የሰው አካል ንቅለ ተከላ በማድረግ ዕድሜን ማራዘም ይቻላል?

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የሰው አካል ንቅለ ተከላ በማድረግ ዕድሜን ማራዘም ይቻል ይሆን?
የሕይወት ዘመንን በማስቀጠል ሞትንስ ለተወሰነ ጊዜ መሸወድ ይቻላል?
የአካል ንቅለ ተከላ በማድረግ ዕድሜን ማራዘም ከሰሞኑ በቻይና የተገናኙት የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያልተጠበቀ የውይይት ርዕስ ነበር።
ሁለቱ መሪዎች በንቅለ ተከላ የሕይወት ዘመንን ስለማስቀጠል እየተወያዩ የነበሩት ቻይና ጃፓንን ድል የተቀዳጀችበት 80ኛው ዓመት የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ መታሰቢያ ላይ በነበረ ታላቅ ወታደራዊ ትዕይንት ላይ ነው።
ለፑቲን በቻይና ዋነኛ ቋንቋ ወደ ሆነው ማንዳሪን እያስተረጎመ የነበረው ግለሰብ ለፕሬዝዳንት ዢ የሰው አካል ንቅለ ተከላ በተደጋጋሚ ማድረግ ይቻላል አላቸው።
ፑቲን አክለውም በዚህም ንቅለ ተከላ "ሰው ዕድሜው ቢጨምርም ወጣት እየሆነ እና ለዘለቄታውም እርጅናን መካላከል እንዲያስችል ለማድረግ" ነው ሲሉ ተናገሩ።
"በዚህ ክፍለ ዘመን እስከ 150 ዓመት ድረስ መኖር እንደሚቻል ተተንብይዋል" ሲሉ አከሉ።
መሪዎቹ ተያዩ እና ፈገግ አሉ። በሳቅ የታጀበ ንግግራቸው ቀልድ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።
ነገር ግን ከዚህ ውይይታቸው ጀርባ ምን አለ?
የሰው አካል ንቅለ ተከላ ሕይወትን ይታደጋል?
በዩናይትድ ኪንግደም ያለውን አሃዝ ብቻ ብንወስድ ባለፉት 30 ዓመታት የ100 ሺህ ሰዎችን ሕይወት መታደግ እንደተቻለ የአገሪቱ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት የደም እና የሰውነት አካል ንቅለ ተከላ ክፍል አስታውቋል።
ዓለማችን በሕክምና እና በቴክኖሎጂ ያሳየችው ልኅቀት በንቅለ ተከላ የተተኩ የሰውነት ክፍሎች በሰዎች ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ እየቆዩ ነው።
አንዳንድ ታካሚዎች በንቅለ ተከላ ያገኙት ኩላሊት ለ50 ዓመታት አገልግሏቸዋል።
የተለገሰው የሰውነት አካል የሕይወት ዘመን ተቀባዩ ምን ያህል ጤነኛ እንዲሁም እንዴት ነው የሚንከባከበው በሚለው የሚወሰን ይሆናል።
ለምሳሌ በሕይወት ካለ ለጋሽ የሚገኝ ኩላሊት ከ20 እስከ 25 ዓመታት ድረስ ግልጋሎት ሊሰጥ ይችላል።
ሆኖም ይህ ኩላሊት የተገኘው ከሞተ ለጋሽ ከሆነ ዕድሜው ከ15 አስከ 20 ዓመታት በሚደርስ ጊዜ ዝቅ ይላል።
በተጨማሪም የሚለገሰው የሰውነት አካሉም ዓይነት ይወስነዋል።
ተለግሰው በንቅለ ተከላ ወደ ሌላ ሰው አካል ውስጥ ከገቡ በኋላ፤ ጉበት እስከ 20 ዓመት፣ ልብ እስከ 15 ዓመት እንዲሁም ሳንባ እስከ 10 ዓመት ድረስ እንደሚያገለግሉ በጆርናል ኦፍ ሜዲካል ኢኮኖሚክስ የታተመ ጥናት ያሳያል።

ንቅለ ተከላ ለዘላለማዊ ሕይወት ቲኬት?
