ፑቲን ሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ አገራቸውን የበለጠ ጠንካራ እያደረጋት ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, RUSSIAN GOVERNMENT
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን ሞስኮ ላይ የጣሏቸው ማዕቀቦች አገራቸውን የበለጠ ጠንካራ እያደረጋት ነው አሉ።
ፕሬዝዳንቱ ሻንጋሃይ ኮኦፐሬሽን ኦርጋናይዜሽን በተባለው የአገራት ስብስብ ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር አገራቸው የምዕራባውያን ጫናን መከላከሏን ትቀጥላለች ብለዋል።
ፑቲን ሻንግሃይ ኮኦፕሬሽን ኦርጋናይዜሽን (ኤስሲኦ) የተባለው ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድ እና ፓኪስታንን ጨምሮ የእስያ አገራትን አቅፎ የያዘ ጥምረት ሲሆን፣ አባል አገራቱ በራሳቸው ገንዘብ እንዲገበያዩ የቀረበውን አማራጭ ደግፈዋል።
ፑቲን በአገራቸው ሩሲያ እና በቻይና መካከል ከሚደረገው ግብይት በ80 በመቶ የሚሆነው የሚፈጸመው በአገራቱ ገንዘቦች ሩብል እና ዩዋን መሆኑን ገልጸው፣ ሌሎች የጥምረቱ አባል አገራትም ይህን እንዲከተሉ አሳስበዋል።
ፑቲን በሕንድ አዘጋጅነት እየተካሄደ ባለው ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አገራቸው ለምዕራባውያን ጫና እንደማትንበረከክ ገልጸዋል።
“ሩሲያ እነዚህን ሁሉ ማዕቀቦች፣ የውጭ ጫናዎች እና ትንኮሳዎችን ተቋቁማ ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ እድገቷ ቀጥሏል” ብለዋል።
ፑቲን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቫግነር በተባለው የቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን አመጽ ከተካሄደባቸው በኋላ በተደጋጋሚ በአደባባይ እየታዩ ነው።
ፑቲን ሞስኮ ላይ ተቀምጠው በኢንተርኔት አማካይ በተሳተፉበት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር “በአመጽ ወቅት የሩሲያ ሕገ-መንግሥት እንዲጠበቅ እና የሩሲያውንን ሕይወት ለመታደግ ድጋፋቸውን ለሰጣችሁ የኤስሲኦ አገራት መሪዎች ምስጋዬ ይድርሳችሁ” ብለዋል።
ፑቲን በዚህ ንግግራቸው ጎረቤት አገር ቤላሩስ በቀጣይ ዓመት የኤስሲኦ ቋሚ አባል ለመሆን ያቀረበችውን ጥያቄ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በበኩላቸው በጥምረቱ አባል አገራት መካከል የንግድ እና የቴክኖሎጂ ልውውጥ መጨመር አለበት በማለት ስለ ቀጠናው ደኅንነት ተናግረዋል።
በቅርቡ ዋሽንግተን ዲሲ በተገኙበት ወቅት በቀይ ምንጣፍ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው የነበሩት ሞዲ፤ በዚህ ንግግራቸው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ስለፈጸመችው ወረራም ይሁን ከቻይና ጋር ስለሚያወዛግባቸው የድንበር ጉዳይ ያሉት ነገር የለም።
እአአ 2020 ላይ ቻይና እና ሕንድ በሚወዛገቡበት ድንበር አቅራቢያ የሁለቱ አገራት ወታደሮች ግጭት ውስጥ ገብተው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ ነበር። በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት ፈጥሮ የቆየው የድንበር ጉዳይ አሁንም ድረስ መፍትሄ አልተበጀለትም።
ሞዲ በንግግራቸው ሕንድ ለረዥም ዓመታት እንደ ጠላት የመትመለከታትን ፓኪስታን ወርፈው አልፈዋል።
ሞዲ ድንበር ተሻጋሪ የሽብር ተግባራትን በጋራ መከላከል አለብን በሚለው ንግግራቸው “አንዳንድ አገራት ድንበር ተሻጋሪ ሽብርን እንደ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ አድርገው ይጠቀማሉ። ለአሸባሪዎች ከለላ ይሰጣሉ. . . ኤስሲኦ እነዚህን አገራት ከማውገዝ ወደ ኋላ ማለት የለበትም” ብለዋል።
ለሞዲ ንግግር ምላሽ በሚመስል መልኩ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚንስትር ሻሃባዝ ሻሪ ደግሞ “የአገር ውስጥ ፖለቲካ አጀንዳን ለማሳካት” አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች መጨቆን የለባቸውም ብለዋል።
ከፍተኛ የእስልምና እምነት ተከታይ ቁጥር ያላት ፓኪስታን በአብዛኛው የሂንዱ እምነት ተከታይ በሚበዛባት ሕንድ የሚገኙ ሙስሊሞች በመንግሥት ይጨቆናሉ ስትል ትከሳለች።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ዢንፒንግ ተራቸው ደርሶ ንግግር ሲያደርጉ በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት አስፈላጊነት ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
ቻይና እና ሩሲያ ከሌሎች አራት የመካከለኛው እስያ አገራት ጋር በመሆን እአአ 2001 ላይ ነበር በቀጠናው የምዕራባውያንን ተጽእኖ ለመግታት ኤስሲኦን የመሠረቱት።
ሕንድ እና ፓኪስታን ጥምረቱን 2017 ላይ ተቀላቅለዋል። ኢራን ደግሞ ከዚህ ዓመት ጀምራ አባል ተደርጋለች።
ይህ ጥምረት ከምዕራባውያን ጋር ያላቸው ግንኙነት ከመቼውም በላይ ለሻከረባቸው ቻይና እና ሩሲያ ጠቃሚነቱን አስመስክሯል።
ምንም እንኳ ኤስሲኦ ተጽእኖ ፈጣሪነቱ ከቡድን 20፣ ከቡድን 7 ወይም ብሪክስ ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም፤ በኤስሲኦ ጥምረት ውስጥ ያሉ አገራት የዓለማችን 40 በመቶ ሕዝብ መያዛቸው፣ እንዲሁም ከዓለም የነዳጅ ክምችት 20 በመቶ የሚሆነው በኅብረቱ አገራት መገኘቱ ጠንካራ ግምት እንዲሰጠው ምክንያት ናቸው።












