የኩላሊት በሽታን ቀድሞ ለማወቅ የሚረዱ አምስት ምልክቶች እና መፍትሔዎቹ

ኩላሊት

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ኩላሊት በሰውነታችን ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ቆሻሻን ከሰውነት ከማስወገድ ባለፈ የውሃ እና ሌሎች የሰውነት ፈሳሾችን ተግባር ይቆጣጠራሉ።

ኩላሊቶች የደም ግፊትን ይቆጣጠራሉ። ደምን ከሳንባ ወደ ሌላው የሰውነት ክፍል የሚያጓጉዙትን የደም ህዋሳትንም ለማምረት ይረዳሉ።

ስለዚህም የኩላሊታችንን ደኅንነት መጠበቅ ለጤናችን ወሳኝ ስለሆነ አሰፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል። እንዲሁም ለውጦችን ምልክቶችን በመከታተል አስፈላጊውን እርምጃ በጊዜ መውሰድ አለብን።

ይሁን እንጂ ሰዎች ብዙውን ጊዜ አንዳንድ የኩላሊት በሽታ ምልክቶችን ችላ ሲሉ ይታያል። ይህም ቀደም ብሎ ሊታከም የሚችል የኩላሊት ችግር ስር እንዲሰድድ እና ወደ ከባድ ደረጃ እንዲደርስ ሊያደርግ ይችላል።

የሚከተሉትን ምልክቶች ከተመለከትን ሐኪም ማማከር ያስፈልገናል።

የአረፋማ ሽንት

በተደጋጋሚ መሽናት የአንድ ሰው የኩላሊት ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል።

አንድ ሰው አረፋማ ሽንት ከየሚሸና ከሆነ የሽንት ቱቦው ላይ ችግር እንዳለበት የሚያሳይ ምልክት ሊሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ በሽታዎችም ሽንታችንን አረፋማ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ዶክተር ሞህሲን ዋሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አልፎ አልፎ አረፋማ ሽንት መኖሩ ችግር አይደለም። ነገር ግን አንድ ሰው ብዙ ውሃ ከጠጣ በኋላ ሽንቱ አረፋማ መሆኑ ከቀጠለ ሽንቱን በትክክል ማጣራት የማይችል የኩላሊት ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል።

የሰውነት እብጠት

የዓይን እና የእግር እብጠት የኩላሊት ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል። በእግርዎ ላይ እብጠት ካዩ ችላ ሊሉት አይገባም።

አንድ ሰው በእግሩ ላይ ስለሚኖረው እብጠት በጣም መጠንቀቅ አለበት ሲሉ ዶክተር ጋሪማ አጋርዋል ተናግረዋል።

በተመሳሳይም የዓይን፣ የፊት እና የእግር እብጠትም የኩላሊት በሽታ ምልክቶች ናቸው።

የደም ግፊት የሚለካ ሰው
የምስሉ መግለጫ, የደም ግፊትን መቆጣጠር ለኩላሊት ጤና ጠቃሚ ነው

ከፍተኛ የደም ግፊት

እንደ ባለሙያዎች ገለጻ ከሆነ ከፍተኛ የደም ግፊት የብዙ ነገሮች ምልክት ነው።

በሽታው የኩላሊትም ሥራ ይጎዳል። ለዚህም ነው ባለሙያዎች ሰዎች የደም ግፊታቸውን እንዲቆጣጠሩ የሚያስጠነቅቁት።

የስኳር በሽታ

የስኳር በሽታ በዋነኛነት ኩላሊትን ይጎዳል።

ዶ/ር ጋሪማ አጋርዋል እንደሚሉት ከሆነ 80 በመቶው የሚሆኑ የኩላሊት ካንሰር ታማሚዎች የስኳር ህመም አለባቸው።

ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የኩላሊት ችግር ያጋጥማቸዋል።

ለዓመታት የደም ስኳር መጠን ሲጨምር የኩላሊት በሽታ መባባስ ይጀምራል።

የደመ ሰኳር መጠን መመርመሪያ መሳሪያ
የምስሉ መግለጫ, በደም ውስጥ ያለ ስኳር መጠንን በመደብኝነት መመርመር ጠቃሚ ነው

ድካም፣ ማሳከክ እና ማቅለሽለሽ

የድካም ስሜት፣ እጅና እግር ላይ ሕመም እና ተደጋጋሚ የማቅለሽለሽ ስሜት የኩላሊት ችግር ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