ፑቲን እና ዢ እየተነጋገሩ የነበሩት በርካታ የሰውነት አካል ክፍሎችን ያውም በተደጋጋሚ ንቅለ ተከላ ማድረግን ነው።
ሆኖም ቀዶ ሕክምና ቀላል ነገር አይደለም።
አደጋው ሕይወትን የሚያሳጣም ጭምር ነው።
በንቅለ ተከላ የቀዶ ሕክምና የሚከናወንላቸው ሰዎች 'ኢሚውኖሰፕረሳንት' የተሰኙ ሰውነታቸው አካሉን ውድቅ እንዳያደርገው ወይም እንዳያጠቃው የሚከላከሉ መድኃኒቶች እስከ ሕይወታቸው መጨረሻ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
እነዚህ መድኃኒቶችም ከፍተኛ የደም ግፊት እንዲሁም የኢንፌክሽን ስጋቶችን የሚጨምሩ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊኖራቸው ይችላል።
ሌላኛው ሊከሰት የሚችለው ሰውነት በንቅለ ተከላ የገባውን አካል አልቀበልም የማለት ነው።
በሰውነታችን ውስጥ በሽታን የሚከላከለው ሥርዓት በንቅለ ተከላ የተዘዋወረውን አካል ባዕድ ነው በሚል ማጥቃት ሲጀምር ነው ይህ ያለመቀበል አጋጣሚ የሚፈጠረው።
ይህ ሁኔታም የመከላከያ መድኃኒቶችንም እየወሰዱም ቢሆን ሊያጋጥም ይችላል።
በሰዎች ልክ የተሠሩ የሰውነት አካላት
ሳይንቲስቶች እነዚህ 'ኢሚውኖሰፕረሳንት' መድኃኒቶች የሚቀሩበትን መንገድ እየዘየዱ ይገኛሉ።
ዘረ መላቸው የተሻሻሉ አሳማዎችን በለጋሽነት ለመጠቀም እየሞከሩ ነው።
ክሪሰፕር የተሰኘ የዘር ማስተካከያ (ማሻሻያን) መሳሪያን በመጠቀም የተወሰኑትን የአሳማ ዘረ መሎች በማስወገድ የሰው ዘረ መሎች በመጨመር የሰውነት አካሉ የበለጠ እንዲጣጣም ለማድረግ እየጣሩ ነው።
የአሳማዎች የሰውነት አካል ከሰዎች አካል መጠን ጋር ተቀራራቢ በመሆኑም ለዚህ ተግባር የሚውሉ አሳማዎችን ማርባት ተመራጭ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ሳይንሱ አሁንም በሙከራ ላይ ቢሆንም በዚህ የአሳማ እና የሰው ዘረ መሎችን በማዋሃድ እና በማስተካከል መንገድ የልብ እና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ተደርጓል።
በዚህ መንገድ ንቅለ ተከላ እንዲደረግላቸው የተስማሙት ወንዶች በዚህ የሕክምና ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ሆነዋል። ሁለቱም ግለሰቦች ከንቅለ ተከላው በኋላ ሕይወታቸው አልፏል።
ሆኖም 'ዜኖትራንስፕላንቴሽን' የተሰኘውን ህዋሳትን ወይም የአካል ክፍሎችን ከአንድ ዝርያ ወደ ሌላ ዝርያ የሚደረግ ንቅለ ተከላ እንዲልቅ ረድተዋል።
ሌላው ምርምር እየተደረገበት ያለው የራሱን የሰውየውን ህዋሳት በመጠቀም አዳዲስ የሰውነት አካል ክፍሎችን ለማሳደግ የሚደረገው ሙከራ ነው።
ስቴም የተሰኙት ህዋሳት (ሴሎች) ወደ ተለያዩ የህዋሳት ዓይነቶች ወይም ኅብረ ህዋስ (ቲሹ) የማደግ ችሎታ አላቸው።

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images
እስካሁን ድረስ የትኛውም የምርምር ቡድን ከእነዚህ ህዋሳት ሙሉ በሙሉ የሚሠራ በንቅለ ተከላ የሚዘዋወሩ የሰው አካላትን መሥራት አልቻሉም።
ነገር ግን ሳይንቲስቶች ይህንን ለማከናወን እየተቃረቡ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2020 የዩናይትድ ኪንግደም ተመራማሪ የሆኑት ዩሲኤል እና ፍራንሲስ ክሪክ ተቋም የሰውነታችን በሽታ በመከላከል ሥርዓት መሠረታዊ አካል የሚባለውን 'ታይመስን' ከሰው የስቴም ህዋሳት መሥራት ችለዋል።
ለሙከራ በአይጥ ላይ ንቅለ ተከላ የተደረገ ሲሆን እየሠራም ነበር።
በለንደን የሚገኘው የግሬት ኦርሞንድ ስትሪት ሆስፒታል ሳይንቲስቶች በበኩላቸው የአንድ ታካሚ ኅብረ ህዋስን (ቲሹ) በመጠቀም የሰውን የአንጀት ክፍል መሥራት መቻላቸውን አስታውቀዋል።
