ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዶናልድ ትራምፕ ከንጉሥ ቻርለስ ሦስተኛ የቀረበላቸውን የጉብኝት ግብዣ ተቀበሉ
ዶናልድ ትራምፕ ከንጉሥ ቻርለስ 3ኛ እና ንግሥት ካሚላ የቀረበላቸውን ይፋዊ ጉብኝት ግብዣ መቀበላቸውን ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት አስታወቀ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ጋር በመሆን ከመስከረም 7 እስከ 9 2018 ዓ.ም. በዊንሶር ቤተመንግሥት በሚደረግላቸው ግብዣ ላይ ይገኛሉ።
የተመረጠው የጉብኝት ቦታ እድሳት እየተደረገለት መሆኑን የባኪንግሃም ቤተ መንግሥት አስታውቋል።
ትራምፕ በመጀመርያው የሥልጣን ዘመናቸው እ.አ.አ በ2019 በንግሥት ኤልሳቤጥ ዳግማዊ ጋባዥነት ጉብኝት አድርገዋል።
በተለምዶ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን የሚመጡ ፕሬዚደንቶች ለይፋዊ ጉብኝት ግብዣ አይቀርብላቸውም። በምትኩ ከንጉሡ ጋር ለሻይ ወይም ለምሳ ብቻ ይገናኛሉ።
የዝግጅቱ ሙሉ መርሃ ግብር እስካሁን ድረስ አልተገለጸም።
ነገር ግን እንደ ሁሉም የዚህ ዓይነት ጉብኝቶች፣ ሙሉ የአቀባበል ሥርዓት እና በዊንዘር ቤተመንግሥት በሚገኝ አዳራሽ ውስጥ ደማቅ ግብዣ ይኖራል።
በቤተ መንግሥቱ ግቢ ውስጥ የሚኖሩትን የዌልሱ ልዑል እና ልዕልትን ጨምሮ ሁሉም የንጉሣዊው ቤተሰብ ከፍተኛ አባላት ይሳተፋሉ።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባለፈው ሳምንት በንጉሡ አስተናጋጅነት ለይፋዊ ጉብኝት በቤተ መንግሥቱ ተገኝተው ነበር።
ማክሮን እና ባለቤታቸው ብሪጂት በዊንሶር ከተማ በሠረገላ ታጅበው ተንሸራሽረዋል።
የትኛውም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጉብኝት የፀጥታ እና ደህንነት ተግዳሮቶችን አብሮ ይዞ ይመጣል።
በ2019 ጉብኝታቸው ወቅት፣ ለደህንነት ሲባል ትራምፕ በመኪና ከመንቀሳቀስ ይልቅ ከቦታ ቦታ በሂሊኮፕተር መብረርን መርጠዋል።
በተጨማሪም ትራምፕ ከፓርላማ አባላት ጋር ተገናኝቶ የመወያየት ዕድል ይኖራቸው እንደሆን ግልጽ አይደለም።
ብዙ ጊዜ በይፋዊ የመንግሥት ጉብኝት ውስጥ ይህ ይካተታል።
የአገሪቱ ምክር ቤቱ ትራምፕ ለጉብኝት በሚመጡበት ወቅት እረፍት ላይ ነው።
በየካቲት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ትራምፕን በዋይት ሐውስ ባገኙበት ወቅት ከንጉሡ የተላከውን የግብዥ ደብዳቤ ሰጥተዋቸው ነበር።
ትራምፕ በሚያዝያ ወር ላይ "እኔ የቻርለስ ጓደኛ ነኝ፣ ለንጉስ ቻርለስ እና ለቤተሰቡ ዊልያም ትልቅ ክብር አለኝ። በእውነት ለቤተሰቡ ትልቅ ክብር አለን" ብለው ነበር።
ግብዣው የመጣው ሰር ኪር የዩክሬን ጦርነትን በተመለከተ በትራምፕ ላይ ተጽእኖ ለማሳረፍ እና ትራምፕ በዩናይትድ ኪንግደም ምርቶች ላይ የሚጥሉትን ታሪፍ ለማስቀነስ ጥረት እያደረጉ በነበረበት ወቅት ነበር።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በዚህ ወር መጨረሻ በስኮትላንድ በአበርዲንሻየር አዲሱን የጎልፍ መጫወቻ ይከፍታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
መጀመሪያ ላይ ንጉሡ እና ትራምፕ በዚያ ጉዞ ወቅት መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይገናኛሉ ተብሎ ነበር።
ነገር ግን ከመስከረም ጉብኝታቸው በፊት ምንም ዓይነት የግል ግንኙነት እንደማይኖር ታውቋል።