የንጉሥ ቻርለስ የኬንያ ጉብኝትና የማኦ ማኦ አርበኞች ቅሬታ

በማኦ ማኦ የነጻነት ትግል ሺዎች በቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ወታደሮች ተገድለዋል

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, በማኦ ማኦ የነጻነት ትግል ሺዎች በቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ወታደሮች ተገድለዋል

ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ እና ባለቤታቸው ካሚላ በኬንያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ነው። አራት ቀናትን ይዘልቃል።

የንጉሡን ጉብኝት ተከትሎ ያመረቀዘ ቁስል አለ። በቅኝ ግዛት ወቅት ስለሞቱ፣ ስለቆሰሉ፣ ስለተሰቃዩ ኬንያዊያን ጉዳይ ‘ይፋዊ ይቅርታ’ ይጠበቃል።

እንግሊዝ ቅኝ አገሪቱን ቅኝ በያዘችበት ዘመን ወደ 10ሺህ ሰዎች እንደተገደሉ፣ ሌሎች ብዙ ሺዎች ደግሞ መልከ ብዙ ሰቆቃ እንደደረሰባቸው ይታወቃል።

በተለይም የማኦ ማኦ የነጻነት ንቅናቄ አመጽ በ1950ዎቹ ሲፋፋም ብዙዎች ተገድለዋል።

በ2013 ዓ/ም ብሪታኒያ ለደረሰው ሞትና ሰቆቃ ይቅርታ ጠይቃ ስታበቃ 24 ሚሊዮን ዶላር ለተጎጂ ቤተሰቦች ካሳ ሰጥታ ነበር። ተጎጂዎቹ ወደ 5ሺ የሚጠጉ ነበሩ። ይህ ግን በቂ አይደለም ይላሉ ብዙዎች።

ከነዚህ መሀል የ90 ዓመቷ አርበኛ ሙቶኒ ይገኙበታል።

በመካከለኛው ኬንያ ሻማታ የሚገኘውን የመቃብር ሥፍራ ሲያስጎበኙን በሐዘን ውስጥ ሆነው ነበር።

የባለቤታቸው መቃብር የሚገኝበትን ሥፍራ አረም ወሮታል። ባለቤታቸው አርበኛ ኤሊያ ኪንዩዋ የሞቱት በ93 ዓመታቸው ከ2 ዓመት በፊት ነበር።

ባለቤታቸው በትግል ስማቸው ጄኔራል ባሓቲ ይባሉ ነበር። ልክ እንደርሳቸው ጦረኛ አርበኛ ነበሩ።

በተለይም በማኦ ማኦ አመጽ ሲቀጣጠል እሳቸውና ባለቤታቸው ብዙ ተዋድቀዋል።

እማማ ሙቶኒ በማኦ ማኦ ትግል ወቅት ሻለቃ ማዕረግ ነበራቸው።

እማማ ሙቶኒ የጋብቻ ቀለበታቸውን ሲያሳዩን ፊታቸው በፈገግታ በራ። የተገናኙት አመጹ አብቅቶ ባለቤታቸው ከእስር ሲለቀቁ ነበር።

“እንደኔ አርበኛ የሆነች ጀግኒት ካለች ላገባት እፈልጋለሁ አለ፤ ምክንያቱም እኔንም ሕመሜን ትረዳለች”

ባለቤታቸውና እሳቸው ከዚያ በኋላ ተጋቡ። ትግሉ አጣመራቸው።

ይሁንና ሁለቱ አርበኞች ኬንያ ነጻ ከወጣች በኋላም ሕይወታቸው አልተለወጠም። ብዙዎቹ የማኦ ማኦ አርበኞችም ይኸው ነው የገጠማቸው።

ማኦ ማኦ የነጻነት ተፋላሚ ቡድን ለረዥም ዘመን ሕገ ወጥ በሚል ተፈርጆ ነው የኖረው።

 የ90 ዓመቷ አርበኛ ሙቶኒ
የምስሉ መግለጫ, የ90 ዓመቷ አርበኛ ሙቶኒ

በቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ አሸባሪ ድርጅት ተብሎም ተፈርጆ ነበር። ይሁንና ከነጻነት በኋላም ይኸው ፍረጃ ሳይነሳለት ቀረ።

“ለምሳሌ ሦስት የማኦ ማኦ አባላት መገናኘት አይችሉም፤ ክልክል ነበር። “ይላሉ የሕግ አዋቂና ፖለቲከኛው ፓል ሙቲ።

ይህ ፍረጃ የተነሳው በ2003 እንደ አውሮፓዊያኑ ነበር።

ከዚያ ወዲህ ነው የማኦ ማኦ አርበኞች አሸባሪ ሳይሆኑ የነጻነት ተፋላሚዎች ተደርገው የታዩት።

ይህ ብዙ ችግር አምጥቶባቸዋል። በአገሪቱም በትውልዱም የተሰጣቸው ቦታ እንዲያንስ አድርጓል።

“በርካታ የአሁን ልጆች ኬንያ በቅኝ ገዢዎች ምን ያህል አበሳዋን እንዳየች አያውቁም “ትላለች ካሮላይን ኤልኪንስ። ካሮላይን በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት አድርጋለች በ90ዎቹ።