ይህም ለወደፊቱ የአንጀት ችግር ላለባቸው ህጻናት የተስማሙ ንቅለ ተከላዎችን ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተነግሯል።
እነዚህ ሁሉ የሕክምና የሳይንስ ልኅቀቶች የታመሙ ሰዎችን ለማከም እንጂ ሰዎች እስከ 150 ዓመት ዕድሜ ድረስ እንዲቆዩ ለማድረግ አይደለም።
ሆኖም በቴክኖሎጂ የሥራ ፈጠራ ላይ የተሰማራው ብርያን ጆንሰን በበኩሉ በዚህች ዓለም ላይ የሚኖርበትን ዕድሜ ለማስረዘም በዓመት ሚሊዮን ዶላሮችን እያጠፋ ነው።
እስካሁን ድረስ እኛ እስከምናውቀው ድረስ አዳዲስ የሰውነት አካሎችን በንቅለ ተከላ አላስገባም።
ነገር ግን የ17 ዓመቱን ልጅ ፕላዝማ በሕክምና እየተጠቀመ ነበር።
ፕላዝማ በደማችን ውስጥ 55 በመቶ የሚሆነውን የደም ህዋሳት፣ ፕሮቲን እና ሌሎች ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ነው።
ሆኖም ቱጃሩ የቴክኖሎጂ ፈጣሪ በሰውነቱ ላይ የጎላ ጥቅም ባለማየቱ እንዲሁም የአሜሪካው የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር ከመሳሰሉ ድርጅቶች የሕክምና ጥያቄዎች ጫና መበራከቱን ተከትሎ ግለሰቡ ይህንን አቁሟል።
በለንደን የኪንግስ ኮሌጅ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ጁሊያን ሙትዝ የሰውነት አካላትን ንቅለ ተከላ ከማድረግ ባለፈ እንደ ፕላዝማ ያሉትን ለመተካት ምርምር እየተደረገ ነው ይላሉ።
"እነዚህ የምርምር ውጤቶች የሰውን ልጅ የሕይወት ዘመንን የማስቀጠል ያውም በከፍተኛ ደረጃ ለሚለው በእርግጠኝነት የተረጋገጠ ነገር የለም። ሆኖም ሳይንስ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ፍላጎት ስላለው ምርምሩ ይቀጥላል" ብለዋል።
በኤድንብራ ዩኒቨርስቲ የሮዝሊን ተቋም የበሽታ መከላከያ ሕክምና (ኢሚዩኖፓቶሎጂ) ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ኒል ማቦት በበኩላቸው የሰው ልጅ እስከ 125 ድረስ መኖር የዕድሜ ጣሪያው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
እስካሁን ድረስ በዕድሜ ትልቅነታቸው የተረጋገጠው በአውሮፓውያኑ 1875-1997 ድረስ ለ122 ዓመት የኖሩት ፈረንሳያዊቷ ጂን ካልሜንት መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደከሙ ወይንም በሕመም የተጎዱ የሰውነት አካሎቻችንን በንቅለ ተከላ መተካት ይቻል ይሆናል።
ነገር ግን ዕድሜያችን እየገፋ በሄደ ቁጥር የሰውነታችን የመቋቋም አቅሙ እየቀነሰ ይሄዳል።
"ሰውነታችን በኢንፌክሽኖች ሲጠቃ የሚሰጠው ምላሽ እየቀነሰ፣ ሰውነታችን እየተዳከመ እንዲሁም ለጉዳት ተጋላጭ እየሆንን እና ከሕመሞች ማገገም እያቃተን ይመጣል" ይላሉ።
ከባድ የሆነው የሰውነት ንቅለ ተከላ እንዲሁም የተተከለውን አካል ሰውነት ውድቅ እንዳያደርገው የሚወሰዱ መድኃኒቶች ዕድሜያቸው ከፍ ባሉ ታማሚዎች ላይ የሚኖራቸው ውጤትቸው የከፋ እንደሚሆንም ያስረዳሉ።
የሕይወት ዘመንን ከማስቀጠል ወይም ዕድሜን ማራዘም ላይ ከማተኮር ይልቅ የምንኖረውን ሕይወት ጤናማ ማድረግንም ይመክራሉ።
"ረጅም ዕድሜ መኖር ነገር ግን በተጻራሪው ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ በሚመጡ በርካታ በሽታዎች መሰቃየት እና ተደጋጋሚ ንቅለ ተከላዎችን ለማድረግ ሆስፒታል በመመላለስ የጡረታን ሕይወት በዚህ መንገድ ለማሳለፍ አጓጊ አይመስለኝም" ሲሉ ፕሮፌሰር ማቦት ያስረዳሉ።















