ትራምፕ የኤፍቢአይ ወኪሎች የፍሎሪዳ መኖሪያ ቤታቸውን ‘እንደፈተሹ’ ተናገሩ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፍሎሪዳ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በኤፍቢአይ አባላት መከበቡን እና ካዝናቸው መስበሩን ተናገሩ።

ትራምፕ በሰጡት መግለጫ በፓልም ቢች የሚገኘው ማር-ኤ-ላጎ በተባለው ቤታቸውን “በርካታ የኤፍቢአይ ወኪሎች ተገኝተዋል” ብለዋል።

ፍተሻው ከትራምፕ የመንግሥታዊ ሰነዶች አያያዝ ጋር በተገናኘ ነው ተብሏል።

ይህ የተከሰተው ትራምፕ እአአ በ2024 ለሦስተኛ ጊዜ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ሆነው ለመቅረብ ሲዘጋጁ ነው።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው ሰኞ ዕለት ፍተሻው በተካሄደበት ወቅት ትራምፕ በኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው ትራምፕ ታወር ነበሩ።

“እነዚህ ዓመታት ለአገራችን የጨለማ ጊዜያት ናቸው” ሲሉ የተናገሩት ትራምፕ፣ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ትብብር ማድረጋቸውን ገልጸው “በቤቴ ላይ የተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ አላስፈላጊ ወይም ተገቢ አይደለም” ብለዋል።

በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት እንዳይወዳደሩ ለማድረግ “የሕግ ጥሰት መፈጸም” እና “የፍትህ ሥርዓቱን እንደመሳሪያ መጠቀም” ነው የተከናወነው ብለዋል።

“እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ሊፈጸም የሚችለው ደካማ መንግሥት ባላቸው የሦስተኛ ዓለም አገራት ብቻ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ አሜሪካ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በሙስና ከተዘፈቁ አገራት አንዷ ሆናለች” ብለዋል።

“ካዝናዬን ጭምር ሰብረውታል” ሲሉም ገልጸዋል። 

የፕሬዝዳንቱ ሁለተኛ ልጅ ኤሪክ ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት ኤፍቢአይ በትራምፕ የማር-አ-ላጎ ቤት ላይ የሚደረገው ፍተሻ ከብሔራዊ የመዛግብት አያያዝ ጋር ካለው ምርመራ ጋር የተያያዘ ነው።

ፕሬዝዳንታዊ መዝገቦችን የሚያስተዳድረው የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት በየካቲት ወር ትራምፕ ኦፊሴላዊ ሰነዶችን ስለሚይዙበት መንገድ የፍትህ ክፍሉ ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ብሔራዊው ቤተ መዛግብቱ ከማር-አ-ላጎ 15 ሳጥኖችን ማውሰዱን አስታውቋል። 

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ደብዳቤዎቻቸውን፣ የሥራ ሰነዶቻቸውን እና ኢሜሎቻቸውን ወደ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እንዲያስተላልፉ በሕግ ይገደዳሉ።

ባለሥልጣናት የቀድሞው ፕሬዝደንት በሕገ-ወጥ መንገድ ብዙ ሰነዶችን ቀደዋል ብለዋል።

አንዳንዶቹም አንድ ላይ ተጣብቀው መያያዝ ነበረባቸው ሲል ቤተ መዛግበቱ ይገልጻል። ትራምፕ በወቅቱ ኦፊሴላዊ የሆኑ መዝገቦችን በትክክለኛው መንገድ አልያዙም መባሉን “ሐሰተኛ ዜና” በማለት ውድቅ አድርገውታል።

በፓልም ቢች ከፍተኛ የትራምፕ አማካሪ የሆኑ ግለሰብ ለሲቢኤስ እንደተናገሩት በማር-አ-ላጎ ላይ በፌዴራል ወኪሎች የተደረገው ፍተሻ ፕሬዝዳንታዊ መዛግብት ላይ ያተኮረ ነበር።

“ትኩረቱ የፕሬዝዳንት ሪከርድ ሕግ ነው” ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የትራምፕ ምንጭ ተናግረዋል።

“በዚህ ሕግ ምክንያት ፍተሻ መከናወኑን ሰምተው ያውቃሉ?”

ምንጩ አክለውም “እነሱ (ኤፍቢአይ) ባልደረቦች በቅርቡ ነው ቤቱን ጥለው የሄዱት። ጥቂት ነገር ነው ያገኙት” ብለዋል።

የፌዴራል ፍተሻ ማዘዣ በዳኛ መፈረም አለበት። የሕግ አስከባሪ ተቋማት ፍተሻው ሕገ-ወጥነትን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሊኖራቸው ይገባል ።

ስማቸው ያልተጠቀሰ የሕግ አስከባሪ ለሲቢኤስ እንደተናገሩት የትራምፕ ጠባቂዎች የፍተሻ ማዘዣው ቀደም ብሎ እንደደረሳቸው እና የኤፍቢአይ መርማሪዎች ተናግረዋል።

በርካታ ሣጥኖች ተወስደዋል ያለው የመረጃ ምንጩ በሮች አለመሰበራቸውን እና ፍተሻው ከሰዓት በኋላ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

አንድ ከፍተኛ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣን ለሲቢኤስ እንደተናገሩት ኤፍቢኤይ ​​ትራምፕ ቤት ላይ ስላደረገው ፍተሻ የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ምንም አይነት ማሳወቂያ አልደረሰውም።

ስለ ጉዳዩ በይፋ የመናገር ፍቃድ ያልተሰጣቸው ባለሥልጣኑ “በቅድሚያ አልተነገረንም። አንዳንዶች ከመገናኛ ብዙኃን ሌሎች ደግሞ ከማኅበራዊ ሚዲያ ነው የሰሙት” ብለዋል። 

የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዋይት ሐውስ ማንኛውንም አይነት የፖለቲካ ጫና ወይም ተገቢ ያልሆነ ፍንጭን ለማስቀረት ከከፍተኛ የፍትህ ባለጅልጣናት ጋር ያለውን ግንኙነት ገድቧል።

ባይደን ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ከፍትህ ጉዳዮች ለመውጣት ቃል ገብተዋል። ፕሬዚዳንቱ እና ቤተሰባቸው የፌደራል ዐቃቤ ሕጎች ልጃቸውን ሃንተር ባይደን በግብር ማጭበርበር ወይም በሌላ የፌደራል ክሶች መከሰሳቸውን ለማየት እየጠበቁ ናቸው።

ከብሔራዊ ቤተ መዛግብት በተጨማሪ የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ኮሚቴ እአአ ጥር 6/2021 በካፒቶል አመጽ ዙሪያ ትራምፕ የወሰዱትን እርምጃ እየመረመረ ነው።

የትራምፕ በርካታ ደጋፊዎቻቸው የሕግ አውጪ አካላት በተሰበሰቡበት ወቅት በስፍራው ተገኝተው ብጥብጥ ፈጥረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የፍትህ ሚኒስቴር ትራምፕ በ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ላይ ያቀረቡትን ጥያቄ እየመረመረ ነው። ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሜሪክ ጋርላንድ "ሁሉንም ሰው" ተጠያቂ ለማድረግ ማሰባቸውን ተናግረዋል።

በፉልተን ካውንቲ ጆርጂያ የሚገኘው ዓቃቤ ህግ ትራምፕ እና አጋሮቻቸው በግዛቱ በ2020 ምርጫ ውጤቶች ላይ ጣልቃ ለመግባት ሞክረው እንደሆነ ለማወቅ እየመረመረ ነው።