጋር እንዳያወሩ እንዲሁም ሕክምና ፍለጋ ወደ ሕክምና ከመሄድ አግዷቸዋል።

ዶ/ር ኬናን "ምልክታቸው በፆታ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል ብለው በማሰብ ወይም ከትዳር አጋራቸው እንደተላለፈባቸው እና ወስልቶባቸው ወይም ሌላ አጋር አለው ብለው ስለሚያስቡ ከሕክምናም ሆነ ከመናገር ይቆጠባሉ" ብለዋል።

"ሰዎች 'ሰውነቴ ላይ ምን ችግር እንዳለብኝ አላውቅም፣ በቃ ከሰውነት ጎዳና ወጥቻለሁ' የሚሉ ገጥመውናል። ከእንዲህ ዓይነት መገለል እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ጋር ነው የሚኖሩት።"

ዕድሜያቸው ከ50 በላይ የሆናቸው እና በሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን የታመሙ ደግሞ ለድብርት፣ ጭንቀት የተጋለጡ መሆናቸውን ዓለም አቀፍ ጥናቶች ያሳያሉ።

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ይጋባል?

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ከሰው ወደ ሰው የማይተላለፍ እና በወሲብ ከሚተላለፉ በሽታዎች መካከል አይደለም።

ይሁን እንጂ ግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም ባክቴሪያ ከፊንጢጣ ወደ ዩሬትራ እንዲገባ ያደርጋል።

የዩኬ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ ወዲያው መሽናት ወደ ሽንት ቱቦ የገባን ባክቴሪያ ለማስወጣት ያግዛል።

በተደጋጋሚ በሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ለሚታመሙ ሰዎች የሕክምና ባለሙያዎች ከግንኙነት በኋላ ወዲያውኑ የሚወስዱት ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት ሊያዙላቸው ይችላሉ።

በናሙና መስጫ ብልቃጥ ሽንት የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሽንት ምርመራ በሽንት ውስጥ የባክቴሪያ ወይም የኢንፌክሽን ምልክቶች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ይረዳል

የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ለማወቅ የሚደረግ ምርመራ

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን ለመመርመር "ምርጡ መላ" የሽንት ምርመራ ማድረግ ሲሆን፣ ይህም የትኛው ባክቴሪያ ኢንፌክሽኑን እንዳስከተለ እና የትኛው መድኃኒት ሊያድነው እንደሚችል በትክክል ለመለየት ይረዳል።

በዚህ ውጤት መሠረት የሕክምና ባለሙያው ታማሚውን የተሻለ ሊረዳው የሚችል የትኛውን ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት መስጠት እንዳለበት ይወስናል።

አንዳንድ ባለሙያዎች ግን ለሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን የሽንት ምርመራ ማድረግ ጊዜው ያለፈበት ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

ከዚያ ይልቅ ዶክተሮች የሕመምተኛዋን ምልክቶች እና የሕክምና ታሪክ ማየት አለባቸው ባይ ናቸው።

የሽንት ምርመራ በአውሮፓውያን 1950ዎቹ በሳይንቲስት ኤድዋርድ ካስ የተገኘ ሲሆን፣ በወቅቱ የኩላሊት ኢንፌክሽን (pyelonephritis) ካለባት ነፍሰ ጡር ሴት በተገኘ መረጃ መሠረት ምርመራው መደረግ ጀምሯል።

ዶ/ር ካህስሪያ "ተመሳሳይ መስፈርት በመውሰድ ነፍሰጡር ያልሆነች ሴትን እንመረምራለን፤ በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶችን፣ ወንዶችን፣ ሕጻናትን፣ ወጣቶችን፣ ማንኛውም ሰውን እንመረምራለን" ይላሉ።

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እንደታመሙ ከጠረጠሩ ከሕክምና ባለሙያ ምን ማድረግ እንዳለብዎ ምክር መጠየቅ ይኖርብዎታል።

ሦስት ብርጭቆ የክራንቤሪ ጭማቂ የክራንቤሪ ፍሬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የክራንቤሪ ጭማቂ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን ያድናል የሚል አመለካከት አለ

በተደጋጋሚ የሚከሰት ኢንፌክሽንን ለመከላከል

25 በመቶ ሴቶች የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በተደጋጋሚ ያጋጥማቸዋል ተብሎ ይገመታል።

በዓመት ሦስት ጊዜ ወይንም በስድስት ወር ሁለት ጊዜ አንዳንዶቹም ከዚያ ከፍ ላለ ጊዜ ይታመማሉ።

ነፍሰጡር ባልሆኑ ሴቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰትን የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በመከላከል ረገድ የክራንቤሪ ጭማቂ ፍቱን መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች ቢኖሩም በሁሉም ተመራማሪዎች ዘንድ ስምምነት የተደረሰበት አይደለም።

የዩኬ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽንን ለመከላከል፡

  • ሽንት ቤት ከተጠቀሙ በኋላ ከፊት ወደ ኋላ ማፅዳት ወይም መጥረግ የባክቴሪያ ሥርጭትን ይከላከላል
  • የብልት አካባቢዎችን ንጹህና ደረቅ ማድረግ
  • በቂ ፈሳሽ፤ በተለይ ውሃ በብዛት መጠጣት። ይህም ባክቴሪያዎችን ከሽንት ሥርዓትዎ ለማስወጣት (ለማስወገድ) ይረዳል።
  • ሽንትዎ ሲመጣ ሳይታገሱ በጊዜ ይሽኑ፤ ፊኛዎንም ሙሉ በሙሉ ባዶ ያድርጉ።
  • ከግብረ-ሥጋ ግንኙነት በፊት እና በኋላ መሽናት በጣም አስፈላጊ ነው።
  • ከጥጥ የተሠሩ እና የማያጣብቁ የውስጥ ልብሶችን (ፓንቶችን) መልበስ

በተደጋጋሚ የሚከሰትን የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ለመከላከል አነስተኛ መጠን ያላቸው ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶችን መውሰድ አማራጭ መሆኑን በእንግሊዝ የሚገኘው ናሽናል ኢንስቲትዩት ፎር ሄልዝ ኤንድ ኬር ኤክሰለንስ ይመክራል።

ስር የሰደደ የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ምንድን ነው?

በተደጋጋሚ የሚከሰት የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እንዳለው ሁሉ ስር የሰደደ የሚባል ወይንም ረዥም ጊዜ የሚቆይ ወይም አብሮ የሚኖር የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንም አለ።

በዚህ ኢንፌክሽን የተያዙ ሰዎች ምልክቶቹን በየቀኑ ያይዋቸዋል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአንዳንድ ሁኔታዎች ባክቴሪያዎች የሽንት ፊኛን በመውረር በሰውነታችን ሴሎች ውስጥ ሊደበቁ ይችላል።

ባክቴሪያዎች ከሽንት ፊኛ ግድግዳ ላይ ራሳቸውን በማጣበቅ ባዮፊልም በመባል በሚታወቀው ተከላካይ ሽፋን ስር ይደበቃሉ። ይህም የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅምን እና ፀረ ተህዋሲያንን ያስወግዳል።

አንድ ሰው ተደጋጋሚ ወይም ሥር የሰደደ የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን እንዴት እና ለምን እንደሚያዳብር ዶ/ር ካህስሪያ እና ሌሎች ተመራማሪዎች ለማወቅ የሚፈልጉት ነገር ነው።

"በሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ላይ በቂ ጥናት ስለተሠራ ብዙ የመረጃ እጥረት ያለ ይመስለናል፤ በሴቶች ጤና ላይ በቂ ጥናት የለም" ብለዋል።