የሷን ጥናት ምልከታ ዛሬ በናይሮቢ ጎዳናዎች ገሃድ ወጥቶ ማየት ይቻላል።

ብዙ የዛሬ ወጣት ኬንያዊያን ስለ ማኦ ማኦ አያውቁም፤ አባላቱ ያዩትን ፍዳና መከራ በጭራሽ አይረዱም። እነሱ አሁን የሚያሳስባቸው ምጣኔ ሀብቱና የንጉሥ ቻርለስ ጉብኝት አንዳች የሚያመጣው ለውጥ ይኖር ይሆን የሚለው ነው።

ዋቺራ ጊቱኢ ለምሳሌ የአርበኛዋ የልጅ ልጅ ነው። አሁን 36 ዓመቱ ነው። ስለ ማኦ ማኦ ከአያቱ ሰምቷል። ይሁንና ቅኝ ግዛት ለአሁኗ ኬንያ መመሰቃቀል ያለውን ተጽእኖ አይረዳውም።

“እንግሊዝኛ እችላለሁ፤ በዚያ ደግሞ ኩራት ይሰማኛል፤ በዚያ ላይ የቼልሲ ቡድን ደጋፊ ነኝ” ይላል በኩራት።

እግር ኳስ የሚጫወቱ ልጆች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኬንያ ማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ ሲጀመር ይደምቃሉ። ብዙዎች ይወራረዳሉ፤ በጨዋታ መልክ ይበሻሸቃሉ፤ ይቀላለዳሉ። ሳቅና ጨዋታው ይደምቃል።

በኬንያ ጎዳናዎች እስከ ቢሮዎች ድረስ የብሪቲሽ ሥርወ መንግሥቱ ቅሪቶች ጎልተው ይታያሉ።

ለምሳሌ ጠበቃው ፓል ሙቲ ቢሮው ኪሊማኒ ይገኛል። ችሎት ሲሰየም አናቱ ላይ የሚያጠልቀው እንግሊዞቹ የሚያደርጉትን ማጌጫ ነው። የኬንያ የትምህርት ሥርዓቱ፣ የአስተዳደርና የሕግ አካሄዱ ሁሉ የተቀዳው ከቅኝ ገዢዎች ነው።

ነገር ግን ከቅኝ ግዛቱ በአርበኞች ላይ ያሳደረውን ጠባሳ ማንም ዞር ብሎ የሚያየው አይመስልም።

ምናልባትን ይህንን አሁን በጉብኝት ላይ ያሉት ንጉሥ ቻርለስ አንስተው ይቅርታ ይጠይቁበት ይሆናል።

ምንም እንኳ የእንግሊዝ መንግሥት ለተፈጸመው ነገር ይቅርታ ጠይቆ ካሳ ቢከፍልም ያ ግን ለአርበኞቹ በቂ ሆኖ አይታያቸውም።

አርበኞቹ እንደሚሉት የተካሱት አሁን በሕይወት ኖረው ግርፋት እንደደረሰባቸው በሐኪሞች ማረጋገጥ የቻሉት ብቻ ናቸው ይላሉ።

ቸል ከተባሉት መካከል ታላይ የሚባሉት ጎሳዎች ይገኙበታል። የናንዲ ማኅበረሰብ የሆኑት እነዚህ ኬንያዊያን የመሪያቸው የራስ ቅል እንዲመለስ ይሻሉ።

መሪያቸው ኮይታሌል ሳሙኤ ይባላሉ። ታግሎ አታጋይ ሥመ ጥር አርበኛ ነበሩ። በዱር በገደል እንግሊዝን ተፋልመዋል።

በአንድ ወቅት ግን የሰላም ስምምነት እንፈርም ይምጡ ብለው እንግሊዞች አታለው ገደሏቸው። አሁን የራስ ቅላቸው በዩኬ ሙዝየም ይገኛል።

የናንዲ ጎሣ መሪዎች የጀግናቸው ራስ ቅል እንዲመለስ ለንጉሡ ጥያቄ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እማማ ሙቴኒ አዲሱ ትውልድ ይህን አገር ስላጸኑት አርበኞች ቢያውቅ ደስ ይመኛሉ።

በትግሉ የቆሰሉ፣ የተሰቃዩ የተገደሉ ሁሉ መካስ አላባቸው ይላሉ። ይቅር መባባሉ ከዚያ ነው መጀመር ያለበት ሲሉ ያሰምሩበታል።

“አሁን ልባችን ጥላቻ የለውም፤ ያለፈው አልፏል፤ ሰው ይቅር ካልተባባለ እንዴት ይሆናል፤ ሆኖም ግን መሬት እንዲሰጠኝ እሻለሁ” ይላሉ።

የንጉሱን ጉብኝት የተቃወሙ ኬንያውያን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የንጉሱን ጉብኝት የተቃወሙ ኬንያውያን