በስህተት የጣለውን ቢትኮይን በ13 ሚሊዮን ዶላር እያፈላለገ ያለው ግለሰብ

ከ10 ዓመታት በፊት ነው። ጄምስ ሃዌልስ ያስቀመጠውን ቢትኮይን ረስቶ የኮምፒውተሩን የመረጃ ቋት (ሃርድ ድራይቭ) አውጥቶ ጣለው።
ጄምስ ተዝናግቶ የወረወረው ቢትኮይን ዘንድሮ ባለው ገበያ 184 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጣ ይችላል።
ይህ የከነከነው ጄምስ ከዓመታት በፊት የጣለውን ቢትኮይን ሚሊዮን ዶላር ከፍሎ ሊያስቆፍረው አስቧል።
የሰውዬው ‘ሃርድ ድራይቭ’ ኒውፖርት በተሰኘችው የዩናይትድ ኪንግደም ከተማ ቆሻሻ መጣያ ሥፍራ ይኖራል ተብሎ ተገምቷል።
ጄምስ ይህ ውድ ቁስ ከተገኘለት ከቢትኮይኑ 10 በመቶውን ቆንጥሮ ከተማዋን የክሪፕቶከረንሲ ማዕከል ለማድረግ ቃል ገብቷል።
ነገር ግን የከተማዋ ምክር ቤት የቆሻሻ መጣያውን መቆፈር ሥነ-ምኅዳራዊ (ኢኮሎጂካል) ቀውስ ያስከትላል እያለ ነው።
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) ባለሙያው ጄምስ ከዘጠኝ ዓመት በፊት በፈረንጆቹ 2013 ነበር፤ 8 ሺህ ቢትኮይን ያቀፈውን ሃርድ ድራይቭ ጠርጎ የጣለው።
ወቅቱም ቢትኮይን የተሰኘው ዲጂታል የመገበያያ ገንዘብ ብቅ ብቅ ማለት የጀመረበት ነበር።
ቢትኮይን ገበያው ላይ የሚታወቀው በሚዋዥው ዋጋው ነው።
ለምሳሌ የጄምስ ቢትኮይን ዋጋ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት [2021] 256 ሚሊዮን ዶላር ደርሶለት ነበር።
ነገር ግን ከዘንድሮው ዓመት መባቻ ጀምሮ ዋጋው አሽቆልቁሏል።
ጄምስ በተደጋጋሚ ለኒውፖርት ከተማ ምክር ቤት ቆሻሻ ማከማቻው ይቆፈርልኝ ብሎ ቢያመልክትም ጥያቄው ሰሚ አጥቷል።
ይህ ያታከተው ግለሰብ አሁን ሃርድ ድራይቩ ከተገኘ 10 በመቶ ገቢውን ለከተማዋ የክሪፕቶከረንሲ ማስፋፊያ ለመስጠት ወስኗል።
ነገር ግን የጄምስን መዳፍ የምታክል ቁስ ለማግኘት ሲል ከተማ አስተዳደሩ በርካታ ወጪ አውጥቶ ለዓመታት የተከማቸውን ቆሻሻ ይቆፍር እንደሁ አልታወቀም።
ከተማ አስተዳደሩ የቆሻሻ ማከማቻውን ማመስ አካባቢውን ሊበክለው ይችላል የሚል ስጋት አለው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጄምስ ደግሞ “እኔ ማከማቻውን የማስቆፈር አቅም እንዲሁም አደጋ ሳያደርስ የሚያስስ ባለሙያ አለኝ” ይላል።
“እርግጥ ነው ቆሻሻ ማከማቻ መቆፈር ራሱን የቻለ ትልቅ ሥራ ነው” ይላል ጄምስ።
“ነገር ግን ማስቆፈሪያ ወጪውን እችላለሁ። የሰው-ሠራሽ ልኅቀት [አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ] ባለሙያ አስመጥተናል። ሃርድ ድራይቩን ነቅሎ የሚያወጣ ቴክኖሎጂ አለ።”
ግለሰቡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከበቢያዊ አደጋን የሚመረምር ቡድን ማዘጋጀቱን ይገልጣል።
“በሁሉም ዘርፍ የተካኑ ልምድ ያላቸው ሙያተኞች ይዣለሁ። ከተፈቀደላቸው ይህንን ሥራ በብቃት መከውን የሚችሉ ናቸው።”
ነገር ግን ሃርድ ድራቩን ማግኘት ብቸኛው ሥራ አይደለም። ይህ የመረጃ ማከማቻ ቁስ ቢገኝ እንኳ ለመሥራቱ ማስተማመኛ የለም።
ይህ በርካታ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን ያቀፈው ቁስ ቢገኝ ጄምስ ሚሊየነር ይሆናል። ነገር ግን የቢትኮይንን የገበያ ዋጋ መገመት ከባድ ነው።
ቢሆንም የ37 ዓመቱ ግለሰብ የበርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ባለቤት ሊሆን ይችላል።
ጄምስ ገንዘቡ ተቆፍሮ ይውጣለት እንጂ፣ ያደገባትን ከተማ የክሪፕቶከረንሲ ማዕከል ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል።
“ሕብረተሰቡን የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ዕቅድ አስቀምጫለሁ” ይላል።
“አንደኛው ሥራ የቆሻሻ ማከማቻውን ማዘመን ነው። ከተቻለ በአካባቢው በነፋስ ኃይል የሚሠራ የኤሌክትሪክ ማመንጫ እንገነባለን።”
የኒውፖርት ማኅበረሰብ የሚጠቀምበት የክሪፕቶከረንሲ ገበያ ለመዘርጋት ነው የጄምስ ዓላማ።
ለእያንዳንዱ የኒውፖርት ነዋሪ 61 ዶላር ዋጋ ያለው ቢትኮይን ለመስጠትም ቃል ገብቷል። በተከማዋ ዋና ዋና ቦታዎች ደግሞ ክሪፕቶ ላይ የተመሠረቱ ፌርማታዎች ለመግንባትም አስቧል።
የኒውፖርት ከተማ ምክር ቤት ግን በተደጋጋሚ የሰውዬውን ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል።
የከተማዋ ቃል አቀባይ “ቆሻሻ ማከማቻን በተለመከተ የተቀመጠ ሕግ አለን። ይህን ሕግ መከተል አለብን” ብለዋል።
“አንደኛው ጉዳይ ይህ የቆሻሻ ማከማቻ ከተቆፈረ በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ የሚያደርሰው ሥነ ምኅዳራዊ አደጋ ነው። የጄምስ ዕቅድ ደግሞ ይህን አደጋ የሚያስከትል ነው። ይህን ልንቀበለው አንችልም። በሕጉ መሠረት እንዲያውም ከግምት ውስጥ ልናስገባው የምንችለው ሐሳብ አይደለም።”