እንደ ባለሙያዎች ገለጻ ማሳከክ የሚከሰተው በሰው አካል ውስጥ በሚኖረው በፎስፈረስ እጥረት ምክንያት ነው። የኩላሊት በሽታም የፎስፈረስ እጥረት ሊያስከትል ይችላል።

አንዳንድ የኩላሊት በሽታ ያለባቸው ሰዎች የማቅለሽለሽ ስሜት ስለሚኖራቸው ረሃብ አይሰማቸውም።

ጥንቃቄ የተሞላበት አመጋገብ በሽታን ለመከላከል እንደሚረዳ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በቂ ውሃ መጠጣት እና የጨው እና የስኳር መጠንን መቀነስ የኩላሊት ጤናን ለመጠበቅ ይረዳል ሲሉም ያክላሉ።

የኩላሊት ጤናን ለማሻሻል የሚረዱ መንገዶች

ውሃ መጠጣት

የፎቶው ባለመብት, AFP

በቂ ውሃ መጠጣት

ውሃ በኩላሊት ጤና ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ብዙ ውሃ ከጠጣን ኩላሊታችን ብዙ ሽንት እንዲያመርት ስለሚያደርግ ጎጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ከደማችን ያስወግዳል።

የኩላሊት ጠጠር ስጋትንም ይቀንሳል። አንድ ሰው በቂ ውሃ ከጠጣ ሽንቱ ነጣ ያለ ቢጫ ወይም ቀላል ቢጫ ቀለም ይኖረዋል።

እንደ ዶ/ር ጋሪማ አጋራዋል ከሆነ አንድ ሰው በየቀኑ ከሁለት እስከ ሁለት ተኩል ሊትር ውሃ መጠጣት አለበት።

ጨው ይቀንሱ

ጨው አብዝቶ መመገብ ለጤና ጥሩ አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ ለደም ግፊት እና ለኩላሊት በሽታ ተጋላጭነትን ስለሚጨምር ነው።

ጨው የበዛባቸው የተጠበሱ ምግቦችን ያስወግዱ።

ጨው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በምግባችን እና በመጠጣችን ውስጥ የምንጠቀማቸውን የጨው መጠን በመቀነስ መቆጣጠር

ስኳር ይቀንሱ

የኩላሊት በሽታን ለማስወገድ ከፈለጉ ትንሽ ስኳር ይመገቡ።

ከስኳር መራቅ ደግሞ የተሻለው አማራጭ ነው።

እንደ ኬክ እና ቸኮሌት ያሉ ነገሮች የተጣራ ስኳር አላቸው። ስኳር የኩላሊት በሽታ እና ከመጠን ያለፈ ውፍረት የመፈጠር ዕድልን ይጨምራል።

ስብ ይቀንሱ

ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ከሆነ አንድ ሰው ክብደት መቀነስ አለበት። ከመጠን በላይ ወፍራም የሆኑ ሰዎች ለኩላሊት በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

ቆሻሻን ከሰውነት ውስጥ ለማስወገድ ስለሚረዳ መደበኛ እና መካከለኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግም አስፈላጊ ነው።

አንድ ሰው 50 ዓመት ከሞላው በኋላ በስኳር በሽታ እና በደም ግፊት የመያዝ ዕድሉ ይጨምራል።

ጤናማ ምግብ መመገብ

አትክልት፣ ሾርባ እና ፍራፍሬዎችን ይመገቡ። የተጠበሱ ምግቦችን ያስወግዱ።

በቂ ውሃ መጠጣት፣ ጤናማ አመጋገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለኩላሊት እና ለሌሎችም የሰውነት ክፍሎች ጤና ጠቃሚ ነው።

በሐኪም ያልታዘዙ መድኃኒቶችን አይውሰዱ

ዶ/ር ጋሪማ አጋራዋል እንደሚሉት ከሆነ "ሰዎች ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒት ገዝተው ሲወስዱ እናያለን።"

አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን በተደጋጋሚ እንደሚወስዱ አክለዋል።

"አረጋውያን የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን ይወስዳሉ። አንዳንዶቹ ግን ኩላሊት ላይ ችግርን ይፈጥራሉ" ሲሉ አክለዋል።

ስለዚህም በሐኪም ያልታዘዙ መድኃኒቶችን አይውሰዱ፤ የሕመም ማስታጋሻዎችን በተደጋጋሚ ለመውሰድ የሚያስገድድዎ ሁኔታ ካለ ሐኪም ማማከር ይጠቅማል።