ታሊባን በአፍጋኒስታን ያሉ ፀጉር ቤቶች እና የውበት ሳሎኖች እንዲዘጉ አዘዘ

አፍጋኒስታን የውበት ሳሎን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አፍጋኒስታንን እያስተዳደረ ያለው ታሊባን በአገሪቱ ያሉ ፀጉር ቤቶች እና የውበት ሳሎኖች በሙሉ እንዲዘጉ አዘዘ።

በአገሪቱ ጥብቅ የእስልምና ሕጎችን ያሚስፈጽመው ሚንስቴር መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ፣ በፀጉር ቤት እና በውበት ሳሎኖች ሥራ የተሰማሩ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሥራቸውን ማቆም አለባቸው ብለዋል።

ታሊባን እአአ 2021 ላይ የአገሪቱን የመሪነት ሥልጣን መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ፣ የዜጎችን በተለይ ደግሞ የሴቶች መብቶች ላይ ከፍተኛ ገደብ ሲጥል ቆይቷል።

ታሊባን ታዳጊዎችን ጨምሮ ሴቶች ወደ ትምህር ቤት እንዳይሄዱ ገደብ ጥሏል። አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረጊያ ቦታ እና የሕዝብ መናፈሻ ቦታዎች ላይም ሴቶች እንዲታዩ አይፈቀድላቸውም።

በቅርቡ ደግሞ ታሊባን የአፍጋኒስታን ሴቶች ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቀጥረው መሥራት አይችሉም ብሏል።

ከዚህ ባለፈም ታሊባን ሴቶች ዐይኖቻቸውን ብቻ የሚያሳይ ልብስ ብቻ እንዲለብሱ እንዲሁም ከመኖሪያቸው ከ72 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው የሚጓዙ ከሆነ ዘመዳቸው በሆነ ወንድ መታጀብ አለባቸው የሚል ሕግ አውጥቶ እያስፈጸመ ነው።

ታሊባን የሴቶችን መብቶች የሚገድቡ ጥብቅ ሕግጋትን ማውጣቱ ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ትችት ቢያደርስበትም ቡድኑ ሕጎችን ከማስፈጸም ወደ ኋላ አላለም።

ታሊባን ከዚህ ቀደም ከእአአ 1996 እስከ 2001 ላይ አፍጋኒስታንን ያስተዳድር በነበረበት ወቅት የውበት ሳሎኖችን ይዘጋ ነበር። ይሁን እንጂ ታሊባን ከሥልጣን መባረሩን ተከትሎ የውበት ሳሎኖች ዳግም ተከፍተው ነበር።

አዲሱ የታሊባን ጥብቅ ትዕዛዝ ከተሰማ በኋላ አንዲት የአፍጋኒስታን ዜጋ ለቢቢሲ ስትናገር፤ “ታሊባን ከአፍጋኒስታን ሴቶች መሠረታዊ የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶችን እየነጠቀ ነው” ብላለች።

“የሴቶችን መብቶች እየጣሱ ነው። ዜናውን ስሰማ ከፍተኛ ድንጋጤ ነው የተሰማኝ። ታሊን የሴቶችን ገላ ከመቆጣጠር ውጪ ፖለቲካዊ ዓላማ እና ዕቅድ ያለው አይመስለኝም። በየትኛው ደረጃ የሴቶችን ማኅበራዊ ሕይወት ለማጥፋት ነው ጥረታቸው” ብላለች።

የአሜሪካን ከአፍጋኒስታን መውጣት ተከትሎ ከሁለት ዓመት በፊት ታሊባን አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ የውበት ሳሎኖች ክፍት ሆነው ቆይተው ነበር።

ከታሊባን መመለስ በኋላ የውበት ሳሎኖች ውስጣቸው እንዳይታይ በመጋረጃ ተሸፍነው እና ለማስታወቂያ ተብለው በውበት ሳሎች የሚለጠፉ የሴቶች ምስል በቀለም እንዲጠፉ ተደርገው ተጠቃሚዎች ከሞላ ጎደል አገልግሎቶችን ሲያገኙ ቆይተዋል።

የታሊባን መንግሥት ፀጉር ቤቶች እና የውበት ሳሎኖችን ለመዝጋት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ያለው ነገር የለም። እንደ አማራጭም ከታሊባን የተሰጠ መፍትሄ የለም።

አንድ ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀች ሴት በመዲናዋ ካቡል ገና ከአሁኑ የውበት ሳሎኖች እየተዘጉ እንደሆነ ትናገራለች።

“ወጣ ብዬ ስለመለከት በአካባቢዬ ያሉ ፀጉር ቤቶች በሙሉ ተዘግተዋል። ይህ ለአፍጋን ሴቶች ከአስደንጋጭም በላይ የሆነ ዜና ነው” ብላለች።